ትራምፕ የሕዳሴ ግድብ "የተገነባው በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ ነው" ሲሉ ለሦስተኛ ጊዜ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ "የተገነባው በአብዛኛው አሜሪካ ገንዘብ ነው" ሲሉ ለሦስተኛ ጊዜ ተናገሩ።
ትራምፕ ይህንን አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት በዋይት ሐውስ ለሪፐብሊካን ሴናተሮች የእራት ፕሮግራም ባደረጉበት ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም. ምሽት ነው።
በዓለም ላይ ያሉ ጦርነቶችን ሰላማዊ እልባት ለመስጠት አገራቸው እያደረገችው ያለውን ጥረት በማጉላት የተናገሩት ትራምፕ ግብፅ እና ኢትዮጵያ "በሕዳሴ ግድብ እየተጣሉ መሆኑን ታውቃላችሁ" ብለዋል።
በመቀጠልም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አገራቸው ለሕዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ መስጠቷን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ የተናገሩት ትራምፕ በሦስተኛው እና በአሁኑ ንግግራቸው ላይ ጠንከር ባለና አጽንኦት በመስጠት ነው የደገሙት።
"ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችው በአሜሪካ ገንዘብ ነው፤ በአብዛኛው" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ አገራቸው መቼ ገንዘቡን እንደሰጠች ወይም በምን መልኩ እንደሆነ ያሉት ነገር ግን የለም።
ትራምፕ ሐምሌ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. ከኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት ስለ ግብፅ እና ግድቡ በጠቀሱበት ወቅት "አላውቅም፤አሜሪካ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ይመስለኛል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተበጀተለት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተገነባው ሕዝቡ ባወጣው ገንዘብ እና አገር ውስጥ ባለ ሃብት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የትራምፕን ይህንን "ሕዳሴ የተገነባው በአሜሪካ ገንዘብ ነው" የሚለውን ንግግራቸውን አስመልክቶ በይፋ ትክክል እንዳልሆነ ካለመግለጽ በተጨማሪ ዝምታን መርጠዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በስም ያልጠቀሱት ትራምፕ "በዓለማችን ካሉ ትልልቅ ግድቦች አንዱ ነው። ነገር ግን አንድ ትንሽ ችግር አለው" ብለዋል።
ይህም "ወደ ናይል ወንዝ ብዙ ውሃ እንዳይገባ ይከለክላል፤ ይህ በጣም መጥፎ ነገር ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ከኔቶው ዋና ፀሐፊ ጋር በነበራቸው ውይይት በሰጡት አስተያየት ግድቡ "ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው" የሚል የተሳሰተ ንግግር አድርገዋል።
ትራምፕ ይህንን ይበሉ እንጂ ግብፅ በበኩሏ ግድቡ ውሃውን ይቀንሰዋል እንጂ "ይዘጋዋል" ወይም ናይልን ያደርቀዋል በሚል ክስ አቅርባ አታውቅም።
ግብፅ ትራምፕ እንደሚሉት "በናይል ወንዝ ውሃ" ስለሌላት ወይም ደርቆ ሳይሆነ ድርሻዬ የምትለው 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዳይቀንስ ነው እየጠየቀች ያለችው።
በግድቡ ላይ በሚያደርጉት ንግግር ለግብፅ ወገንተኛነታቸውን የሚያንጸባርቁት የአሜሪካው መሪ በዚህኛውም ንግራቸው "ግብፅ በዚህ ደስተኛ እንዳልሆነች ማሰብ ትችላላችሁ" ብለዋል።
ግብፅ በተደጋጋሚ የናይል ወንዝ የህልውናዬ መሠረት ነው የምትለውን አቋም ያንጸባረቁት ትራምፕ "እነሱ የኑሯቸው መሠረት የናይል ወንዝ ነው። ደማቸው፣ ልባቸው፤ ሁሉ ነገራቸው ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር ናይል ለግብፅ ሕይወት ነው የሚለውን አጽንኦት በመስጠት "በናይል ወንዝ ውሃ እንዲኖር እየሠራን ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
ይህንን ንግግራቸው ከግብፁ መሪ በኩል ከፍተኛ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን፣ "ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢትዮጵያን ግድብ በተመለከተ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያስጠብቅ ፍትሃዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያላቸውን ፍላጎት እንዲሁም ናይል ለግብፅ የሕይወት ምንጭ አድርገው ዕውቅና መስጠታቸውንም ግብፅ ታመሰግናለች" ሲሉ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
አሁን ለሴናተሮች ባደረጉት ንግግር ግድቡ ሲገነባ እየተከታተሉት እንደነበር የጠቀሱት ትራምፕ ፎቶዎች እና የሳተላይት መረጃዎች እና ሌሎችንም አገኝ ነበር ብለዋል።
"ይህንን ግዙፍ ግድብ እየተመለከትኩኝ ወደ ናይል ወንዝ የሚሄደውን ወንዝ ይዘጋዋል? አልኩኝ" ሲሉ መጠየቃቸውን ትራምፕ አውስተዋል።
አክለውም "ይህ መፈጠር አልነበረበትም። ያውም በአሜሪካ ገንዘብ ታግዞ፤ ሁሉ ነገር ትንሽ የእብደት ሥራ ነው" ሲሉ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ያሉትን የሕዳሴ ግድብ የናይልን ፍሰት ያቋርጠዋል የሚለውን አቋማቸውን ደግመዋል።
አክለውም "ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚፈታ ይመስለኛል" ሲሉ ምኑ እንደሚፈታ ሳይጠቅሱ አስተያየታቸውን ጠቅሰዋል።
ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ላይ ለግብፅ የሚወግኑት እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉት ከጋዛ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በመጀመሪያ ሳምንት በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሁኔታ እልባት ማበጀት የግብፅ እና የዮርዳኖስ ጉዳይ ነው የሚል አቋም ይዘዋል።
ፍልስጤማውያኑን ከጋዛ ለማስወጣት ያቀዱት ትራምፕ ግብፅ እና ዮርዳኖስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን በአገራቸው እንዲቀበሉ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደም የአረብ መንግሥታት ትራምፕ ላቀረቡት የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ አማራጭ የሆነውን ፍልስጤማውያን ባሉበት እንዲቆዩ ለሚያስችለው የግብፅን የ53 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ ድጋፍ አድርገዋል።
ማንኛውንም የፍልስጤም ሕዝብ የማፈናቀል ዕቅድ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ነው ሲሉ ሙሉ በሙሉ የአረብ መንግሥታቱ ውድቅ አድርገውታል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ተናግራለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብፅን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ከሰሞኑም ይህንኑ በመድገም አስጠንቅቃለች።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሮ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።















