ለሩሲያ ሲዋጋ በዩክሬን ተገድሏል በተባለው ዜጋዋ ጉዳይ ዛምቢያ ጥያቄ አነሳች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛምቢያ በዩክሬን ለሩሲያ ሲዋጋ የነበረ ተማሪ መገደሉን ተከትሎ ጥያቄ አነሳች።
ዛምቢያ በሌሚካኒ ኒሬንዳ አሟሟት ዙሪያ በአስቸኳይ ሩሲያ መረጃ ትስጠኝ ስትል ጠይቃለች።
ለሩሲያ ሲዋጋ ነበር የተባለው ዛምቢያዊ የሞስኮ ኢንጂነሪንግ ፊዚክስ ኢንስቲትዩት ተማሪ ሲሆን የ23 ዓመት ወጣት ነው።
ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ዓመት እስር ተፈርዶበትም በእስር ቤት ውስጥ ነበር።
ተማሪው የተገደለው መስከረም ወር ላይ ቢሆንም ሩሲያ ለዛምቢያ መንግሥት ያሳወቀችው በቅርቡ ነው።
የሌሚካኒ አስከሬን ወደ ሩሲያ ደቡባዊ ድንበር ከተማ ሮስቶብ አን ዶን በማጓጓዝ ወደ ዛምቢያ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑንም በሩሲያ የሚገኘው የዛምቢያ ኤምባሲ ማረጋገጡን የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስታንሊ ካኩቦ ተናግረዋል።
“ቤተሰቡን በግል አግቻቸዋለሁ። ከሟች ቤተሰብ ጋር ያለኝን ግንኙነትም እቀጥላለሁ፤ የሚወዱትን ሰው ሞት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት የተቻለውን አደርጋለሁ” ብለዋል።
ዛምቢያ የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎችን ወደ ሩሲያ የምትልክ ስትሆን ሌሚካኒም ስኮላርሽፕ አግኝቶ ነበር የሄደው።
ከእስር የተፈታበት ሁኔታ በውል የማይታወቅ ሲሆን ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ሊዋጉላት ፈቃደኛ ለሆኑ እስረኞች በምትኩ ነጻነታቸውን ሰጥታለች።
መስከረም ወር ላይ የሩስያ ቅጥረኛ ቡድን ዋግነር በዩክሬን የሚዋጉ እስረኞችን ሲመለምል የሚያሳይ ቪዲዮ ሾልኮ ወጥቶ ነበር።
በቪዲዮው ላይ የዋግነር ቡድን ኃላፊው ዬቭጄኒ ፕሪጎዝሂ የጦርነቱን ህግጋት ሲገልጽ ታይቷል። ሰራዊቱን ትቶ መሄድ፣ ከዩክሬን ሴቶች ጋር ወሲብ መፈጸም የተከለከለ ስለመሆኑ ሲናገር የሚሰማ ሲሆን እስረኞቹ መዋጋት ይፈልጉ እንደሆነ እንዲወስኑ አምስት ደቂቃ ሰጥቷቸዋል።
እስረኞቹን ከእስር ቤት እንደሚያስወጣቸው ቢነግራቸውም ከጦርነቱ በህይወት ለመመለስ ቃል አልገባም ሲልም አክሏል።
ዛምቢያ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ገለልተኛ አቋም ብትወስድም ነገርግን ማንኛውንም አይነት ጦርነት እንደምታወግዝ አስታውቃለች።












