"ሕልም ስላለኝ ብታመምም መኖር፣ መታገል እና ታትሮ መሥራትን አላቋርጥም"- በካንሰር የታመሙት ሌሊሴ ዱጋ

ሌሊሴ ዱጋ

የፎቶው ባለመብት, Lelise Dhugaa

የኦሮሚያ የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ የካንሰር ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን በመግለጽ ፎቷቸውን ጭምር አያይዘው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከቀናት በፊት አጋርተው ነበር።

ሌሊሴ ፀጉራቸውን ተላጭተው ከሚሠሩበት ላፕቶፕ ፊት ለፊት በፈገግታ የተሞላ ፎቶ ግራፋቸውን "እየሠራሁ፣ እየታገልኩ፣ እያሳካሁ" ከሚል የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ጋር አጋርተዋል።

ኮሚሽነሯ ይህንን ፎቶ እና መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ በርካታ ሰዎች እንዲፈወሱ መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ ፎቷቸውን እያጋሩት ነው።

እንዲህ ያለውን የጤና ሁኔታ ለሕዝብ ማጋራት ባልተለመደበት ማኅበረሰብ ውስጥ ኮሚሽነር ሌሊሴ ይህንን ማድረጋቸው በብዙዎች ዘንድ መነጋጋሪያ ከመሆኑ በላይ አድናቆት እንዲቸራቸው አድርጓል።

ቢቢሲም ሌሊሴን ሕክምና እየተከታተሉ ከሚገኙበት የመካከለኛው ምሥራቋ ዮርዳኖስ በስልክ አግኝቷቸው ስላሉበት ሁኔታ አጭር ቆይታ አድርጓል።

ሌሊሴ፤ 'ሊምፎሚያ' በተባለው የካንሰር ዓይነት መያዛቸውን ያወቁት ከአራት ወራት በፊት ለሌላ ምርመራ ወደ ጤና ተቋም በሄዱበት ወቅት ነበር።

ይህ የካንሰር ዓይነት ነጭ የደም ሕዋስን የሚያጠቃ ነው።

"የጋስትሮኢንተስታይን ችግር [ሰውነት ምግብ የሚያብላላበት ሆድ ዕቃ ሕመም] መስሎኝ ወደ ሆስፒታል ሄድኩ። ካንሰር እንደሆነ ተነገረኝ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ቀላል አይደለም። የካንሰር አራተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለሁት። የሚጎዳኝ ነገር ቢሆንም በፈጣሪ አምናለሁ። ፈጣሪን አስቀድማለሁ። እፀልያለሁ።"

"ባለቤቴ፣ ልጆቼ፣ ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ከጎኔ ናቸው። ይፀልዩልኛል። ያበረታቱኛል። ሕልም ስላለኝ ብታመምም መኖር፣ መታገል እና ታትሮ መሥራት አላቋርጥም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ፀጉሬን አጥቻለሁ፤ ቆንጆ ፀጉር ነበረኝ"

ሌሊሴ አሁን ላይ የኬሞቴራፒ ሕክምና እያገኙ ነው። ብዙ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም ይናገራሉ።

"ፀጉሬን አጥቻለሁ። ቆንጆ ፀጉር ነበረኝ። ፀጉር ማጣት ለሴት ልጅ ከባድ ነው። ፀጉርን ማጣት የተለየ ዝግጅት ይጠይቃል" ሲሉ ይገልጹታል።

"ፈጣሪ ረድቶኝ ወደ አገሬ ከተመለስኩ ለሕክምና ገንዘብ የሌላቸውን የካንሰር ሕሙማን የሚደግፍ ማዕከል ማቋቋም እፈልጋለሁ" በማለት ሕልማቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

የካንሰር ሕክምና ከፍተኛ ገንዝብ ከማስወጣቱም ባሻገር የሥነ ልቦና ጥንካሬን ይፈታተናል።

"በባለቤቴ በኩል የተባበሩት መንግሥታት የጤና መድኅን አለኝ፤ መንግሥትም እያሳከመኝ ነው። የገንዘብ ችግር ስለሌለብኝ ነው እየታከምኩ ያለሁት። እርዳታ የሚያሻቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ሲሻለኝ እነዚህ ሰዎች ለመርዳት ማዕከል አቋቁማለሁ" ሲሉ ሌሊሴ ተናግረዋል።

"የሕይወት ፍልስፍናዬ ቀላል ነው"

አሁን ላይ ብርታት የሰጣቸው የሕይወት ፍልስፍናቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

"የሕይወት ፍልስፍናዬ ቀላል ነው። በየቀኑ የምችለውን ማድረግ፣ ዋጋ ያለው ነገር ማድረግ እና ጥሩ መሆን። ፈጣሪ ያስተማረን ይሄንን ነው። ምድር ላይ እስካለን ድረስ ጥሩ ነገር ብናደርግ መልካም ነው" ይላሉ።

"ያለኝ ሕይወት የኔ አይደለም። የእግዚአብሔር ነው። የምኖረው እሱ የሰጠኝን ነው። ያለ ፀፀት መኖር ነው የምሻው። ለመኖር የሚያበረታኝ እና ወደፊት የምቀጥለው በዚህ ነው።"

ሌሊሴ በየዕለቱ ጥሩ እንዳደረጉ ለራሳቸው እንደሚነገሩና ከፈጣሪ ምሕረትን ጠይቀው እንደሚተኙ ይናገራሉ።

ሕክምናቸውን ለመጨረስ ከአራት እስከ አምስት ወራት ይወስድባቸዋል።

የካንሰር ሕክምና ያላቋረጠው ሥራ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሌሊሲ ከአምስት ዓመታት በላይ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል።

'ቪዚት ኦሮሚያ' የሚለው መሪ ቃል ሲሰማ የሌሊሴም ስም አብሮ ይነሳል።

በዮርዳኖስ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ጎን ለጎን ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ቢሮ አላቸው። አንድም ቀን ታምሜያለሁ ብለው እያሰቡ እንደማያድሩ ይናገራሉ።

"የኦሮሚያ የቱሪዝም ኮሚሽን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን እያወጣሁ ነው። በቀጣይ አምስት ዓመታት ምን መሠራት አለበት የሚለውን ነው የምሠራው" ሲሉ ገልጸዋል።

ካለፉት አምስት ዓመታት በመማር በቀጣይ አምስት ዓመታት ምን መሥራት እንደሚቻል የትኩረት አቅጣጫ እየቀረጹ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

"ኬሞቴራፒ ያለኝ ቀን ሆስፒታል እሄዳለሁ። ሁሉም ቀኖቼ በሥራ የተሞሉ ናቸው" ይላሉ ሌሊሴ።

ሌሊሴ ከአሥር ዓመታት በላይ በብሔራዊ ደረጃ በሚካሄደው የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።

ሥራቸውን የጀመሩት ወጣት ሴቶችን ከኤችአይቪ/ኤድስ ለመከላከል በሚደረግ ንቅናቄ ነው።

"ችግር ሲገጥመን የመጀመሪያው እርምጃ በሰላም ለመኖር ራስን ማሳመን ነው" ይላሉ።

ብዙዎች በካንሰር ሲያዙ በሽታው ፈውስ የሌለው ገዳይ ነው ብለው ስለሚያስቡ ስላሉበት የጤና ሁኔታ ለመናገር ይፈራሉ።

በአገራችን ሰዎች ካንሰርን ቀርቶ ስለሌሎች በሽታዎች በአደባባይ ሳይሆን በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ለመንገር እና ለማሳወቅ አይደፍሩም።

ሌሊሴ ግን ይህንን በመስበር ስለጤናቸው ሁኔታ እና ስለወደፊት ዕቅዳቸው ተስፋ በተሞሉ ቃላት ከምሥላቸው ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርተዋል።

"ልክ በኤችአይቪ እንዳደረግኩት ሁሉ ሰዎችን ስለ ካንሰር ማስተማር እፈልጋለሁ" ይላሉ።

ሌሊሲ የአመራር ብቃትን የተመለከተ መጽሐፍም እየጻፉ ነው። መጽሐፉን እንዳጋመሱት ይናገራሉ። በቅርቡ እንደሚጠናቀቀም ገልጸዋል።

"በየቀኑ አዲስ ነገር እንማራለን። አንድ ሰው በየቀኑ የሚማረውን ነው የሚሆነው። አዲስ ራዕይ ይኖረዋል። ወይም ተሞክሮውን ተመርኩዞ አካሄዱን ይለውጣል።"

አንድ መሪም በዚህ ሒደት እንደሚያልፍ ሌሊሴ ይናገራሉ።

"ስለ አመራር የሚገልጸውን መጽሐፍ የምጽፈው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያገኘሁትን ተሞክሮ ለማስተላለፍ ነው" ሲሉም ያክላሉ።

ሌሊሴ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ውስጥ ነው።

በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሠርተዋል። በብሪታኒያ ኤምባሲ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ቢሮ አማካሪ ሆነው ከአንድ ዓመት በላይ ሠርተዋል።

እሳቸው የሚመሩት የኦሮሚያ ኮሚሽን የተቋቋመው የኦሮሚያን የቱሪስት መዳረሻዎች በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ እና የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ነው።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከፍቷል። በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ለውጥ በማምጣትም ተጠቃሽ ተቋም ነው።