'የሺዎች እናት' አበበች ጎበና ምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

የፎቶው ባለመብት, AGOHELMA
በበጎ ሥራዎቻቸው እውቅናን ያተረፉት እና 'የአፍሪካዋ ማዘር ትሬዛ' በሚል ስያሜ የሚታወቁት የክብር ዶክተር አበበች ጎበና በኮቪድ-19 መያዛቸውን ተከትሎ በሕክምና ላይ ይገኛሉ።
በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሕይወታቸው ማለፉ መዘገቡን ተከትሎ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሕልፈተ ሕይወታቸውን ዜና ሲቀባበሉት ነበር።
ይሁን እንጂ ቢቢሲ የክብር ዶክተር አበበች ጎበና በጳውሎስ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ እና የጤና መሻሻል እያሳዩ እንደሚገኙ ማረጋገጥ ችሏል።
አበበች ጎበና የመሰረቱት አበበች ጎበና የሕጻናት ክብካቤ ልማት ማኅበር በፌስቡክ ገጹ ላይ የክብር ዶክተር አበበች ጤና መሻሻል ማሳየቱን አስታውቋል።
"ለእናታችን ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና (እዳዬ) ህክምና እየተደረገላችው ነው። አሁን ወደ ጠዋት አከባቢ ትንሽ ምግብ ቀምሰዋል" ሲል ማኅበሩ አርብ ጠዋት በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ማኅበሩ ጨምሮም ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ከማጋራት እንዲቆጠቡ እና ትክክለኛውን መረጃ ከማኅበሩ ገጽ ላይ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁሟል።
የማኅበሩ ኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆነው ይትባረክ ተካልኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ የክብር ዶክተር አበበች በሆስፒታል እየተደረገላቸው ባለው ሕክምና የጤና መሻሻል አሳይተዋል።

የክብር ዶክተር አበበች ጎበና ማን ናቸው?
አበበች የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ሰላሌ አካባቢ በ1938 ዓ.ም. ነበር። ወላጅ አባታቸው በጣሊያን ጦርነት ወቅት መገደላቸውን ይናገራል።
በ10 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ያለ ፍላጎታቸው ለትዳር ቢሰጧቸውም አበበች ግን ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ ሸሽተዋል።
ያሳደጓቸው ልጆች 'እዳዬ' ብለው ይጠሯቸዋል። ይህ ስም ዛሬ የሚሠሩትን እንደሚገልጽ እምነታቸው ነው።
በ1970ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ ተከስቶ በተለይ በወሎ በርካቶች በረሃብ ሕይወታቸውን ባጡበት ወቅት የክብር ዶክተር አበበች ለጸሎት ወደ ግሸን ማርያም ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ።
ከጸሎታቸው ሲመለሱ በረሃብ ከሞተች እናት አጠገበ የተቀመጠች ልጅ አይተው ትተው ማለፍ ስላልቻሉ፤ በሚሥጥር ታዳጊዋን ይዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
በዚህ መልኩ በጀመሩት ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ አበበች የሚያሳድጓቸው ልጆች ቁጥር 21 ደረሰ።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ተጋላጭ ለሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ድጋፍ መደረጉን አበበች ጎበና የመሰረቱት አበበች ጎበና ሕጻናት ክብካቤ ልማት ማኅበር ይገልጻል።
ለዚህ መልካም ተግባራቸው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአበበች ጎበና የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መስጠቱ ይታወሳል።












