የጣልያኑ መዝገበ ቃላት ሴት ለሚለው የሰጠውን 'አፀያፊ' ትርጉም እንዲቀይር ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
100 የሚሆኑ ስመ- ጥር ጣልያናውያን ትሪካኒ የተባለው የጣልያን መዝገበ ቃላት ሴት በሚል ያስቀመጠውን ትርጓሜ እንዲቀይር ፊርማ አሰባስበዋል።
ዘመቻውን የሚያራምዱ ሰዎች መዝገበ ቃላቱ ሴት የሚለውን አፀያፊ በሆነ ሁኔታ ተርጉሞታል ይላሉ።
በመዝገበ ቃላቱ ሴት ለሚለው ቃል ተመሳሳይ ተብሎ የሰፈረው ፑታና (ሸርሙጣ ወይም የወሲብ ንግድ ተዳዳሪ ) በሚል ሲሆን ፤ለሴት ተመሳሳይ ትርጉም ነው ተብሎ ከሰፈረው ዘርፍ ሊወገድ ይገባል ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ትርጉሞች"አፀያፊ፣ ፆተኛ፣ ሴቶችን በወሲብ አይን ብቻ የሚመለከቱና የበታችነት ቦታ የሰጡ ናቸው" ብሏል።
በበይነ መረብ መዝገበ ቃላቶችን በማተም የቁንጮነትን ስፍራ የተቆናጠጠው ትሪካኒ በበኩሉ ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን ከዚህ ቀደም ግን ደግፎ ተከራክሮ ነበር።
ደብዳቤውን ከፈረሙት መካከል የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን መብት የሚከራከሩት ፖለቲከኛ ኢማ ባታግሊያ፣ ፖለቲከኛ ላውራ ቦልድሪኒና የጣልያን ባንክ ዋና ዳይሬክተር አሌሳንድላ ፔራዛሊና ይገኙበታል።
የዘመቻው ፅሁፍ የተፃፈው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ማሪያ ቢትሪስ ጂዮቫናርዲ ሲሆን ከዚህ ቀደምም የኦክስፎርዱ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ለሴት ተመሳሳይ ተብለው የሰፈሩት ቃላት ወፍና ሌሎች ቃላቶችን እንዲያስወግዱ ዘመቻ ከከፈቱት መከካል አንዷ ናቸው።
ተመሳሳይ የተቃውሞ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈረማቸውን ተከትሎ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ትርጉሙን ለማሻሻል ተገዷል።
በተጨማሪ በትሪካኒ መዝገበ ቃላት የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎችን ትርጓሜ በተመለከተ 30 ቃላትን የተጠቀመ ሲሆን ይህም ከኦክስፎርዱ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት የከፋ እንደሆነ ቢትሪስ ጂዮቫናርዲ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ነገር ግን ወንድ ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጓሜ አዎንታዊ ሲሆን ለምሳሌም የንግድ ሰው የሚል ነው።
"ቋንቋዎች የምንኖርበት አለም ላይ ተፅእኖ ያሳርፋሉ። ሴቶች በምን መንገድ ሊታዩ እንደሚችሉም ጠቋሚ ናቸው" በማለትም በደብዳቤው ላይ አስፍረዋል።
"መዝገበ ቃላት፣ ኢንሳይክሎፒዲያና ሌሎች ከቋንቋዎች ጋር የተገናኙ መፃህፍት ለበርካታ ተማሪዎች እንደ ተጨማሪ መማሪያ የሚያገለግሉ የትምህርት መሳሪያዎች ናቸው። የትሪካኒን መዝገበ ቃላት በትምህርት ቤቶች፣ ቤተ መፃህፍትና በቤቶቻችን የምንጠቀምባቸው ናቸው" ይላሉ።
"የመዝገበ ቃላቱ ትርጉም መቀየር በየቀኑ የሚደርሰውን ፆተኛነት አያስቀረውም። ነገር ግን ሴቶች በማህበረሰቡ ላይ ያላቸውን ትክክለኛ ሚና እንዲሁም አሁን ባለንበት ማህበረሰብ ሊኖራቸው የሚችለውን ራዕይ ሊያንፀባርቅ ይችላል" ብለዋል።
በህዳር ወር ላይ ትሪካኒ ባወጣው ፅሁፍ መዝገበ "የቃላቱ ትርጉም በሞራል ፍርድ ወይም በጭፍንነት ተሞልቶ አይደለም"፤ ነገር ግን
"ማህበረሰቡና ባህሉ አንዳንድ ቃላትን በአሉታዊ መልኩ ይገልፃቸዋል። መዝገበ ቃላትም ይህንን አገላለፅ አልመዘግብም አይልም" ብሏል መግለጫው












