ሩሲያ በኃይል በያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ምርጫ አካሄደች

የአካባቢ ምርጫው እየተደረገ ያለው በአራት ክልሎች ነው

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, የአካባቢ ምርጫው እየተደረገ ያለው በአራት ክልሎች ነው

በሩሲያ በኃይል በተያዙ ግዛቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች ወጥተው ድምጽ እንዲሰጡ እየተደረጉ ነው።

ይህን የአካባቢ ምርጫ ዩክሬን ‘ቀልድ’ ስትል አውግዘዋለች።

ዩክሬን እንደምትለው ይህ ሩሲያ እያካሄደችው ያለው ምርጫ ሕጋዊ መሠረት የለውም።

ለምርጫ የቀረቡት ሁሉም እጩዎች ሩሲያዊያን ወይም የሩሲያ ደጋፊዎች ሲሆኑ ለእጩነት የቀረቡትም በሩሲያ መንግሥት ተመልምለው እንደሆኑ ዩክሬን ትገልጣለች።

ብዙዎቹ ነዋሪዎች ድምጽ እየሰጡ ያሉትም የሩሲያ ወታደሮች በሚገኙበት ሁኔታ 'ተገደው' ነው።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ሕዝቡ ወጥቶ ምርጫ እንዳይሰጥ ጠይቀዋል።

ማንኛውም በዚህ ምርጫ የሚሳተፍ ዩክሬናዊ ወደፊት ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል የዩክሬን ባለሥልጣናት።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ‘ሩሲያ በኃይል በያዘቻቸው ቦታዎች እያካሄደች ያለችው ምርጫ ተቀባይነት የለውም’ ብለዋል።

ይህ የአንቶኒ ብሊንከን አስተያየት ሩሲያን ያስቆጣ ሲሆን በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር ‘አሜሪካ በሩሲያ የውስጥ ጉዳይ መግባት የለባትም’ ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በመጪው እሑድ ይጠናቀቃል የሚባለው ምርጫ ሩሲያ ገና ሙሉ በሙሉ ባልተቆጣጠረቻቸው አራት ክልሎች የሚደረግ ነው።

ይህም በምሥራቅ በኩል ዶኔስክና ሉሃንስክ፣ በደቡብ በኩል ዛፖሬዥያ እና ኬርሶን ክልሎችን ያካተተ ነው።

እነዚህ አራት ክልሎች የሩሲያን ጠቅላላ ግዛት 15 በመቶ የሚይዙ ናቸው።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት፣ መስከረም ወር ላይ ሩሲያ እነዚህን ግዛቶች በኃይል ከያዘች በኋላ ነዋሪዎችን ሕዝብ ውሳኔ በማስደረግ 'የሩሲያ አካል ነን' ብለዋል በሚል ነው ሕጋዊ ግዛቷ አድርጋ የምትወስዳቸው።

ይሁንና ይህ ሕዝበ ውሳኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት ደርሶበታል።

በሩሲያና ዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከቅርብ ቀናት ወዲህ ዩክሬን አይሰበርም የተባለ የሩሲያ ወታደራዊ ምሽግን ሰብሬ ገብቻለሁ በሚል ወታደራዊ ድል እንደቀናት ገልጻለች።