ወርቅ ተሸላሚው ፈንጂ አነፍናፊ አይጥ ጡረታ ወጣ

ወርቅ ተሸላሚው ፈንጂ አነፍናፊ አይጥ

የፎቶው ባለመብት, APOPO

የምስሉ መግለጫ, ወርቅ ተሸላሚው ፈንጂ አነፍናፊ አይጥ

በጀግንነቱ የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለመው ማጋዋ የተባለው አይጥ ፈንጂዎችን ከማንነፍ ሥራው ጡረታ ወጣ።

አይጡ በአምስት ዓመት የሥራ ዘመኑ በካምቦዲያ 71 ፈንጂዎችን እና በደርዘን የሚቆጠሩ ያልፈነዱ ተቀጣጣይ ቁሶችን አግኝቷል።

አስተዳዳሪው ማሌን የሰባት ዓመቱ ግዙፍ አፍሪካዊ አይጥ የእርጅና ዕድሜው በመድረሱ "እየቀዘቀዘ በመሆኑ ፍላጎቱን ማክበር" እንደምትፈልግ ተናግራለች።

በደቡብ ምስራቅ እስያዋ ሃገር እስከ ስድስት ሚሊዮን የሚደርሱ ፈንጂዎች አሉ ተብሎ ይገመታል።

ማጋዋ በቤልጂየም በተመዘገበው እና መቀመጫውን ታንዛቢያ ባደረገ አፖፖ በተሰኘ ድርጅት ሰልጥኗል።

እንስሳቱ የአንድ ዓመት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል።

አፖፖ ባለፈው ሳምንት እንዳለው አዲስ የወጣት አይጥ ቡድን በካምቦዲያ የፈንጂ ማዕከል በከፍተኛ ውጤት አልፈዋል ተብሏል።

ቡድኑ እንዳስታወቀው ማጋዋ አዲሶቹን ምልምሎች "ለማገዝ" ለጥቂት ተጨማሪ ሳምንታት በሥራው ይቆያል።

"የማጋዋ አፈፃፀም የማይደረስበት ነው። ከእሱ ጋር በመሥራቴ ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል ማሌን።

"ትንሽ ቢሆንም ግን በጣም አስፈላጊ የሆነውን ደህንነቱ የተጠበቀ መሬት በተቻለ ፍጥነት ለህዝባችን እንድንመልስ በማስቻል ብዙ ሰዎችን ለማዳን አግዞናል"

ባለፈው መስከረም መጋዋ "ለሕይወት አድን ሥራው" የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል። 77 ዓመት ካስቆጠረው የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ሜዳሊያው የተሰጠው የመጀመሪያ አይጥ ነው።

ክብደቱ 1.2 ኪሎ ግራም ሲሆን 70 ሴ.ሜትር ርዝመት አለው። ይህ ከሌሎቹ በርካታ የአይጥ ዝርያዎች እጅግ የላቀ ቢያደርገውም መጋዋ አነስተኛ ክብደት ስላለው ፈንጂዎች ላይ ቢራመድ የማፈንዳት ክብደት የለውም።

አይጦቹ በፈንጂዎቹ ውስጥ ያለው የኬሚካል ውህድን ለመለየት የሰለጠኑ ናቸው። ይህም የቆሻሻ ብረትን ቁርጥራጦችን ችላ በማለት ፈንጂዎችን በፍጥነት መፈለግ ያስችላቸዋል። ፈንጂ ሲያገኙ የተቀበረበትን ቦታ በመቧጨር ለሥራ ባልደረቦቻቸው ምልክት ይሰጣሉ።

ማጋዋ በ 20 ደቂቃ ውስጥ የሜዳ ቴኒስ ስፋት ያለው መስክ የማካለል ችሎታ አለው። እንደ አፖፖ ከሆነ ይህን ያህል ቦታ በፈንጂ አሳሽ ግለሰብ ለማካለል ከአንድ እስከ አራት ቀናት ሊጠይቅ ይችላል።