በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የታዩ ትልልቅ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ክስተቶች የትኞቹ ነበሩ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጓዙን ጠቅልሎ እየሄደ ያለው 2015 ዓ.ም ጉልህ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊ እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የተከናወኑበት ዓመት ነው።
ከእነዚህም መካከል በፈጣን ዕድገት የሚገኙ የአምስት አገራት ጥምረት የሆነው ብሪክስ በቅርቡ በአባልነት ከተቀበላቸው ስድስት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች።
ኢትዮጵያ ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ እንደ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል የቆጠረችው ሲሆን፣ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስገኘቱ ረገድ የጎላ እመርታ ያስገኛል ብላለች።
በዚህ ዓመት ከተከናወኑ አበይት ጉዳዮች መካከል ደግሞ ሌላው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት ነው።
ኢትዮጵያ የመጨረሻውን የሕዳሴ ግድብ ሙሌት “በተሰካ ሁኔታ” ማካሄዷን የገለፀችው ትናንት ጳጉሜን 5 2015 ዓ.ም ነበር።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች አስራ ሁለት ዓመታት ያህል አስቆጥራለች።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብን በውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ሲወተውቱ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ለአራት ዙር ግድቡ ውሃ እንዲይዝ አድርጋለች።
ለመሆኑ ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
የፕሪቶርያ ሰላም ስምምነት
በኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት የተፈረመው በዚህ ዓመት የጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል በተፈረመው ስምምነት መሰረት በጦር መሳርያ ይደረግ የነበረ ተኩስ ወድያው ቆሟል፤ በሂደትም በትግራይ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶች ተመልሰዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወትን በመቅጠፍና በማቁሰል፣ ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን ለከፋ ድህነት የዳረገውና በትሪሊዮን ብሮች የአገር ኢኮኖሚ ጉዳትና ኪሳራ ያደረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በድርድር ተቋጭቶ አንፃራዊ ሰላም ሠፍኗል።
ይኹን አንጂ የረድዔት ድርጅቶች በክልሉ ያቀርቡ የነበረውን የሰብዓዊ እርዳታ በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች ሳይሆን ከታለመለት ዓላማ ውጭ ገበያ ላይ ሽያጭ መቅረቡን እንዲሁም ስርቆት ተፈጽሟል በሚል ለጊዜው አቋርጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት፣ ዩኤስኤአይዲ በጦርነቱ በከፋ ለተጎዳችው ትግራይ የሚያቀርቡትን እርዳታ በማቋረጣቸው በርካታ ሕጻናት እና እናቶች ለሞት መዳረጋቸውን የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ።
የፌደራል መንግሥቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር ‘ሸኔ’ ድርድር በዛንዚባር
በዚህ ዓመት ከታዩ የሠላም ንግግሮች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ራሱን የኦሮሚያ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው ‘ሸኔ’ በዛንዚባር ያደረጉት ንግግር ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በታንዛኒያ ዛንዚባር ደሴት ተገናኝተው ለዘጠኝ ቀናት ገደማ የሰላም ንግግር ያደረጉት በዚህ ዓመት ነበር።
በዛንዚባር በነበረው የመጀመርያው ምዕራፍ ንግግር ወሳኝ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረስ ባይቻልም ሁለቱም ወገኖች ለቀጣይ ውይይት ፈቃደኛ ስለመሆናቸው የንግግሩን መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጡት የተናጠል መግለጫ አስታውቀው ነበር።
የተጀመረው የሠላም ንግግር ያልቀጠለ ሲሆን፣ ይልቁኑስ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሉ በኩል በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚደረጉ ፍልሚያዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ይሰማል።

ከአስር ዓመት በኋላ ህልውናው ያከተመው የክልሎች ልዩ ኃይል
በዚህ ዓመት ከተከናወኑ ትልልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የክልሎች ልዩ ኃይል አባላት መበተን ነው።
በሚዘያዝያ ወር ላይ በአገሪቱ ውስጥ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል የፀጥታ አደረጃጀት ከዚህ በኋላ እንደሌለ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይፋ አደረጉ።
በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ክልሎች ውስጥ የፀጥታ ሥራዎችን የሚያከናውኑት መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊሶች ብቻ ሆነዋል።
በወቅቱ ከዚህ በኋላም በክልል ልዩ ኃይል ስም “ተልዕኮም ሆነ ግዳጅ የሚቀበል ኃይል አይኖርም” ሲሉ ኤታማዦር ሹሙ ተናግረዋል።
በፌደራል መንግሥቱ በቀረበው ዕቅድ መሠረት የክልል ልዩ ኃይል አባላት በምርጫቸው መሠረት ወደ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና ክልል ፖሊስ የሚገቡ ሲሆን፣ ፍላጎት የሌላቸውም መቋቋሚያ አግኝተው ወደ ሚመርጡት ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳሉ ተብሏል።
በዚህም አዲሶቹን ጨምሮ በክልሎች ከፖሊስ በተለየ ሁኔታ በሥልጠና፣ በትጥቅ እና በአደረጃጀት የተዋቀሩት ልዩ ኃይሎች ከአስር ዓመታት በኋላ ህልውናቸው አብቅቷል።
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት
የፌደራል መንግሥት ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት ያለውን ዕቅድ ይፋ ካደረገ በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ ልዩ ኃይሉን ለምን ይፈርሳል በሚል ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።
በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎችም በመከላከያ ሠራዊት እና በተቃዋሚዎች፣ በልዩ ኃይል እና በፋኖ አባላት መካከል በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት እስከመጥፋት ደርሷል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የግጭቱን መባባስ ተከትሎ የታጠቁ ኃይሎች የክልሉን ትልልቅ ከተሞች እስከ መቆጣጣር ደርሰዋል።
ይህ ግጭት ከክልሉ አቅም ውጪ በመውጣቱ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጆ እርምጃ መወሰድ መጀመሩ ተገልጿል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ቅዳሜ ሐምሌ 29/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ከአርብ ጀምሮ “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ስምሪት የሚሰጡ፣ ችግሩን የሚያባብሱ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማድረግ ተጀምሯል” ብለዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትን አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በ12 ክልሎች የተዋቀረችው ኢትዮጵያ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ሁሉም የደቡብ ኢትዮጵያ ዞኖች እና ማኅበረሰቦች በሚያስብል ሁኔታ በተናጠል ክልል ለመመሥረት በምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ አሳልፈው ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው ነበር።
አገሪቱ ካሏት ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት የሚገኙበት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አሁን ወደ አራት ክልልነት ተሸጋግሯል።
የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል በመውጣት ቀዳሚ ሲሆን፣ በመቀጠልም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አሁን ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንዲመሠረት ተወስኗል። የቀሩት ደግሞ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር ይቀጥላሉ።
የሲዳማን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 28/2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለአዲሱ ለ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ይሁንታን ሰጥቶ የፌዴሬሽኑ አካል ሆኗል።
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ተካተው የነበሩ የጌዴኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የዲራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው አዲሱን ክልል የመሠረቱት።
የኦሮምያ እና የትግራይ ሲኖዶሶች ቅሬታ እና ጥያቄ
ጥር 14/2015 ዓ.ም. የኦሮምያ የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ የሚባል ሊቋቋም ሙከራ ተደርጎ ነበር።
ከኦሮሚያ የተገኙ ሦስት ጳጳሳት የቤተ ክርስትያኗ ሲኖዶስ ልዩነትን የሚያስተናግድ እና አካታች አይደለም በማለት አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ።
ችግሩ በሽምግልና መፍትሔ አግኝቶ፤ የተወገዙት አባቶች በይቅርታ ተመለሰዋል።
የቀረቡ ጥያቄዎችም በቤተክርስትያኗ ሥርዓት እና ደንብ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኙ ከስምምነት ተደረሷል።
በሌላ በኩል ለሁለት ዓመታት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ሲኖዶሱ ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን በገንዘብ እና በቅስቀሳ በጦርነቱ ተሳትፏል ብለው የትግራይ አባቶች ወቅሰዋል።
በትግራይ የቤተ ክርስትያኗ ተቋማት ውድመትና ምዕመናን ላይ ግድያ ሲፈጸምም ዝምታን መርጧል ሲሉ ይከስሳሉ።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀድሞ ቢቃወመውም ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም. የትግራይ አባቶች መንበረ ሰላማ ብለው በሰየሙት ቤተ ክህነት ከተመረጡት አስር ኤጲስ ቆጶሳት መካከል የስድስቱን ሹመት በአክሱም አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ በአክሱም ጽዮን ማርያም የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ የትግራይ አባቶችን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ተሽሮ እንዲለዩ መወሰኑን አስታውቋል።
ይህንን ውግዘት ተከትሎ የትግራይ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. የትግራይ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ውግዘቱ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ድርቅ
በምሥራቅ አፍሪካ ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ በመጥፋቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ተከስቶ ነበር።
በዚህም ከ36 ሚልዮን በላይ ሰዎች በድርቁ ምክንያት እርዳታ ጠባቂ ሆነው የነበረ ሲሆን ከሁለት ሚልዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከቀያቸው መሰደዳቸውን የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሪፖርት ጠቁሞ ነበር።
ከእነዚህ አስቸኳይ እርዳታ ፈላጊ ሰዎች 24 ሚልዮኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው።
የዝናብ እጥረቱ በኦሮሚያ በቦረና፣ ጉጂ እና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ በደቡብ ኦሞ እና ጎፋ እንዲሁም በሶማሌ ክልል አካባቢዎች ለአስርት ዓመታት ያልታየ ከባድ ድርቅን የተከሰተባቸው አካባቢዎች ናቸው።












