በናይጄሪያ ትምህርት ቤቶች ከተፈጸመው የጅምላ እገታ 50 ተማሪዎች አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በናይጄሪያ ኒጀር ግዛት ከሚገኝ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ባለፈው አርብ በታጣቂዎች ከታገቱት 315 ተማሪዎች መካከል ሃምሳዎቹ ማምለጣቸው ተገለፀ።
የናይጄሪያ ክርስቲያኖች ማኅበር ያመለጡት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን ተናግሯል።
አሁንም በአጋቾቹ ቁጥጥር ሥር ያሉትን 265 ሕጻናት እና 12 መምህራንን ለማግኘት የአገሪቱ ጦር ከፍተኛ አሰሳ እያካሄደ ነው።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት በኒጀር የተፈፀመውን የጅምላ እገታ እንዲሁም ሰኞ ዕለት በኬቢ ግዛት 20 ተማሪዎች ከአዳሪ ትምህርት ቤት መወሰዳቸውን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አዝዘዋል።
ባለፈው ሳምንት በኳራ ግዛት በቤተክርስቲያን ውስጥ የአምልኮ ሥነስርዓት እየተካፈሉ ሳለ ታፍነው የተወሰዱ 38 ሰዎች እሁድ ዕለት መለቀቃቸውን የግዛቱ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
በኤሩኩ የክርስቶስ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በኬቢ፣ ኒጀር፣ ካትሲና፣ ዮቤ እና ክዋራ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ትዕዛዝ ተላልፏል።
የልጆቹ የማምለጥ ዜና፤ ለቤተሰቦቻቸው እና በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምዕራብ የታገቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እጣ ፈንታ ስጋት ገብቷቸው ለነበሩ ናይጄሪያውያን እፎይታን የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኝ አንድ የክርስቲያን ቡድን ተማሪዎቹ ከአርብ እስከ ቅዳሜ ባለው ጊዜ ውስጥ ለማምለጥ መቻላቸውን አብራርቶ፣ ከአጋቾቻቸው መዳፍ መውጣታቸውን አደጋ የተሞላበት የጀግንነት ተግባር ሲል ገልጾታል።
ተማሪዎቹ እና መምህራኑ የተወሰዱት በኒጀር ግዛት ፓፒሪ ከሚገኘው ቅድስት ማርያም የካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው።
አሁን በአጋቾቹ የተወሰዱት ተማሪዎች እና መምህራን ቁጥር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2014 ከተፈጸመው እና 276 ተማሪዎች ከታገቱበት የቺቦክ የጅምላ እገታ በልጧል።
የኒጀር ግዛት አስተዳዳሪ መሀመድ ኡማሩ ቦንጎ፤ በአካባቢው ያሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚዘጉ ቅዳሜ ዕለት አስታውቀዋል። ይህ "ጣታችንን የምንቀሳሰርበት እና የምንወነጃጀልበት ጊዜ አይደለም" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች እንዲለቀቁ የጠየቁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ "ከፍተኛ ሀዘን" አንደተሰማቸው በመግለጽ ባለሥልጣናቱ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት እና ሴት ልጆቻቸው በትምህርት ቤቱ የሚማሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶሚኒክ አዳሙ "ሁሉም ሰው ደካማ ነው... ሁላችንንም ያስደነገጠ ነው" ብለለል። "በአገራችን ባለው የፀጥታ ሁኔታ ሕዝቡ እየተማረረ ነው" ሲሉም አክለዋል።
አንዲት የተጨነቀች እናት ደግሞ እያለቀሰች እድሜያቸው 6 እና 13 የሆነ የእህቶቿ ልጆች መታገታቸውን ተናግራለች።
"ወደ ቤት እንዲመጡ ብቻ ነው የምፈልገው" ብላለች።
የመከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ታጣቂዎቹ ይደበቁባቸዋል ተብለው የሚታመኑ ደኖች እና ራቅ ያሉ መንገዶችን ላይ አሰሳ እያካሄዱ ነው።
የኒጀር ግዛት ባለሥልጣናት ሴቶች እና ወንዶች በሚማሩበት ይህ ትምህርት ቤት ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የተሰጠውን ትዕዛዝ ችላ ብሎ ነበር ብለዋል።
በናይጄሪያ ሽፍቶች ተብለው የሚታወቁት ወንጀለኛ ቡድኖች ሰዎችን አግተው የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸው የተለመደ ነው።
የወንጀለኛ ቡድኖችን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ በሚል ለታገቱ ሰዎች ማስለቀቂያ የሚከፈል ገንዘብ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም እምብዛም ውጤት አላስገኘም።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት ሙስሊም መሆናቸው የተነገረላቸው ከ20 በላይ ልጃገረዶች በኬቢቢ ግዛት ከሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ታግተዋል።
የግዛቲቱ ባለስልጣናት ሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች እንዲዘጉ አዝዘዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የናይጄሪያ መንግሥት "ክርስቲያኖች እንዲገደሉ መፍቀዱን ከቀጠለ" ወታደሮቻቸውን እንደሚልኩ ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ አገሪቱ የገጠማትን የጸጥታ ጉዳዮች ለመፍታት በሚል በሳምንቱ መጨረሻ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
በሰሜን ምስራቅ የጂሃዲስት ቡድኖች ከአስር ዓመታት በላይ ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።
በአካበቢው የሚካሄዱ ግጭቶችን የሚከታተሉ ድርጅቶች አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በመሆኑ የእነዚህ ቡድኖች ተጠቂዎች ሙስሊሞች ናቸው ይላሉ።
በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል በአብዛኛው ሙስሊም በሆኑ አርብቶ አደሮች እና በክርስትያን አርሶ አደሮች መካከል ከባድ ግጭት ይቀሰቀሳል።
ይሁን እንጂ ተንታኞች እንደሚናገሩት እነዚህ ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት ይልቅ እንደ ውሃ ወይም መሬት ባሉ አለመግባባቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ናቸው።















