በናይጄሪያ ታጣቂዎች ከ200 በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት አግተው ወሰዱ

አርብ ማለዳ ላይ እገታ የተፈጸመበት ቅድስት ማሪያም የካቶሊክ ትምህርት ቤት
የምስሉ መግለጫ, አርብ ማለዳ እገታ የተፈጸመበት ቅድስት ማሪያም የካቶሊክ ትምህርት ቤት

በማዕከላዊ ናይጄሪያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች አርብ ዕለት ወደ አንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት በመግባት ከ200 በላይ ተማሪዎችን አግተው መውሰዳቸው ተሰማ።

ይህ በዚህ ሳምንት የደረሰ ሁለተኛው የጅምላ እገታ ነው።

እገታው የተፈጸመው በኒጀር ግዛት ፓፓሪ በሚገኘው የቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱ በፀጥታ ስጋት ምክንያት ሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

የናይጄሪያ ክርስቲያኖች ማኅበር እንደገለፀው አርብ ማለዳ ታጣቂዎች ወደ ትምህርት ቤቱ በመግባት 215 ተማሪዎች እና 12 ሠራተኞችን ወስደዋል።

ናይጄሪያ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በታጣቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ አዲስ ጥቃቶችን እያስተናገደች ነው።

ሰኞ ዕለት በኬቢ ግዛት ከሚገኝ አዳሪ ትምህረት ቤት ሙስሊሞች ናቸው የተባሉ ከ20 በላይ ሴት ተማሪዎች ታግተው ተወስደዋል።

በክዋራ ግዛት የሚገኝ አንድ ቤተ ክርስትያን የአምልኮ ሥነ ስርዓቱ በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ በተፈፀመ ጥቃት ሁለት ምዕመናን ሲገደሉ 38 ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ እነዚህን የጸጥታ ጉዳዮች ለመፍታት በሚል በዚህ ሳምንት መጨረሻ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ ፖሊስ ገለጻ፤ በአካባቢው "ሽፍታ" ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ታጣቂዎች፤ አርብ እለት ማለዳ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ወደ ቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት በመግባት ተማሪዎችን ከማደሪያቸው አፍነው ወስደዋል።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ዶሚኒክ አዳሙ ሴት ልጆቻቸው በቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት ቢማሩም አለመታገታቸውን ገልፀው "ሁሉም ሰው ደካማ ነው... ሁላችንንም ያስደነገጠ ነው" ብለዋል።

አክለውም "በአገራችን ባለው የፀጥታ ሁኔታ ሕዝቡ እየተማረረ ነው" ይላሉ።

አንዲት የተጨነቀች እናት ደግሞ እያለቀሰች እድሜያቸው 6 እና 13 የሆነ የእህቶቿ ልጆች መታገታቸውን ተናግራለች።

"ወደ ቤት እንዲመጡ ብቻ ነው የምፈልገው" ብላለች።

የኒጀር ግዛት ባለሥልጣናት ሴቶች እና ወንዶች በሚማሩበት ይህ ትምህርት ቤት ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የተሰጠውን ትዕዛዝ ችላ ብሎ ነበር ብለዋል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ የቅድስት ማርያም ትምህርት ቤት የክልሉ መንግሥትን ሳያውቅ ወይም ፈቃድ ሳይጠየቅ እንደገና በመክፈት የመማር ማስተማሩን ተግባር ቀጥሏል፤ በዚህም ተማሪዎችን እና ሠራተኞችን ሊወገድ ይችል ለነበረ አደጋ አጋልጧል" ብሏል በመግለጫው።

ትምህርት ቤቱ ለፖሊስ መግለጫ ምላሽ አልሰጠም።

የጸጥታ አካላት "የታገቱትን ተማሪዎች ለመታደግ በማሰብ ጫካዎች ውስጥ ፍለጋ እያካሄዱ ነው" ሲል ፖሊስ ተናግሯል።

ጥቃቱ የደረሰው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስቲያኖች ጥቃት እያስተናገዱ ነው ካሉ እና የአገሪቱ መንግሥት ውንጀላውን ውድቅ ካደረገ በኋላ ነው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የናይጄሪያ መንግሥት "ክርስቲያኖች እንዲገደሉ መፍቀዱን ከቀጠለ" ወታደሮቻቸውን እንደሚልኩ ተናግረው ነበር።

ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስትር ፒት ሄግሰት ከናይጄሪያ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጋር ባደረጉት ስብሰባ አገራቸው በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም አስቸኳይ እና ዘላቂ እርምጃ እንድትወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

ሄግሰት "ዩናይትድ ስቴትስን የሚያሰጉ አሸባሪዎችን ለመከላከል እና ለማጥፋት ከናይጄሪያ ጋር በመተባበር በጥምረት ትሰራለች" ሲሉ ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ ሽፍቶች ተብለው የሚታወቁት ወንጀለኛ ቡድኖች ሰዎችን አግተው የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸው የተለመደ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ታጣቂዎች ተማሪዎቹን በኬቢ ግዛት ከሚገኘው ማጋ አካባቢ አግተው ከመውሰዳቸው በፊት ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Africa Independent Television via Reuters

የምስሉ መግለጫ, በዚህ ሳምንት መጀመርያ ታጣቂዎች በኬቢ ግዛት ከሚገኘው ማጋ አካባቢ ተማሪዎችን አግተው ከመውሰዳቸው በፊት ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ነበር

በሰሜን ምስራቅ የጂሃዲስት ቡድኖች ከአስር ዓመታት በላይ ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።

በአካበቢው የሚካሄዱ ግጭቶችን የሚከታተሉ ድርጅቶች አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈጸሙት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በመሆኑ የእነዚህ ቡድኖች ተጠቂዎች ሙስሊሞች ናቸው ይላሉ።

በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል በአብዛኛው ሙስሊም በሆኑ አርብቶ አደሮች እና በክርስትያን አርሶ አደሮች መካከል ከባድ ግጭት ይቀሰቀሳል።

ይሁን እንጂ ተንታኞች እንደሚናገሩት እነዚህ ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት ይልቅ እንደ ውሃ ወይም መሬት ባሉ አለመግባባቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ናቸው።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ታጣቂዎች በክዋራ ግዛት ከሚገኝ ቤተክርስትያን ለታገቱት ሰዎች የማስለቀቂያ ገንዘብ ጠይቀዋል።

ለወንጀለኛ ቡድኖች የሚሰጥ ገንዘብን ለመቀነስ በሚል ለማስለቀቂያ የሚከፈል ገንዘብ በሕግ የተከለከለ ነው።

ሰኞ ዕለት በኬቢ ግዛት በማጋ ከተማ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ማምለጥ የቻሉ ሲሆን 23ቱ ግን አሁንም በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ናቸው።

በጥቃቱ ሁለት ሙስሊሞች ተገድለዋል።