የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በውጣ ውረድ እና በስጋት መካከል

መስቀል የያዙ ቄስ እና የእጣን ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላት በአገሪቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ገጽታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋለች።

በአንድ ወቅት በአገሪቱ ፖለቲካ ትልቅ ተጽዕኖ የነበራት ቤተ ክርስቲያኒቱ በጊዜ ሂደት ይህ ሚናዋ እየደበዘዘ መጥቷል።

በአገሪቱ የሚከሰቱ የፖለቲካ ለውጦች የቤተ ክርስቲያኗን ሚና እየቀያየሩት ይገኛሉ።

ባለፉት ወራት ደግሞ በሁለት አቅጣጫ ፈተና ተደቅኖባት ነበር።

አንዱ ምላሽ ሲያገኝ ሁለተኛው መከፋፈልን አስከትሏል።

በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ እና ሃይማኖቶች ጥናት ክፍል ባልደረባ ለሆኑት ለፕሮፌሰር ቴሪ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ አሁን ተፈጥሮ የታየው መከፋፈል ቀደም ብሎ አለመፈጠሩ “የሚደንቅ” ነው።

ለዚሀም ምክንያታቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት 30 ዓመታት በብሔር ፖለቲካ ሲናጥ መቆየቱ ነው።

ይህ ደግሞ እንደ እርሳቸው ማብራርያ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሃይማኖቶች ዙርያ ለሠሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ለተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኗ የመለየት ጉዳይ አዲስ አይደለም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ምረቃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ተካልኝ፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከግብፅ የተሾሙ ፓትሪያርክ ተነስተው በምትካቸው ከኢትዮጵያ እንዲሾሙ መደረጉን ያስታውሳሉ። ይህ የሆነው ያለ ግብፅ ኮፕቲክ ዕውቅና ነው።

ኤርትራ ነጻ ስትወጣ እና አዲስ ሲኖዶስ ስታቋቁምም በፊት ከነበረችበት የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ዕውቅና አለማግኘቷ “ትልቅ ችግር ፈጥሮ ነበር” ይላሉ።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ይሁን ደርግ እና ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ዕውቅና ያላገኙ ሹመቶች መከናወናቸውን ያወሳሉ።

ኦሮሚያ እና ትግራይ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥር 14/2015 ዓ.ም. የኦሮሚያ የብሔር ብሔርሰቦች ሲኖዶስ የሚባል ሊቋቋም ሙከራ ተደርጎ ነበር።

ከኦሮሚያ የተገኙ ሦስት ጳጳሳት የቤተ ክርስትያኗ ሲኖዶስ ልዩነትን የሚያስተናግድ እና አካታች አይደለም በማለት አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ።

ችግሩ በሽምግልና መፍትሔ አግኝቶ፤ የተወገዙት አባቶች በይቅርታ ተመለሱ። የቀረቡ ጥያቄዎችም በቤተክርስትያኗ ሥርዓት እና ደንብ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኙ ከስምምነት ተደረሰ።

ለሁለት ዓመታት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ሲኖዶሱ ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን በገንዘብ እና በቅስቀሳ በጦርነቱ ተሳትፏል ብለው የትግራይ አባቶች ወቅሰዋል።

በትግራይ የቤተ ክርስትያኗ ተቋማት ውድመትና ምዕመናን ላይ ግድያ ሲፈጸምም ዝምታን መርጧል ሲሉ ይከስሳሉ።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀድሞ ቢቃወመውም ሐምሌ 16/2015 ዓ.ም. የትግራይ አባቶች መንበረ ሰላማ ብለው በሰየሙት ቤተ ክህነት ከተመረጡት አስር ኤጲስ ቆጶሳት መካከል የስድስቱን ሹመት በአክሱም አከናውነዋል።

የሁለቱም ጥያቄ “ከመሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮት የሚመነጭ ሳይሆን፣ ከአስተዳደር ጋር የተያያዘ” መሆኑን ተካልኝ ይጠቁማሉ።

ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተሉ የሚገልፁት በስዊድን የኤርትራውያን ቤተ ክርስትያን አገልጋይ ቄስ ዮናስ በበኩላቸው፣ መነሻቸው ‘ስር የሰደዱ ናቸው’ ሲሉ የልዩነቶቹን ምክንያቶች ይገልጻሉ።

እንደ ቄስ ዮናስ ገለጻ ቤተክርስቲያኒቱ የገጠማት ፈተና ሲብላላ የቆየ የታሪካዊ ትርክቶች ድምር ውጤት ነው።

አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከአገር ውጪ የነበሩ አባቶችን መመለሳቸውን ይቃወሙ የነበሩ አካላት በጦርነቱ ወቅት ከተፈጠሩ ጉዳዮች ጋር ተዳምረው ቁርሾው ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል ሲሉ ያብራራሉ።

መስቀል

ፖለቲካዊ ጫናዎች እንዳሉ በመግለጽም “በእርግጥ አማርኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ውስጥ የበላይ ሆኖ ቆይቷል” ብለዋል።

በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍት ወደ አማርኛ፣ ኦሮሚኛ እና ትግርኛ መተርጎማቸውን በመጥቀስም “በቋንቋዎች ምክንያት የምትለያይ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፤ ቋንቋም ዋነኛ የልዩነት ምንጭ ሆኖ አይሰማኝም” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በትግራይ ለተፈጠረው ችግር ብዙዎች ሁለት አካላትን ተጠያቂ አድርገው እንደሚያምኑ ተካልኝ ተናግረዋል።

የመጀመሪያዎቹ “የዘውግ ተኮር ፖለቲካ ያለው ጫና ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ (ቤተ ክርስቲያኗ) በፕሮቴስታንት ትምህርት መሠረት ታድሳ መመልከት የሚፈልጉ የተሃድሶያውያን ስውር ሴራ ነው ብለው ይናገራሉ” ሲሉ ይገልጻሉ።

በጉዳዩ ላይ በትግራይ አባቶች ዘንድ ተቃውሞ አለመሰማቱን በመጥቀስም የሃይማኖት አባቶቹ ‘ተጠቂ ናቸው’ ከሚሉት ጀምሮ “ተጠቂ ሳይሆኑ ተባባሪ ወይንም ተሳታፊ ናቸው ብለው የሚያምኑ መኖራቸውንም” ያነሳሉ።

የሚደግፉት ደግሞ በታሪክ፣ በባህል እና በቋንቋ ባልተሳሰረ እና “ከሌላ ቦታ በመጣ ሲኖዶስ መመራት እና መተዳደር ልክ አይደለም” በሚል ከጎኑ መቆማቸውን ጠቁመዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞም “ከሃይማኖት አባቶች በማይጠበቅ መልኩ እስከ ጄኖሳይድ ቅስቀሳ ተደርጓል የሚል ዓይነት ቅያሜም አለ። ይህ የቅያሜውን ጥልቀት ያሳያል” ብለዋል።

የትግራዩ ከኦሮሚያው የሚለየው “ራሳቸውን የትግራይ ማኅበረሰብ አካል አድርገው የሚቆጥሩ ብዙ ሰዎች” አለማውገዛቸው እንደሆነ የሚጠቅሱት ተካልኝ (ዶ/ር)፣ “በኦሮሚያው ግን በሁሉቱም ጎን የቆሙ አካላት ነበሩ” ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትም ጣልቃ አልገባም ማለቱ “በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የሚያደርጉትን ነገር እንዳያደርጉ አንዳች ክልከላ አናደርግባቸውም የሚል ነው” ሲሉ ይገልጹታል።

ፌደራል መንግሥቱ ጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ በሲኖዶሱ ቢጠየቅም ዝምታ መምረጡ አንዳንዶች “ሁኔታውን የሚጠላው አይደለም እንዲሉ አድርጓቸዋል።”

የአውስትራሊያ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ሰረቀብርሃን ወልደ ሳሙኤል ወደ መቀለ ለመጓዝ መከልከላቸው ደግሞ ማዕከላዊው መንግሥት “የተጀመረውን የመለየት ሂደት ደግፏል የሚለውን ለመናገር በጣም የሚያስቸግር ያደርገዋል” ሲሉም ያብራራሉ ተካልኝ (ዶ/ር)።

ሃይማኖት እና ፖለቲካ

እንደ ቄስ ዮናስ እምነት ከሆነ በቤተክርስቲያኗ እየታየ ያለው ቀውስ ዋነኛ ምንጭ የፖለቲካ እና ሃይማኖት ድንበር አለመጠበቁ “ቤተክርስቲያኒቱን እየረበሻት እና እያናወጣት ነው” ይላሉ።

በፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ እና ሃይማኖቶች ጥናት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ቴሪ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

ቄስ ዩናስ በጦርነት ወቅት ቤተ ክርስቲያኗ የወሰደችው አቋም ፖለቲካዊነቱ እንደሚያመዝን በመግለጽም፣ መንግሥት በተለያዩ መንገዶች እጁን ማስገባቱ ለተፈጠረው ቀውስ ምክንያት እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መንግሥታት እና ቤተክርስቲያን የሚገናኙባቸው ሁኔታዎች ሲታዩ እንደቆዩ በመግለጽም “ብልፅግና ሲመጣ የችግሩ ተቀጥያ ሆኖ ታይቷል” ብለዋል።

ፕሮፌሰር ቴሪ ኦስቴቦ፣ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሃይማኖት የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ከመሆን ባለፈ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን በተመለከተ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች እና ከንግግሮቻቸው በኋላ ‘ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ’ ማለታቸው “ከሃይማኖት ጋር የተቆራረጠ ከሚመስለው ኢህአዴግ የተለየ ነው” ሲሉ በምሳሌነት ያነሳሉ።

ይህ ለሃይማኖት ተቋማት በራስ መተማመን ከመስጠቱም ባለፈ “አንዳንድ የሃይማኖት አካላትም ስለ ፖለቲካ እንዲናገሩ ያደረገ ይመስለኛል” ብለዋል።

የኦሮሚያ ሲኖዶስ እንዲመሠረት እንቅስቃሴ ሲደረግ በግልጽ ባይሆንም መንግሥት ለጳጳሳቱ ከለላ መስጠቱ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ክስተቱን እንደደገፈው ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋናው ማጠንጠኛ ብሔር መሆኑን ጠቅሰው ብዙ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች መሠረቴ በሚሉት አካባቢ የተለያዩ ሃይማኖቶች መኖራቸውን አንስተው “ብሔር እና ሃይማኖት እርስ በርስ ሊደጋገፉ ቢችሉም የሚተላለፉበት አጋጣሚ ስለሚኖር የተወሳሰበ ሁኔታን ይፈጥራል” ብለዋል።

መስቀል

ስጋት እና ተስፋ

ለሥነ መለኮት መምህሩ ተካልኝ (ዶ/ር) ጉዳዩ ወዴት ያመራል በሚለው ውስጥ ታሳቢ መደረግ ካለባቸው ጉዳዮች ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ከፓትሪያርኩ እውቅና ማግኘት እና ቤተክርስቲያነወ “ለአዲሱ ለውጥ ምን አይነት ምላሽ ትሰጣለች የሚለው” መሆኑን ያነሳሉ።

እንዲሁም በትግራይ ክልል ውስጥ እንቅስቃሴው ያለው ድጋፍ እና የክልሉ ፍላጎትም ሌላው መታየት ያለበት መሆኑንም ይጠቁማሉ።

ከማዕከላዊ መንግሥት አንጻርም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት የነበረውን ውጥረት እንዲቀጥል በመፍቀድም ሆነ በማስቆም ሂደት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።...ስለዚህ የማዕከላዊ መንግሥቱ በምን ዓይነት መንገድ ነው ይህንን የሚይዘው የሚለው ትልቅ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም የግብፅ፣ የሩሲያ እና የሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡት ድጋፍም ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚጠቁሙት ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ሲኖዶሱ ይቅርታ የጠየቀባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ “አንዳንዶች ማን ያላጠፋ አለ” እያሉ በመሆኑ ነገሩ ሊካረር እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም በግለሰብ ደረጃ ያጠፉ ይቅርታ እንዲጠይቁ ዕድል ቢፈጠር ምናልባት ችግሩን ለማለዘብ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

የፌደራል እና የክልሉ መንግሥታት ፍላጎት እና ጫና በዚህ ሂደት ውስጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በማንሳት “የትግራይ ሕዝብ ቤተኝነቱን እንዲያጠናክር የምንናገራቸው እና የምናሳያቸው ልበ ሰፊነቶች፤ በትዕግስት ነገሩን ለመያዝ ያለን ጥበብ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ነገር ግን “ቅያሜው በጊዜ ሂደት የማያልፍ እና የበለጠ ስር እየሰደደ የሚሄድ ከሆነ ግን፣ ይህ አደረጃጀት አሁን ባለበት የመቀጠል ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል፤ ሆኖም አሁን ያለው ሁኔታ ወዴት እንደሚያመራ መናገር አይቻልም” ብለዋል።

የተፈጥረው መካረር እጅግ ከባድ እና አስጊ መሆኑን የሚጠቅሱት ቄስ ዮናስ “ቤተ ክርስቲያኗ መሆን ወዳልነበረበት...የመበታተን አደጋ እንደተጋረጠባት የሚያሳዩ ብዙ ምክንያቶች እየታዩ መሆናቸው አያጠራጥርም” ይላሉ።

አክለውም ጦርነቱን የመሩ ፖለቲከኞች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ሲነጋገሩ “መሪ እና የዕርቅ አብነት መሆን የነበረባቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንደዚህ በመረረ ሁኔታ መራራቃቸው መልካም ሆኖ አይሰማኝም” በማለት የተፈጠረውን አደጋ አሳሳቢነት ይገልጻሉ።

ተካልኝ (ዶ/ር) በርካታ ብሔር ብሔረሰብ ያለባቸው አገራትን ባህል፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት እንደሚያስተሳስራቸው በመጠቆም፣ የአሁኑ ሁኔታ “በኢትዮጵያ ያሉ ማኅበራዊ ድልድዮች በሆነ ዓይነት መንገድ ቀስ በቀስ እየተሰባበሩ ስለመምጣታቸው አመላካች ነው።”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ወደ መቀለ ባቀኑበት ጊዜ የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ “በሃይማኖት ጉዳይ እጃችንን አናስገባም ግን ደግሞ ሊያስከትለው የሚችለው መዘዝ አይመለከተንም ማለት አይደለም” ማለታቸውን የሚያነሱት ቄስ ዩናስ፣ የቀውሱ መዘዝ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ “ቀላል አይሆንም” ይላሉ።

ከሃይማኖት በተጨማሪ በፖለቲካ ዙሪያ ሁሉም አካላት ወደ መሃል ለመምጣት ነገሮችን ማመቻመች አለባቸው የሚሉት ፕሮፌሰር ቴሪ፣ “ሃይማኖት እና ብሔር የማንነት መገለጫዎች እና የግንኙነት መስመሮች ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳስረዋል።...ስለዚህ በሁለቱም ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል” ብለዋል።

ጣት መጠቋቆም ነገሩን ሊያባብስ ስለሚችል ከዚህ መቆጠብን የሚመክሩት ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ውይይት መኖር እንዳለበት በማንሳት “ሲኖዶሱ የሚይዘው አቋም እና የሚያሳየው ልበ ሰፊነት ትልቅ ሚና ይኖረዋል” ብለው ያስባሉ።

መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ቢባልም ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚመጡ መዘዞች ትልቅ ስለሚሆኑ፤ መንግሥት የገለልተኝነት ሚናውን ሳይተው ሁለቱን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አንስተዋል።

“ቤተ ክርስቲያን የፍቅር እና የሰላም ምሳሌ መሆን ስላለባት፣ በተለይ ሲኖዶሱ በጦርነቱ ወቅት በወሰደው አቋም በሙሉ ልብ ደጋግሞ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል። ተገቢውን ካሳም መክፈል ይኖርባታል። በጦርነቱ ወቅት ከአንደበታቸው ሊወጣ የማይገባ ነገር በመናገር ጥላቻን እና ጦርነትን በማቀጣጠል ተሳትፎ በነበራቸው አባቶች ላይም ተገቢው ቅጣት መጣል አለበት” የሚሉት ደግሞ ቄስ ዮናስ ናቸው።

“ምንም እንኳ በሕዝባቸው እና በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ የደረሰው በደል ከፍተኛ ቢሆንም፣ በትግራይ ሃይማኖታዊ አባቶችም በኩል ክርስቶስ በደሙ ይቅር እንዳለልን ይቅር ማለት አለባቸው። ወደ እርቅ እና ሰላም ሊመጡ ይገባል” ሲሉ መክረዋል።