ለሩሲያ ሲዋጋ በዩክሬን ጦር ሜዳ የተገደለው ዛምቢያዊ ቤተሰብ ሐዘን

ሌሚካኒ ኒሬንዳ

የፎቶው ባለመብት, Zambians in Moscow/ Facebook

ለሩሲያ ሲዋጋ በዩክሬን ጦር ሜዳ የተገደለው የዛምቢያዊ ተማሪ ሐዘን የቤተሰቡን ልብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሰበረ ታላቅ እህቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከሞቱ አሟሟቱ እንዲሉ ለቤተሰቡም የእግር እሳት የሆነባቸው ወጣቱ በባዕድ አገር በግፍ እንዴት ተገደለ? የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

ሌሚካኒ ኒሬንዳ በሩሲያ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

ነገር ግን ተፈትቶ ዩክሬን ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ለመሳተፍ ወደ ግንባር ዘመተ።

“ቤተሰቡ ሳይነገረው እንዴት ወደ ጦር ሜዳ እንደዘመተ ማወቅ እንፈልጋለን። ተገዶ ነው?” ስትል ሙዛንጋሉ ኒሬንዳ ትጠይቃለች።

ቤተሰቡ በወንድሟ ሞት ልባቸው መሰበር ብቻ ሳይሆን “ልጃችንን ነጥቀውናል” ይላሉ።

የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስታንሊ ካኩቦ ሰኞ ኅዳር 5/2015 ዓ. ም. በሞስኮ ኢንጂነሪንግ ፊዚክስ ተቋም ተማሪ የነበረው ኒሬንዳ ከአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ጋር በተያያዘ የዘጠኝ ዓመት እስራት ተፈርዶበት እንደነበር አስታውቋል።

ተማሪው በጦር ሜዳ የተገደለው መስከረም ላይ ቢሆንም፣ የሩሲያ ባለሥልጣናት ለዛምቢያ ሞቱን ያሳወቁት በቅርቡ እንደሆነ አስረድተዋል።

ካኩቦ እንደተናገሩት ዛምቢያ የተማሪውን አሟሟት በተመለከተ እንዴት ወደ ዩክሬን እንደተላከ ሩሲያ መልስ ትስጠኝ ስትል ጠይቃለች።

ዜናው አብዛኞቹን ዛምቢያውያን ያስደነገጠ ሲሆን፣ በተጨማሪም ተማሪው ወደ ዩክሬን እንዴት ዘመተ? የሚለውን ጉዳይ ለማስረዳት መንግሥት ተጨማሪ መረጃ አለማካፈሉ በርካቶችን አበሳጭቷል።

እንደ ሙዛንጋሉ ገለጻ ወንድሟ ወደ ሩሲያ የተጓዘው በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።

ሁለቱ አገራት ባላቸው ስምምነት መሠረት የኒውክሌር ምኅንድስና ትምህርትን በመንግሥት ስፖንሰርሺፕ ለመማር ነበር ወደ ሩሲያ ያቀናቸው።

“እኛ የማናውቀው ብዙ ነገር አለ። የዛምቢያ መንግሥት ለምን ወደ ጦርነት እንደተላከ ለምን አላወቀም ነበር?” ስትል ታላቅ እህቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ወደ ጦር ግንባር የወሰዱት ሰዎች ለቤተሰቡ ግድ አልሰጣቸው። ሕይወቱም ለእነሱ ምንም አልነበረም። ተጠቅመው እንደ ቆሻሻ ጥለውታል” ብላለች።

የአደንዛዥ ዕፅ ክስ

ሌሚካኑ ኒሬንዳ በአውሮፓውያኑ 2020 አደንዛዥ ዕፅ ከያዘ እሽግ ጋር በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በትርፍ ሰዓቱ በእቃ አመላላሽነት ይሠራ እንደነበር እህቱ ተናግራለች።

“ሊያደርሰው በነበረ እሽግ ውስጥ ምን እንዳለ አላወቀም ብለን እናምናለን። እሱም ውስጡ ምን እንደያዘ እንደማያውቅ ነግሮናል። ዕቃ ለማድረስ፣ የት እንደሚደርስ መመሪያ በጽሑፍ መልዕክቶች ይደርሱት ነበር” ብላለች።

“በአንድ ወቅት ፖሊስ አስቁሞ ሲፈትሸው በጥቅሉ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ አገኙ። በበይነ መረብ ለሚሠራ ድርጅት እቃ በማድረስ እንደሚሠራ እና ስለ እሽጉ እንደማያውቅ ቢናገርም በእስር ላይ መዋሉን” ተናግራለች።

ሆኖም ቤተሰቡ ተስፋ አልቆረጠም። አንድ ቀን በሰላም ወደ አገሩ፣ ወደ ቤቱ ይመለሳል የሚል ተስፋን ሰንቀው ነበር።

ነገር ግን በእስር ላይ እያለ የሩሲያ ቅጥረኛ የተዋጊዎች ቡድን በሆነው ዋግነር አማካይነት ለሩሲያ እንዲዋጋ መመልመሉን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።

ቡድኑ እነዚህ እስረኞች ለሩሲያ የሚዋጉ ከሆነ በምትኩ ነጻነታቸውንም ያገኛሉ የሚል ቃል ሰጥቷቸዋል።

መስከረም ወር ላይ ዋግነር በዩክሬን የሚዋጉ እስረኞችን ሲመለምል የሚያሳይ ቪዲዮ ሾልኮ ወጥቶ ነበር።

በቪዲዮው ላይ የዋግነር ቡድን ኃላፊው ዬቭጌኒ ፕሪጎዝሂ የጦርነቱን ሕግጋት ሲገልጽ ታይቷል።

ሠራዊቱን ትቶ መሄድ፣ ከዩክሬን ሴቶች ጋር ወሲብ መፈጸም የተከለከለ ስለመሆኑ ሲናገር የሚሰማ ሲሆን እስረኞቹ መዋጋት ይፈልጉ እንደሆነ እንዲወስኑ አምስት ደቂቃ ሰጥቷቸዋል።

እስረኞቹን ከእስር ቤት እንደሚያስወጣቸው ቢነግራቸውም ከጦርነቱ በሕይወት ለመመለስ ቃል አልገባም ሲልም አክሏል።

ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ወንድሜን ነጠቁን”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሌሚካኒ ወላጆች ኤድዊን እና ፍሎረንስ ኒሬንዳ የዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው። ሌሚካኒ ከአራት ልጆች መካከል የመጨረሻው ትንሹ ነበር።

በእስር ቤትም እያለ ቢሆን የሚወዳቸውን ቤተሰቦቹን ዘመዶቹን በስልክ እየደወለ ያገኛቸው ነበር።

ለመጨረሻ ጊዜ ወላጆቹ ድምጹን የሰሙት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ማገባደጃ ላይ ሲሆን፣ የመጨረሻውም ስልክ ምሥጢራዊ ስለነበር ቤተሰቦቹን ስጋት ውስጥ የከተተ ነበር።

“ለወላጆቼ 'እስር ቤት አይደለሁም፣ ወጥቻለሁ፣ ነገር ግን ስላለሁበት ቦታ በግልጽ መናገር አልችልም' ሲላቸው ወላጆቼ ተጨነቁ፣ ሁላችንም ተጨነቅን። በባዕድ አገር እስረኛ እና መብት የሌለው መሆኑን እናውቃለን። ምን እየሆነ እንዳለ ተጨንቀን ነበር። ነገር ግን የበለጠ መናገር አልቻለም እና ወላጆቼ ብዙም ሊያስጨንቁት አልፈለጉም” ስትል እህቱ ገልጻለች።

ሆኖም ቤተሰቡ ያልተለመደውን ጥሪ ለዛምቢያ ባለሥልጣናት ያሳውቁ ሲሆን፣ የት እንደሚኝም እንዲያጣሩላቸው ከጠየቁ ከወራት በኋላ የልጃቸውን ሞት ተረዱ።

“ወጣት ነበር፣ ሕይወቱን ነጠቁት። መንታ ወንድም አለው፣ የወንድሜን ግማሽ ነጠቁት” ትላለች እህቱ በእንባ ታጥባ።

“ሌሚካኒ በጣም ብዙ ዕቅድ ነበረው። ትምህርቱን ጨርሶ አገሩ ተመልሶ እናቴን አንቀባሮ የመያዝ ዕቅድ ነበረው። ዛምቢያን መልሶ ለመገንባትም ዕቅድ ነበረው። ዘርፈውናል” ብላለች።

“እርማችንን ልናወጣ አንችልም። ጥያቄዎች ብቻ ናቸው ያሉን። አስከሬኑ በሰላም እንዲያርፍልን ወደ አገሩ ማምጣት እንፈልጋለን። ቢያንስ አስከሬኑ በሚወዱትና በሚያፈቅሩት ሰዎች መካከል ይረፍ። ግን አሁንም ቢሆን መልስ እንፈልጋለን” ብላለች።

የሌሚካኒ አስከሬን ወደ ሩሲያ ደቡባዊ ድንበር ከተማ ሮስቶቭ አን ዶን በማጓጓዝ ወደ ዛምቢያ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የዛምቢያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቢቢሲ ለዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረባቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም።

ዛምቢያ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት ገለልተኛ አቋም ብትወስድም፣ ማንኛውንም አይነት ጦርነት እንደምታወግዝ አስታውቃለች።