የኡጋንዳው ቤተ እምነት የዓለም የጭብጨባ ክብረ-ወሰንን ሰበረ

ማጨብጨብ የታከተው ምዕመን ከቸርቹ እንዲወጣ ተደርጓል

የፎቶው ባለመብት, Phaneroo Ministries

የምስሉ መግለጫ, ማጨብጨብ የታከተው ምዕመን ከቸርቹ እንዲወጣ ተደርጓል

አንድ የኡጋንዳ ቤተ እምነት በጭብጨባ የዓለም ጊነስ ክብረ ወሰንን ሰበረ።

የጭብጨባ ክብረ ወሰኑን የሰበሩት የዚህ ቸርች ምዕመናኑ ለረዥም ሰዓት ያለማቋረጥ በከፍተኛ ድምጽ በማጨብጨባቸው ነው።

ጊነስ እንዳረጋገጠው የምዕመናኑ ጭብጨባ ለሦስት ሰዓታት ሳይቋረጥ ዘልቋል።

ለሦስት ሰዓት ብቻም ሳይሆን ሦስት ሰዓት ከ16 ደቂቃ ላይ ነው የቆመው።

ጭብጨባው በክብረ ወሰን እንዲመዘገብ ያስቻለው ለዚህን ሰዓት መቆየቱ ብቻ ሳይሆን እንደጋለ መዝለቁ ነበር።

የጭብጨባው የድምጽ ምጣኔው 88.5 ዲሳይቤል (dB)ነበር።

ጊነስ ክብረ ወሰን ለመመዝገብ ትንሹ የድምጽ ምጣኔ 80 ዲሳይቤል (dB) ነው።

“ለኢየሱስ አጭብጭቡ” ("Clap For Jesus") በሚል የተሰየመው ይህ ክብረ ወሰንን የሰበረ ጭብጨባ የተደረገው በኡጋንዳ ዋና መዲና ካምፓላ ውስጥ በሚገኝ ፋኔሩ በሚባል ቸርች ነው።

ጭብጨባውም የዚህን ቸርች 9ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የተሰናዳ ነበር።

የዚህ ቸርች መሪ ግሬስ ሉቤጋ በጊነስ ክብረ ወሰን ምዝገባ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ክብረ በዓሉ ዋናው ዓላማው ምዕመናንን ለማመስገን ነው።

ከሦስት ሰዓት በዘለቀው ጭብጨባ 926 ምዕመናን እጃቸው እስኪቀላ ድረስ አጨብጭበዋል።

ከአቅም በላይ ሆኖባቸው መቀጠል ያልቻሉት ከቸርቹ እንዲወጡ ሲደረግ ነበር።

ይህ ሥነ ሥርዓት በቀጥታ ለሕዝብ ሲተላለፍ የነበረ ሲሆን የኡጋንዳ ደረጃ ምደባ ኤጀንሲ እና የብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናት ታዝበውታል።

ይህ አዲስ ክብረ ወሰን ከመሰበሩ በፊት በዩኬ በ2019 ክላርክ ስቲቨንስ እና ፌስቲቫል ኦውሰምነስ ረዥም ሰዓት አጨብጫቢ ተብለው ተይዘው ነበር። ሰዓቱም ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ነበር።