የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተካሄደው መቶ በመቶ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ ነው - ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Grand Ethiopian Renaissance Dam

የምስሉ መግለጫ, የታላቁ ሕዳሴ ግድብ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ግዙፉ የሕዳሴ ግድብ መቶ በመቶ የተገነባው "ያለምንም የውጭ እርዳታም ሆነ ብድር በራስ አቅም"፣መሆኑን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ባሠራጨው መግለጫ ላይ መላው ኢትዮጵያውያን ንግድቡ ግንባታ ሂደት ውስጥ "በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት" መሳተፈቸውን ጠቅሷል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረጓን በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹ ሲሆን፣ ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ ግድቡ "በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ" የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከመንግሥት እና ከሕዝቡ በቀጥታ የተገኘ መሆኑ እና ከየትኛውም ወገን ድጋፍ እንደሌለ ሲነገር ቆይቷል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በተለያዩ አጋጣሚዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ መድረካቸው ላይ አሜሪካ አስተዋጽኦ ማድረጓን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ባለፈው አርብ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም. ዋይት ሐውስ ውስጥ ለሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተሮች የእራት ግብዣ ላይም ባደረጉት ንግግር አገራቸው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል።

ይህንን የፕዝዳንቱን ተደጋጋሚ አስተያየት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን ይፋዊ አስተያየት ለመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል።

አሁን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ግን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግንባታው ከተጀመረ አስራ አራት ዓመት የሆነው የግድቡ ግንባታ ወጪ ሙሉ ለሙሉ በአገሪቱ መሸፈኑን አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለግድቡ በ2017 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ድረስ ብቻ "በቦንድ ግዢ እና በስጦታ" ከአገር ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ከአገር ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 95 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ጠቅሷል።

__________

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለያዩ ጊዜያት ስለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተናገሩትን እዚህ በቪዲዮ ያገኛሉ

__________

በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ከአገር ውስጥ እና ውጪ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰበሰበው ገንዘብ 1.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ይህም ከዕቅዱ የ7 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክቷል።

ኢትዯጵያ ግድቡን መገንባት ከጀመረችበት ገዜ ጀምሮ ከአገር ውስጥ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ 20̏ ቢሊዮን ብር በላይ፣ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቧን አስታውቋል።

ይህም በአጠቃላይ እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም. ድረስ 23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ መዋሉን ገልጿል።

ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቁን ገልጾ፣ የቀረው "ሪቫን መቁረጥ" መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰኔ ወር መጨረሻ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የሕዳሴ ግድብ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመርያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ መናገራቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. ከየሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት ስለ ግብፅ እና ግድቡ በጠቀሱበት ወቅት "አሜሪካ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ይመስለኛል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ከኔቶው ዋና ፀሐፊ ጋር በነበራቸው ውይይት በሰጡት አስተያየት ግድቡ "ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው" የሚል የተሳሰተ ንግግር አድርገዋል።

በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ግብፅ "የሕዳሴ ግድብን ልታፈነዳ ትችላለች" የሚል አወዛጋቢ ንግግር የተናገሩት ትራምፕ፤ በአሁኑም ለግብፅ ወገንተኝነታቸውን በግልጽ ያንጸባረቀ አስተያየት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።

ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።

በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ከሰሞኑም ይህንኑ በመድገም አስጠንቅቃለች።

በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሮ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።