ናይጄሪያ እገታ የሚፈጽሙ ሰዎችን በሞት የሚቀጣ ሕግ ልታወጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እገታ የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት መጣል የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ላይ መነጋገር ጀመሩ።
የሴኔቱ አባላት እገታ ፈጽመው የሚገኙ ሰዎች የሽብር ተግባር ላይ እንደተሰማሩ ተቆጥሮ የሞት ቅጣት እንዲጣልባቸው ለማድረግ የአገሪቱን የጸረ ሽብር ሕግን ለማሻሻል መወያየት ጀምረዋል።
የናይጄሪያ የሴኔት አባላት የሕግ ማሻሻያው ላይ መነጋገር የጀመሩት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚፈጸም የጅምላ ጠለፋ እና እገታ እንዲሁም ደም አፋሳሽ ጥቃቶች እየጨመሩ በመጡበት ወቅት ነው።
ባለፉት ሳምንታት የታጠቁ ሰዎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት ከፍተው ከ300 በላይ ተማሪዎችን አግተዋል።
የተለያዩ ማኅበረሰቦች መኖሪያዎች እና የአምልኮ ስፍራዎች በታጣቂዎቹ ዒላማ የሆኑ ሲሆን የፀጥታ ኃይሉም በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ግድያዎች እና እገታዎች ተወጥሯል።
የሕግ አውጪዎች እያደገ የመጣው ስጋት ፈጣን እና የማያወላውል ምላሽ መስጠትን ይጠይቃል ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት የሕዝብ ተወካዮቹ ባደረጉት ውይይት የአገሪቱ ወታደራዊ እና የደህንነት ተቋማት በመረጃ ላይ የተመሰረተ የአየር ላይ ቅኝት፣ የደኖች አሰሳ፣ ድንበር ተሻጋሪ ትብብር እና ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው ክዋራ፣ ኮጊ፣ ኬቢ እና ኒጀር ግዛቶች ማኅበረሰብ ተኮር መረጃ የመሰብሰብ ዘመቻ እንዲያካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
የፌደራል መንግሥትም የአካባቢ ታጣቂ ቡድኖችን፣ ሚሊሻዎችን፣ እንዲያጠናክር እና የናይጄሪያ ጦር መሣሪያ ሕግን እንዲከልስ ጠይቀዋል።
175 አገራት ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥጥር በሚደረግበት ሁኔታ መሣሪያ እንዲታጠቁ ይፈቅዳሉ ብለዋል።
በናይጄሪያ ያለው የፀጥታ ስጋት በፈጠረው ጫና ምክንያት ፕሬዚዳንት ቦላ አህመድ ቲኒቡ በዚህ ሳምንት የፖሊስ አባላትን ከልዩ ጥበቃ ስራ እንዲያወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ይህም በፖሊስ ጥበቃ እና እጀባ የሚፈልጉ የሕግ አውጪዎች ከለላውን ማግኘት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።
አንዳንድ የሕግ አውጭዎች ፖሊሶች ወደ ሌላ ሥራ ከተሰማሩ የወንጀል ቡድኖች ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
እንዲሁ ረቡዕ ዕለት ፕሬዚዳንት ቲኑቡ በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀው ፖሊስ እና መከላከያ አዳዲስ አባላትን በሰፊው እንዲመለምሉ አዝዘዋል።
ይህም ተጨማሪ 50,000 አዲስ የፖሊስ አባላትን መመልመል ያስችላል ተብሏል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለሚፈጸሙ ጥቃቶች እና እገታዎች ጽንፈኛ ኃይሎች ሲሉ የሚጠሯቸውን ኢስላሚክ ስቴት እና ቦኮ ሃራምን ይወነጅላሉ።
ከእገታው ማትረፍ የሚፈልጉ ወንጀለኞችም ከጠለፋው ጀርባ መኖራቸው ይጠቀሳል።
ፕሬዚዳንት ቲኒቡ መግለጫቸው ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹን አገሪቱን እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ "የክፋት ወኪሎች" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
የፕሬዚዳንቱ መግለጫ ናይጄሪያ በከፍተኛ ኃይል የታጀበ በሰው ኃይል የሚመራ የደህንነት ስልት ለመከተል መወሰኗን ያሳያል።
ፕሬዚዳንቱ አክውም አዲስ ክልላዊ የፖሊስ ኃይል እንዲኖር የሚጠይቀውን ዕቅድ የደገፉ ሲሆን ይህም የናይጄሪያ የወደፊት የፀጥታ ኃይል አወቃቀር ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውይይት እና ክርክር ይቀሰቅሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንቱ ለአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ተጨማሪ አዳዲስ ዲፕሎማቶችን ሾመዋል።
ሹመታቸው የአገሪቱ የሕዝብ ተወለካዮች ምክርቤት ከተወያየበት በኋላ የሚጸድቅ ይሆናል።
አንዳንድ የናይጄሪያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች የፕሬዚዳንቱ ውሳኔዎች የመጡት የአሜሪካ ጫናን ተከትሎ ነው ይላሉ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስትያኖች" ሞትን ለማስቆም "ጦራቸውን እንደሚያዘምቱ" በመግለጽ አስጠንቅቀው ነበር።
ይህም በአገሪቱ ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ክፍሎች ጥቃቶች መቀጠላቸውን ተከትሎ አቡጃ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን በፍጥነት መውሰድ እንድትጀምር አድርጓታል።















