ግብፅ እና ሱዳን የሕዳሴው ግድብ "ዘላቂ ስጋት" ደቅኖብናል አሉ

የፎቶው ባለመብት, MFAEgypt/fb
ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው እና ሊመረቅ ቀናት የቀሩት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይልተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል አሉ።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ አጠናቅቃ ለምረቃ እየተዘጋጀች ባለችብት ጊዜ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሮች በካይሮ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ነው ስጋታቸውን የገለጹት።
በሚኒስትሮቹ ረቡዕ ነሐሴ 28/ 2017 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ ግድቡ "በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ መረጋጋት ላይ ቀጣይነት ያለው ስጋት" መደቀኑን አመልክተዋል።
የሁለቱ አገራት ሚኒስትሮች በካይሮ ባደረጉት በዚህ ስብሰባ ላይ ግድቡ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እና በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ ለመሙላት የወሰደችው የተናጠል እርምጃ የተቃወሙት አገራቱ የውሃ ደኅንነታቸው ጉዳይ አንድ እና የማይነጣጠል መሆኑን በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
አክለውም "ኢትዮጵያ ትብብርን ዳግም ለማጠናከር በምሥራቃዊ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ መቀየር አለባት" ብለዋል።
ግብፅ እና ሱዳን በዚህ መግለጫቸው ሌሎች የናይል ተፋሰስ አገራትን ተሳትፎ ውድቅ አድርገው ጉዳዩ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና ሱዳን መካከል ብቻ መታየት እንዳለበት አስታውቀዋል።
በ2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ በሦስቱ አገራት መካከል የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ እየተካሄዱ የነበሩ ድርድሮች ውጤት ሳያመጡ ተቋርጠዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር አሁንም ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።
ነገር ግን ግብፅ እና ሱዳን የግድቡን ውሃ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በሚመለከት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነትን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ይፈልጋሉ።
በኢትዮጵያ በኩል ግን ይህ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እና ሁሉንም የተፋሰሱ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት እንዲደረስ ትፈልጋለች።
ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ዓመታት የተቆጠሩት ግድቡ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በካይሮ በተደረገው የሁለትዮሽ የምክክር መድረክ ላይ የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እንዲሁም የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ሀኒ ስዌይለም እንዲሁም የሱዳኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦመር ሲዲቅ እና የግብርና እና መስኖ ሚኒስትሩ ኢስማት ቁረሺ ተገኝተዋል።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ያለ አሳሪ ስምምነት በተናጠል የግድቡን ውሃ ሙሌት ማድረግ እንደሌለባት በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።
ግብፅ ግድቡ የውሃ መጠኑን ይቀንሳል ስትል ስጋቷን በተደጋጋሚ የገለፀች ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር የአገራቸው የውሃ ድርሻ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማይፈቅዱ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክቶ በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈው ውይይታቸው ላይ ወደ ግብፅ የሚፈስሰው የውሃ መጠን አለመቀነሱን እና ከተለመደው ጊዜ የተሻለ ውሃ በግብፅ ግድብ ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
አክለውም የሕዳሴ ግድብ መገደብ የአባይ ውሃን ይቀንሰዋል በሚል የዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡ አገራት በሚቀጥሉት ጊዜያት ውሃቸው አለመቀነሱን ሲያዩ ውጥረቱን ያረግበዋል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
የግብፅ እና የሱዳን ሚኒስትሮች ረቡዕ ዕለት ባወጡት መግለጫ የሁለቱን አገራት የውሃ ደኅንነት አስፈላጊነት ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱ አገራት በውሃው ላይ ያላቸውን ሙሉ መብት ለመከላከል እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው ስምምነት እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጋራ ፍላጎት መርሆችን እና እኩል መብቶችን ባከበረ መልኩ በጋራ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ሁለቱም አገራት የውሃ ደኅንነት አንድ እና የማይነጣጠል መሆኑን የገለፁ ሲሆን፣ በምሥራቅ ናይል ተፋሰስ ላይ የውሃ ፍላጎታቸውን የሚጎዳ ማንኛውም የተናጠል ውሳኔን እንደሚቃወሙ ገልፀዋል።
በአፍሪካ ግዙፍ መሆኑ እየተነገረለት ያለው የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታው የተጠናቀቀው ከ14 ዓመታት በኋላ ነው።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ይህ ግድብ በተጀመረበት ወቅት ግብፅ እና ሱዳን "የንግግሩ አካል ነበሩ" ያሉት የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ፣ አሁንም ቢሆን "ኢትዮጵያ ግድቡ ጉዳት እንደማያደርስ ለማስረዳት እና ለመነጋገር ዝግጁ ነች" ብለዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ተናግራለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብፅን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስትገልጽ ቆይታለች።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብፅ ስታስጠነቅቅ ብትቆይም ግድቡ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በውሃ ተሞልቷል።















