በተፈጥሮ ሒሳብ ሰነፍ የሆኑ ሰዎች አሉ?

ፊቱን መጽሐፍ ላይ የደፋ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, djedzura/Getty Images

ለአንዳንዶች ሒሳብ በቀላሉ የሚሠራ ሲሆን፣ ሌሎች ግን ቀላል የሚባለው ስሌት ሳይቀር ይፈትናቸዋል።

ይህ ከዘረ መል ጋር እንደሚያያዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ነገሩ የዘረ መል ብቻ ግን አይደለም።

ከሥነ ሕይወት፣ ከሥነ ልቦና እና አካባቢ ጋር ይተሳሰራል። ለመሆኑ በተፈጥሮ ሒሳብ ሰነፍ የሆኑ ሰዎች አሉ?

መንትዮች ላይ የተሠሩ ጥናቶች

ፕ/ር ዩሊያ ኮቫስ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን ያስተምራሉ። የዘረ መል እና ሥነ ልቦና ተመራማሪ ናቸው።

ሰዎች ሒሳብ ላይ ያላቸው ችሎታ ለምን እንደሚለያይ አጥንተዋል።

ተመሳሳይና የተለያዩ መንትዮች ላይ ያደረጉት ጥናት 10,000 ሰዎች ገደማ አሳትፏል።

ዘረ መልና አካባቢ እንዴት የትምህርት ብቃትን እንደሚወስኑ ለማወቅ ነው ጥናቱ የተካሄደው።

"ከሥነ ልቦና አንጻርተመሳሳይ የሆኑ መንትዮች ከማይመሳሰሉ መንትዮች በበለጠ ተቀራራቢ ናቸው። የሒሳብ ችሎታቸውም ተቀራራቢ ነው። ቤታቸው ወይም አካባቢያቸው ያለው ሁኔታ እምብዛም ልዩነት እንደማያመጣ ያሳያል። ዋናው የዘረ መላቸው ጉዳይ ነው" ይላሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከዚያም በላይ ዘረ መል ለሒሳብ ትምህርት ያለው ሚና ከ50 እስከ 60 በመቶ መሆኑን ፕ/ር ዩሊያ ይናገራሉ።

"ዘረ መል የአካባቢ ያህል ሚና እንዳለው ማሳያ ነው" ብለዋል።

አካባቢ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢም ሌላ የጎላ ሚና የሚጫወት ነው።

ትምህርት ቤቱ ምን ያህል ጥሩ ነው የሚለው ብቻ ሳይሆን የቤት ሥራ ሲሰጥ ተማሪዎች ምን ያህል እርዳታ ያገኛሉ የሚለውም ከግምት ይገባል።

አንድ ሰው ራድዮ ላይ በሰማው ነገር ወይም እንደው ባጋጣሚ ባየው/በሰማው ለሒሳብ ያለው ፍላጎት ሊለወጥ ይችላል።

ዘረ መል ፍላጎት ላይም ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

ሁሉም ሰው የሒሳብ ልሒቅ ባይሆንም ማንኛውም ሰው የሒሳብ ችሎታው ሊሻሻል ይችላል።

በሉግቦሮ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ኢሮ ዤንዶው-ደርቮው ስለ ሒሳብ ችሎታ ያጠናሉ።

የሒሳብ ችሎታን ለማሻሻል አመለካከት፣ ስሜትና አስተሳሰብ ከግምት ውስጥ እንደሚገቡ ዶ/ር ኢሮ ይናገራሉ።

'የሒሳብ ፍራቻ'

ባለሙያዋ እንደሚሉት የሒሳብ ፍራቻ የሒሳብ ችሎታ ላይ ጫና ያሳድራል።

የሒሳብ ክህሎትን ለማሻሻል በራስ ማመን ግድ ይላል።

አንዳንዶች ሒሳብ እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ በራስ መተማመናቸው ይወርዳል። በሒሳብ ፈተና አነስተኛ ውጤት ማምጣትም ለራስ ያለን አመለካከት ያዛባል።

እነዚህ የሒሳብ ፍራቻን ያባብሳሉ።

"ሒሳብን መፍራት ከሒሳብ መሸሽ ያስከትላል። ሒሳብን መሸሽ የሒሳብ ውጤትን ይቀንሳል። የሒሳብ ውጤት ሲቀንስ የሒሳብ ፍራቻ ይባባሳል። ነገሩ እሽክርክሪት ነው" ይላሉ ዶ/ር ኢሮ።

የሒሳብ ፍራቻ አእምሯችን መረጃ የሚይዝበትና ክንውኖችን የሚመራበትን የትውስታ ክፍል (working memory) ያውካል።

"ፍርሃት ይህንን የአእምሮ ክፍል ይጋርደዋል። የሒሳብ ስሌትን ለመሥራት የሚሆን ቦታም ያሳጣዋል" በማለት ባለሙያዋ ያብራራሉ።

የዘጠኝና አሥር ዓመት ልጆች ላይ በተሠራ ምርምር ላይ ሁለት ዲጂት ያለው የሒሳብ ስሌት ተሰጥቷቸዋል። ልጆቹ ቃላት እንዲሰሙ በማድረግ ምን ያህል የሰሙትን ቃላት ያስታውሳሉ? የሚለው ሲጠና የሒሳብ ፍራቻ ያላቸው ልጆች ቃላቱን የማስታወስ አቅማቸው ውስን ሆኖ ተገኝቷል።

በቻይና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ2000ዎቹ በተሰራ ዓለም አቀፍ ጥናት ቻይና በትምህርት ከቀዳሚ አገራት ተርታተመድባለች

ለሒሳብ 'ቅርብ' መሆን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን የሚያስተምሩት ፕ/ር ብራየን በተርወርዝ በኮግኒቲቭ ኒውሮሳይኮሎጂ ላይ ምርምር ያደርጋሉ።

ሰዎች በተፈጥሮ ሒሳብን የማወቅ አዝማሚያ አላቸው ይላሉ። ይህም ሒሳብ ያልተማሩ ሕጻናትን ይጨምራል።

ሆኖም ግን አንዳንዶች ለዚህ ተፈጥሯዊ አወቃቀር እምብዛም ቅርብ አይሆኑም።

ከሒሳብ ጋር የተያያዙ ስሌቶችን አለመረዳት (Dyscalculia) አንደኛው ምክንያት ነው።

ቃላትን አንብቦ መረዳት እንዳለመቻል (dyslexia) ያለ የክህሎት ውስንነት ነው። ይህም 5% ሰዎች ላይ ይስተዋላል።

ሒሳብን የመገንዘብ ክህሎታቸው በተፈጥሮ የደከመ ሰዎች ቀላል የሚባሉ ስሌቶች ሳይቀሩ ይቸግሯቸዋል።

ፕ/ር ብራየን ልጆችን ሒሳብ ለማስተማር የሚረዳ ጌም ፈጥረዋል። በተለይም ዲስካልኩሊያ ወይም ሒሳብን የመገንዘብ ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ይረዳል ተብሎ ይታመናል።

"የልጆችን የአእምሮ ዕድገት በመከታተል ለውጥ ለማምጣት የምንሞክርበት ስልት ነው" ይላሉ።

ዶ/ር ኢሮ እንደሚሉት፤ ሒሳብ ከሌሎች ትምህርቶች የተለየ የሆነው አእምሮ ውስጥ "እንደ ግንባታ ከፍ እያለ የሚሄድ" ስለሆነ ነው ይላሉ።

በሒሳብ ስሌት ውስጥ የሚዘለል ነጥብ የለም። ሒሳብን ለመረዳት እያንዳንዱን የስሌት ቀምር ማወቅ ያስፈልጋል።

ፕ/ር ዩሊያ እንደሚናገሩት፤ በተለያዩ አገራት የ15 ዓመት ታዳጊዎችን የሒሳብ ክህሎት ለመመዘን እአአ በ2000 የተዘረጋ መርሃ ግብር ነበር።

ከፍተኛ ውጤት ያመጡት ቻይናውያን ተማሪዎች እንደሆኑ ያስታውሳሉ።

የምሥራቅ እስያ እና የፊንላንድ ተማሪዎች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

በጂያንግዢ ኖርማል ዩኒቨርስቲ አስተማሪ የሆኔት ዤንዤን ማዎ እንደሚሉት በቻይና የሒሳብ ትምህርት መሠረታዊ እውቀት ላይ ያተኩራል።

"መሠረታዊ እውቀት፣ መሠረታዊ ክህሎትና መሠረታዊ የሒሳብ ምልከታ ላይ እናተኩራለን" ይላሉ።

በቻይና መምህራን በአንድ ቀን ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ክፍል ብቻ ስለሚያስተምሩ በትኩረት ትምህርት ይሰጣሉ። ክትትልም ያደርጋሉ።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቱርኩ የሚያስተምሩት ፕ/ር ፔካ ራሳና እንደሚሉት በፊንላንድ ያለው የሒሳብ ትምህርትም ልክ እንደ ቻይና መሠረታዊ እውቀት ላይ ያተኩራል።

መምህራን ለአምስት ዓመት ይሠለጥናሉ። መምህራን በማኅበረሰቡ ዘንድም ይከበራሉ። ሆኖም ሁሉም ተማሪ ሒሳብ ጎበዝ ነው ማለት አይደለም።