ኢትዮጵያ አሁንም በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር በሯ ክፍት ነው - የውሃ እና ኢነርጂ ሚ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

የፎቶው ባለመብት, AMENSISA IFA/BBC
የኢትዮጵያ መንግሥት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታን አጠናቅቆ በዚህ ዓመት የመጨረሻ ቀናት በይፋ ለማስመረቅ እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰምቷል።
በተለይ አብዛኛውን የናይል ውሃ በብቸኝነት ስትጠቀም የነበረችው ግብፅ በግድቡ ግንባታ እና ውሃ ሙሌት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታ መቆየቷ ይታወቃል።
ባለፉት ዓመታትም ሱዳንን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ድርድር ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ ግድቡ አምስት ጊዜ በውሃ ተሞልቶ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ እየተዘጋጀ ነው።
ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ አሳሪ ስምምነት እንድትፈርም በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ኢትዮጵያ ግን ሳትቀበለው ቀርታ የደረጉተ ድርድሮች ያለ ውጤት ቀርተዋል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ብታጠናቅቅም አሁንም ለንግግር እና ለድርድር በሯ ክፍት መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ይህ ግዙፍ ግድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን፣ ይህም ለበርካታ የአገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲያዩ ዕድል እንደሚፈጥር ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ መንግሥት 46 በመቶ የሚሆነው የኤሌትሪክ የማያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገለፀዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት 54 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
"46 በመቶ ያህሉ አሁንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተጠቃሚ አይደለም። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህንን ቁጥር ለመቀነስ ነው እየሠራን ያለነው።"
ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2030 ቢያንስ 90 በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በአፍሪካ ግዙመሆኑ እየተነገረለት ያለው የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታው በአምሰት ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም 14 ዓመታትን ፈጅቷል።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ይህ ግድብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የተገነባው በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ ነው" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት ከአሜሪካ ድጋፍ ማግኘቷን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችው በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ ነው" ቢሉም አገራቸው መቼ እና በምን መልኩ ገንዘቡን እንደሰጠች ያሉት ነገር ግን የለም።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ይህ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ገንዘብ ነው የተገነባው" በማለት አገሪቱ ከየትኘውም ወገን የገንዘብ ድጋፍ ሳታገኝ በሕዝቧ እና በራሷ አቅም መገንባቷን በተመለከተ ሲነገር የቆየውን አረጋግጠዋል።
ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ግድቡን ለመገንባት ስለተገኘ ገንዘብ የሚሰጡ አስተያየቶችን በተመለከተ ሲናገሩም "ይህ ውሸት ነው" በማለት "በኢትዮጵያውያን ንፁህ ገንዘብ ገንብተን፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ለምረቃ የሚበቃው" ብለዋል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተገነባው ሕዝቡ ባወጣው ገንዘብ እና አገር ውስጥ ባለ ሃብት መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብቱን ያፈሰሰበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ለግድቡ ድጋፍ አድርገናል የሚለው አስተያየትን ትክክል ያልሆነ በማለት ውድቅ አድርገዋል።
የሕዳሴ ግድብ ምረቃ መቃረቡን ግብፅ "የዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ በምሥራቃዊ ናይል ተፋሰስ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን" እንደማትቀበል ለበርካታ አፍሪካ አገራት አሳውቃለች።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የናይል ተፋሰስ አገራት ከሆኑት ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኡጋንዳ፣ ከኬንያ እንዲሁም ከተፋሰሱ ውጪ ካሉት ከጂቡቲ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በተናጠል በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ግብፅ፣ ኢትዮጵያ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዲሁም አስተዳደርን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ምረቃው የሳምንታት ጊዜ በቀረበት ወቅት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AMENSISA IFA/BBC
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት በጀመረችበት ወቅት ግብፅ እና ሱዳን "የንግግሩ አካል ስለነበሩ ያውቁታል። እንዲያውቁት እስከተደረገ ድረስ ኢትዮጵያ ግድቡ ጉዳት እንደማያደርስ ለማስረዳት እና ለመነጋገር ዝግጁ ነች" ብለዋል።
በተደጋጋሚ የተደረጉ ውይይቶችን እና ድርድሮችን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድንም የግድቡን ግንባታ ገምግሞ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት እንደሌለ መናገሩን ገልጸዋል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ከላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት አንዷ ከሆነችው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ከሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ "105 ሚሊዮን ዜጎቻችን እና 10 ሚሊዮን የሚሆኑ በአገራችን ያሉ እንግዶቻችን በሕይወት የሚያቆየው ውሃ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማንፈቅድ ነው" ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አድርገው ነበር።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅምሩ እንዲሁም የውሃ ሙሌቶችን በጽኑ ያወገዙት አልሲሲ፤ አገራቸው በግድቡ የሥራ ሂደት ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራት እና በተናጠል በናይል ውሃ ላይ የሚካሄድ የትኛውንም ዓይነት ሥራ ግብፅ እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።
"ግብፅ በውሃ ደኅንነቷ ላይ የተደቀነን የኅልውና ስጋት ችላ ትለዋለች ብሎ የሚያስብ ማንኛውም አካል ተሳስቷል። የዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሕዝቦቻችንን የኅልውና ሃብቶች ለማስጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ አል ሲሲ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ምስክርነት ብቻ ሳይሆን የመርኅ ስምምነት በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል መፈረሙን አስታውሰዋል።
"ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር ትነጋገራለች ይላል። ይህ በግልጽ ተጽፎ ይገኛል። ስለዚህ ግድቡን መገንባት እንድናቆም ሳይሆን እየገነባን እንድንደራደር፣ እየገነባን መረጃ እንድንለዋወጥ፣ እየገነባን ሃሳቦችን እንድንለዋወጥ፣ እየገነባን ስጋት የሚኖር ከሆነ በጠረጴዛ ዙሪያ እንድንወያይ ነው።"
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ምንም ዓይነት ውጤት ሳያስገኙ የውሃ ሙሌቱ እና የግድቡ ግንባታ ወደ ፍጻሜው ደርሷል።
ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።
ድርድር ሁለቱም ወገኖች የሚያሸንፉበት ማለት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ "አንዱ ወገን ድርድር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማያውቅ ከሆነ ለመቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል" ያሉት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ጥቅሟን እና መብቷን በሚያስከበር ሁኔታ በድርድሩ ውስጥ ስትሳተፍ መቆያቷን አስታውሰዋል።
"እስካሁን ድረስ የሕዳሴውን ግድብ በሚመለከት የተደረጉ ድርድሮች ላይ ሁሉ ኢትዮጵያ ተሳትፋለች" ያሉት ሚኒስትሩ፣ "ወደፊትም በዚሁ አንቀጥላለን። አሁንም ለመደራደር ፈቃደኛ የሚሆን አካል ካለ እኛ ዝግጁ ነን" ብለዋል።
አክለውም "እንደ አለመታደል ሆኖ ግብፃውያን ናቸው ከድርድሩ የወጡት ወይም ከሁለት ዓመት በፊት ድርድር አንፈልግም ያሉት እነሱ ናቸው።"
ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ሲጠቅሱ፣ "ኢትዮጵያ እነርሱ የሚፈልጉትን የውሃ መጠን እንድትለቅ አስገድደው ለማስፈረም ነው። እኛ የአባይ ውሃ ለተፋሰሱ አገራት በሙሉ መሆኑን እናምናለን። እነርሱ ግን አሁንም በቅኝ ግዛት ውል ላይ የሙጥኝ ብለዋል። እርሱ ደግሞ የላይኛውን የተፋሰስ አገራት ከጨዋታ ውጪ አድርጎ መብቱን ለሱዳን እና ለግብፅ ጠቅልሎ የሚሰጥ ነው። ያ ደግሞ ኢ ፍትሐዊ ነው። ያንን ማንም ሊቀበል አይችልም።"
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና የአብዛኛውን የወንዙን ውሃ ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት አድርጋ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ትቃወማለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምታመነጨውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሐዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።















