ትራምፕ ከፌስቡክ እና ኢንስታግራም ለሁለት ዓመታት ታገዱ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፌስቡክ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾች ለሁለት ዓመታት አገደ።

በአሜሪካ ካፒቶል አመጽ ዙሪያ ባሰፈሯቸው ጽሑፎች ምክንያት በጥር ወር ከሁለቱም ገጾች ላልተወሰነ ጊዜ ታግደው ነበር። ባለፈው ወር የፌስቡክ ተቆጣጣሪ ቦርድ የጊዜ ገደብ ያልተቀመጠለትን ቅጣት ተችቷል።

ፌስቡክ የትራምፕ ድርጊቶች የማሕበራዊ ሚዲያው አጠቃቀም "ደንቦቻችንን እጅጉን የጣሱ ናቸው" ብሏል።

ግዙፍ የማህበራዊ ሚዲያ ፖለቲከኞችን ከአሁን በኋላ በአሳሳች አስተያየታቸው ወይም ተሳዳቢ ይዘት ያላቸውን ይዘቶች እንደማይቀበል ገልጿል።

የትራምፕ የመጀመሪያው እገዳው ከተላለፈበት ጥር 7 ጀምሮ የፀና መሆኑን ፌስቡክ አስታውቋል።

ትራምፕ ምን ምላሽ ሰጡ?

ዶናልድ ትራምፕ ባወጡት መግለጫ "የፌስቡክ ውሳኔ 75 ሚሊዮን ሰዎችን ጨምሮ ለመረጡን ብዙ ሰዎች ስድብ ነው ..."

"በዚህ ሳንሱር እና ማፈን እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በመጨረሻም እኛ እናሸንፋለን። ሀገራችን ከእንግዲህ ይህን በደል መሸከም አትችልም!" ብለዋል።

ትራምፕ የሁለት ዓመት እገዳውን አስመልክቶ ለሁለተኛ ጊዜ በሰጡት መግለጫ በፌስቡክ መስራች ላይ ትችት ሰንዝረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት "በሚቀጥለው ጊዜ በኋይት [ስገባ]በእሱ ጥያቄ ከማርክ ዙከንበርግ እና ባለቤቱ ጋር የእራት ግብዣ ብሎ ነገር አይኖርም። ሁሉም ነገር ሥራ ይሆናል!" ብለዋል።

የፌስቡክ ውሳኔ ትራምፕ ከ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት ወደ መድረኩ እንዲመለሱ ያስችላቸዋል።

በወር ከሁለት ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ካሉት ፌስቡክ በተጨማሪ ትራምፕ በጥር ወር ካፒቶል ሂል ረብሻ ምክንያት ከትዊተር፣ ዩቲዩብ፣ ስናፕቻት፣ ትዊች እና ከሌሎች ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ታግደዋል።

ባለፈው ወር የሪፐብሊን ፓርቲ አባል እና የትራምፕ አጋር የሆኑት የፍሎሪዳ ሃገረ ገዥ ሮን ዴሳንቲስ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፖለቲከኞችን ካገዱ እንዲቀጡ የሚያዘው ሕግ ላይ ፈርመዋል።