ናይጄሪያ ለልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰጠውን ትምህርት አስቀርታ በእንግሊዝኛ ተካች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ መንግሥት የመጀመርያ ደረጃ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚያዘውን አወዛጋቢ ፖሊሲ መሰረዙን አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ቱንጂ አላኡሳ ከሦስት ዓመት በፊት ተግባር ላይ የዋለው ይህ ፕሮግራም የታለመለትን ግብ ስላልመታ ከአሁን ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተወስኗል ብለዋል።
በዚያ ምትክ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ እንግሊዘኛ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
አሁን የተሰረዘው በአፍ መፍቻ እንዲማሩ የሚያዘው ፖሊሲ ሥራ ላይ የዋለው በቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር አዳሙ አዳሙ ሲሆን፣ ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይበልጥ ይማራሉ ሲሉ ይከራከራሉ።
አዳሙ ሕጻናት "በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ" ጽንሰ ሃሳቦችን በቀላሉ ለመረዳት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ይህ የቀድሞው ሚኒስትር ሃሳብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ባካሄዳቸው በርካታ ጥናቶች ላይም ተቀባይነት ያገኘ ነው።
የናይጄሪያ ትምህርት ሥርዓት በትምህርት ጥራት ማነስ፣ በቂ የሆነ የማስተማሪያ መሣሪያ ባለመኖር፣ በዝቅተኛ የመምህራን ደሞዝ እና በርካታ የትምህርት ማቆም አድማዎች በመካሄዳቸው ተግዳሮቶች ገጥሞታል።
በአገሪቱ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑ ሕጻናት ወደ መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ቢሄዱም ሁለተኛ ደረጃን ግን የሚያጠናቅቁት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው።
በናይጄሪያ ከማንኛውም አገር በበለጠ፣10 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት የሳያል።
ዶ/ር አሉሳ የቋንቋ ፖሊሲውን መሰረዛቸውን በአቡጃ ባስታወቁበት ወቅት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
የምዕራብ አፍሪካውያን የፈተናዎች ካውንስል፣ የብሐየራዊ ፈተናዎች ካውንስል እና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ቦርድ ያወጧቸውን መረጃዎችም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ "በምዕራብ አፍሪካ ፈተናዎች ድርጅት በርካቶች ወድቀው አይተናል፤ እንዲሁም በአገር አቀፍ የመልቀቂያ ውጤትም በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁ ዝቅተኛ ውጤት ተመዝግቧል። እነዚያ ደግሞ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማር የወሰኑ እና እርሱን የተከተሉት ናቸው" ብለዋል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ፖሊሲው በድንገት መሰረዝ በትምህርት ባለሙያዎች፣ ተንታኞች እና ወላጆች ዘንድ የተደበላለቀ ምላሽ አስከትሏል።
የተወሰኑት አተገባበሩ ችግር እንደነበረበት እና ለጥራት መውረድ አስተዋጽኦ ማድረጉን በመግለጽ መንግሥትን ውሳኔ አድንቀዋል።
ሌሎች ደግሞ ፖሊሲው በአጭር መቀጨቱን ያነሳሉ።
እንደዚህ ዓይነት ለውጥ መምህራንን በበቂ ማሠልጠን፣ የመማሪያ መጻሕፍትን ጨምሮ ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን በበቂ ማቅረብ ያስፈልጋል፤ አልሰራም ከማለት በፊት ውጤቱ አንዲታይ በቂ ጊዜ መሰጠት ነበረበት ብለዋል።
የትምሀርት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አሊዩ ቲልዴ የመንግሥትን ውሳኔ ደግፈው ናይጄሪያ ለእንዲህ ዓይነት ፖሊሲ ዝግጁ አይደለችም ብለዋል።
"ናይጄሪያ በአገሪቱ በሚገኙ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ በቂ የሰለጠኑ መምህራን አሏት? መልሱ የላትም ነው። ሌላው ደግሞ ዋናው መመዘኛ የሆነው የምዕራብ አፍሪካ አገራት ፈተናዎች ድርጅት፣ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ሁሉም የሚሰጡት በእንግሊዘኛ ነው። በአፍ መፍቻ ቋንቋ አየሰጡም።"
"የሚመስለኝ የሚያስፈልገን የትምህርት ቤቶቻችንን ጥራት ማሻሻል እና ብቃት ያላቸው መምህራንን ማፍራት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግዋል።
በአፀደ ሕጻናት የሚማሩ ሁለት ልጆች ያላት ሃጃራ ሙሳ እንዲሁ የመንግሥትን ውሳኔ እንደምትደግፍ ገልጻ፣ ልጆች ገና በሕጻንነታቸው እንግሊዘኛ አንዲማሩ ያደርጋቸዋል ብላለች።
"እንግሊዘኛ በየትኛውም ስፍራ አገልሎት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፤ እናም እነዚህ ሕጻናት ትልቅ እስኪሆኑ ከመጠበቅ ይልቅ በልጅነታቸው ቋንቋውን መጠቀም መጀመር እንዳለባቸው ይሰማኛል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ነገር ግን የማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ሃቡ ዳኡዳ በዚህ አይስማማም።
"ተጨማሪ ጊዜ እንደመስጠት ያለጊዜው የተሰረዘ ይመስለኛል። እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ለውጥ ለመገምገም ሦስት ዓመት በጣም ትንሽ ነው። መንግሥት ተጨማሪ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ነበረበት" ብሏል።
ክርክሩ ናይጄሪያ ያሏትን የቋንቋ ሃብቶች ማስተዋወቅ ከብሔራዊ ሥርዓተ ትምህርት እና ከሉላዊነት ኢኮኖሚ ጋር በማመጣጠን ረገድ ያለባትንን ቀጣይ ተግዳሮት አጉልቶ ያሳያል።















