ፑቲን አሜሪካ የካፒቶል ሂል አመጸኞችን የያዘችበትን መንገድ ተቹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ በካፒቶል አመጸኞችን የያዘችበትን መንገድ ባለሁለት መልክ ያደርጋታል ሲሉ ከሰሱ።
ፑቲን በአመጹ የተሳተፉ አሜሪካዊያንን ላይ "የፖለቲካ" ክስ በመመሠረት በባህር ማዶ የሚደረጉ የጸረ-መንግሥት ተቃውሞዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ መውቀሷ ስህተት ነው ብለዋል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በሁለቱ አሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሏል።
ዓርብ ዕለት በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ የተገኙት ፑቲን ከባይደን ጋር በሚኖራቸው የሁለትዮሽ ውይይት ወቅት አዲስ ለውጥ እንደማይጠብቁ ገልጸዋል።
በቅርቡ በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ የሳይበር ጥቃቶች የደረሱት ከሩስያ ነው የሚለውን ሃሳብ ውድቅ በማድረግ ሞስኮ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች የሚሉ አስተያየቶችንም አጣጥለዋል።
ፑቲን የሞስኮ አጋር በሆነችው ቤላሩስ በጸረ-መንግስት ተቃውሞዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አሜሪካ በማውገዟ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል። የዩኤስ ካፒቶል አመጽ ተሳታፊዎች በፍትሐዊ መንገድ እየተስተናገዱ አለመሆኑን በመግለጽ ፑቲን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
"እነሱ ዘራፊዎች እና የሁከት ሰዎች ብቻ አይደሉም" ሲሉ ፑቲን ጥር 6 ኮንግረሱን በመውረር እና የባለፈው ህዳር ምርጫ አሸናፊውን ሹመት እንዳይጸድቅ በጊዜያዊነት ስላገዱት ሰዎች ተናግረዋል። "ሰዎቹ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ይዘው ነው የወጡት" ብለዋል።
የመድረኩ አወያይ ፑቲን ስለ ካፒቶል አመጽ በሰጡት አስተያየት ከአሜሪካ ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ሊታገዱ እንደሚችሉ ሲገልጽ የሩሲያው መሪ "ሌላ ቦታ ስለመታገድ ምንም አልጨነቅም" በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ተከትሎ የመድረኩ ተሳተፊዎች በጭብጨባ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የካፒቶል አመጽ ተሳታፊዎች በአሜሪካ መንግሥት "ተከሰዋል" ብለዋል።
በሁከትና ብጥብጡ 500 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን አብዛኛዎቹ በተከለከለ ህንፃ ወይም ግቢ ውስጥ በመግባት ወይም በመቆየት ነው የተከሰሱት። ብዙዎች ለፍርድ እስኪቀርቡ የተለቀቁ ሲሆን የተወሰኑት ግን በእስር ይገኛሉ።
ፑቲን የታሰሩትን የተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኔን ጨምሮ ለጸረ-ክሬምሊን ሰልፎች የሩሲያ ባለሥልጣናት የሰጡትን ምላሽ ትችት ያቀረቡትን ምዕራባውያንንም ገስጸዋል።
ፑቲን ከባይደን ጋር ስለሚያደርጉት ውይይት ምን አሉ?
የሩሲያው መሪ አስተያየቶች ሰኔ 16 ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚገናኙበት ውይይት በፊት የተደረገ ነው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት አሁን ካለበት "እጅግ ዝቅተኛ" ደረጃ ውይይቱ ምንም አይነት ማሻሻያ እንደማያደርግ ፑቲን ጠቁመዋል።
የሩሲያው መሪ "እኛ ከአሜሪካ ጋር ምንም ጉዳይ የለንም፣ እነሱ ግን ከእኛ ጉዳይ አላቸው" ሲሉም ተደምጠዋል።
ፑቲን ሌላስ ምን አስተባበሉ?
ፑቲን የሩሲያ መረጃ በርባሪዎች ባለፈው ወር በዩኤስ ነዳጅ ማስተላለፊ ቱቦዎች ላይ እና ባለፈው ሳምንት ደግሞ በስጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ላይ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገዋል፡፡
"ስለ ሥጋ ማቀነባበሪያው አንድ ነገር ሰምቻለሁ። በጣም የማይረባ ነው። ሁላችንም አስቂኝ እንደሆነ ብቻ ተረድተናል" ብለዋል።
አክለውም "ማስተላለፊያ ቱቦ? እሱም የማይረባ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡












