የተቃዋሚ ፓርቲ መሪውን መታሰር ተከትሎ በሴኔጋል ከፍተኛ አመጽ ተቀሰቀሰ

ፖሊሶች በሴኔጋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት የሴኔጋል ፖሊስ ዋነኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኛን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች ለሶስተኛ ቀን ቀጥሏል።

ሰልፈኞቹ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠሉ ሲሆን ከፖሊስም ጋር ተጋጭተዋል ተብሏል።

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት እስካሁን አራት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኦስማን ሶንኮ አርብ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ሰላም በማደፍረስ ክስ ቀርቦበታል። በተጨማሪም የመድፈር ክስ ተመስርቶበታል።

ነገር ግን ኦስማን ሶንኮ "ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም የሚቀርቡትም ክሶች ፖለቲካዊ ናቸው" ብሏል።

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አንትዋን ፌሊክስ አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ ወደቀደመው ሰላም ለመመለስ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ መታሰቡን ገልጸዋል።

በቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ '' ኦስማን ሶንኮ አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል'' ሲሉ ከሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተቃዋሚ ሰልፈኞችና ፖሊስ አላስፈላጊ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ያሳሰቡ ሲሆን መንግስትም ነገሮችን ለማረጋጋት የቤት ስራውን እንዲሰራ ጥያቄ አቅርበዋል።

አርብ ዕለት ፖሊስ የኦስማን ሶንኮ ደጋፊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ የተኮሰ ሲሆን ሰልፈኞቹ ደግሞ በዋና ከተማዋ ዳካር መንገዶችን በመዝጋት መሪያቸው እንዲለቀቅ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።

ፖሊስ በበኩሉ በወጣት የኦስማን ሶንኮ ደጋፊዎች የሚያዘወትሩትን የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴዎች በመከልከል በዋና ዋና መንገዶች ላይ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጓል። ኤኤፍፒ እንደዘገበው በዳካር የሚገኝ አንድ ሱፐርማርኬት አርብ ዕለት ተዘርፏል።

''በዚች አገር ውስጥ እየሆነ ያለውና እኛ የምንኖርበት ሁኔታ በጣም አስገራሚ ነው፤ በጣም አሳፋሪ ነው'' ብሏል አንድ ሰልፈኛ ከሬውተርስ የዜና ወኪል ጋር በነበረው ቆይታ።

የተቃውሞ ሰልፎቹን የሚዘግቡ ሁለት የግል የቴሊቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ ለ72 ሰአታት እንዲዘጉ መንግስት ወስኗል። ሀሙስ ዕለት ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች መታገዳቸውን በኢንተርኔት ላይ የሚሰራው ኔትብሎክስ አስታውቋል።

የ46 ዓመቱ ፖለቲከኛ ኦስማን ሶንኮ ባሳለፍነው ወር ላይ ነበር በውበት ሳሎን ውስጥ በምትሰራ ሴት የመድፈር ክስ የቀረበበት።

በዚህ ምክንያት ሲደረግ የነበረውን ምርመራ ተከትሎ ረቡዕ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በወቅቱም በርካታ ደጋፊዎቹ አብረውት ሄደዋል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለመማዋል የተገደድኩት ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር ብሏል።

ፖለቲከኛው እንደሚለው የቀረቡበት ክሶች በሙሉ ሆን ተብለው የተቀነባበሩ እንደሆኑና በአውሮፓውያኑ 2024 በሚካሄደው ምርጫ ተቀናቃኝ እንዳይኖር ለማድረግ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የሚሰሩት ስራ ነው ሲል ከሷል።

ሌሎች ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ደግሞ ባሳለፍነው ዓመት ክስ ቀርቦባቸው ከምርጫው እንዲገለሉ ተደርጓል።

የወቅቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የአገሪቱን ሕገመንግስት በመቀየር ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር እንዲያስችላቸው ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆነ እየተዘገበ ነው።