ዩናይትድ አየር መንገድ ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን አውሮፕላኖች ወደ ሥራ አስገባለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, United/Boom
ዩናይትድ የተሰኘው የአሜሪካው አየር አየር መንገድ እአአ 2029 ላይ 15 ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን አውሮፕላኖች ወደ አቪዬሽኑ የማምጣት እቅድ አለኝ አለ።
ከዚህ ቀደም የፈረንሳይ እና ብሪቲሽ አየር መንገዶች ኮንኮርድ የተሰኘውን ከፍተኛ ፍጥነት ያላውን አውሮፕላን መንገደኞቻቸውን ለማጓጓዝ ይጠቀሙበት ነበር።
ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት አየር መንገዶች እአአ 2003 ላይ ኮንኮርድን መጠቀም አቁመዋል።
ዩናይትድ አየር መንገድ ወደ አየር እመልሳቸዋለሁ የሚላቸውን ባለ ከፍተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖች የሚያመርተው መቀመጫውን ዴንቨር ያደረገው ቡም የተሰኘ ኩባንያ ነው።
አየር መንገዱ ባለ ከፍተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖችን ወደ አገልግሎት የማመጣው ደህንነታቸው ሲረጋገጥ ነው ብሏል።
ከፍተኛ ፍጥነት ያለው በረራ ማለት ምን ማለት ነው?
አንድ በረራ ከፍተኛ ፍጥነት አለው የሚባለው አውሮፕላኑ ከድምጽ ፍጥነት በላይ ሲበር ማለት ነው። ይህ ማለት ከባህር ወለል በላይ 60ሺህ ጫማ ላይ በሰዓት 1ሺህ 60 ኪ.ሜትር መብረር ማለት ነው።
የተለመዱት የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በሰዓት 900 ኪ.ሜትር ይበራሉ። ዩናይትድ አየር መንገድ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ያቀደው ባለ ከፍተኛ ፍጥነት አውሮፕላን ግን በሰዓት 1ሺህ 800 ኪ.ሜትር በላይ ይበራል።
ይህ ማለት ከኒው ዮርክ - ለንደን ለመብረር የሚወስደውን ጊዜ በግማሽ ያሳጥራል ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮንኮርድ አውሮፕላን እአአ 1976 ላይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀል ከዚህም የላቀ ፍጥነት ነበረው። ኮንኮርድ በሰዓት 1ሺህ350 ኪ.ሜትር ይበር ነበር።
ኮንኮርድ ከአገልግሎት ውጪ የሆነው በሚያወጣው ከፍተኛ ድምጽ እና በሚወስደው ከፍተኛ የነዳጅ መጠን ነበር። አሁንም ቢሆን ባለ ከፍተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖች የድምጽ እና በከባቢያዊ አየር ንብረት ላይ የሚያደርሱት ብክለት ኢንደስትሪውን ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍተና ይሆንባቸዋል እየተባ ነው።
ቡም የተሰኘው ኩባንያ ለኢንዱስትሪው የሚያቀርባቸው ባለከፍተኛ ፍጥነት አውሮፕላኖች በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ካሉ አውሮፕላኖች የበለጠ የድምጽ ብክለት አያስከትሉም እያላ ነው።
ይህ አውሮፕላን ወደ አገልግሎት ሲገባ፤ በአውሮፕላኑ ለመሳፈር የሚጠየቀው ዋጋ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል። ብሪቲሽ ኤየር ዌይስ በኮንኮርድ ለመሳፈር ያስከፍል የነበረው በሌሎች አውሮፕላኖች ለቢዝነስ ክላስ ከሚጠየቀው በላይ ነበር።
ቡም ኩባንያ ግን በአሁኑ ገበያ ባለጸጎች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው በዚህ አውሮፕላን የመብረር ፍላጎት እንዳላቸው አምናለሁ ይላል።












