የሕጻንነት ጊዜያችንን ማስታወስ ለምን ያዳግተናል?

ፈገግ ያለ ሕጻን ልጅ

የተወለድንበት ቀን፤ የመጀመሪያዎቹ ቆመን የተራመድንበት ቅጽበት፣ መጀመሪያ ያውጣናቸውን ቃላት በሕይወታችን ውስጥ ወሳኝ አጋጣሚዎች ናቸው። ሆኖም አንዳቸውንም አናስታውስም። ለምን?

የሳይንቲስቶች እና የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሲታገሉ ቆይተዋል።

ከመጀመሪያዎቹ የሕይወታችንን ዓመታት የተወሰኑትን ክስተቶችን ማስታወስ አለመቻላችን 'ኢንፋንታይል አምኔሲያ' ተብሎ ይጠራል። ይህን ለማብራራት ለዓመታት ንድፈ ሐሳቦች ተዘጋጅተዋል።

በአሜሪካ የዬል ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቡና እና የነርቭ ቀዶ ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ኒክ ተርክ-ብራውን ክርክሩ ሁለት ቁልፍ ጥያቄዎችን ያቀፈ ነው ይላሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ ትውስታዎች የሚኖረን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሆኖ በኋላ ላይ ማስታወስ አንችልም ወይንስ እስክናድግ ድረስ ምንም ዓይነት ትውስታ አንፈጥርም? የሚሉ ናቸው ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ተርክ ብራውን ገለጻ ከሆነ እስካለፉት አስርት ዓመታት መጨረሻ ድረስ ተመራማሪዎች በዋነኛነት ሕጻናት ትውስታ መፍጠር አይችሉም ብለው ይገምቱ ነበር።

አንዳንዶች እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በራስ የመተማመን ስሜት ወይም የመናገር ችሎታ ባለማግኘታቸው መሆኑን ነበር።

ሌላው መላ ምት ደግሞ አራት ዓመት ገደማ እስኪሆነን ድረስ ትዝታን መፍጠር አንችልም። ምክንያቱም ሂፖካምፐስ የተባለው እና አዲስ ትውስታዎችን ለማስቀመጥ ኃላፊነት ያለው የአንጎል ክፍል ሙሉ በሙሉ ስላልዳበረ ነው።

"በጨቅላነት ጊዜ መጠኑ ከእጥፍ በላይ ይጨምራል። ምናልባትም እኛ ያለን ትውስታዎች ሊቀመጡ አይችሉም ምክንያቱም ያንን ለማድረግ አስፈላጊው ክፍል ስለሌለን" ብለዋል።

አንጎልን የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library via Getty Images

የሕፃን አእምሮን መመልከት

ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በፕሮፌሰር ተርክ ብራውን የታተመ ጥናት ይህንን የራሳቸውን ሃሳብ የሚቃረን ይመስላል።

የጥናት ቡድናቸው ከአራት ወር እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸው 26 ሕጻናትን ምስሎችን በማሳየት አእምሯቸውን መመልከት (ስካን ማድረግ) ችሏል።

ቀጥሎም ለሕፃናቱ ቀድመው ካዩዋቸው ምስሎች አንዱን ከአዲሱ ምስል ጋር በማሳየት የሕጻናቱ ዓይን ወደየትኛው ምስል የበለጠ እንደሚመለከት ለማወቅ ችለዋል።

ሕጻናቱ የሚመለከቱት የቀደመውን ምስል ከሆነ ሕጻናቱ ምስሉን ለማስታወስ እና ለመለየት መቻላቸውን ለማወቅ ነበር። ተመሳሳይ የጥናት መንገዶች ቀደም ብለው ተግባራዊ ሆነዋል።

የሕጻናቱ ሂፖካምፐስ የበለጠ ንቁ ሆኖ ሲገኝ ምስልን ለመጀመሪያ ጊዜ ካዩ በኋላ ላይ የማስታወስ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተማራማሪዎቹ አሳውቀዋል። ይህ የሚሆነው በተለይ ሕጻኑ ከ12 ወር በላይ ሲሆነው ነው።

ይህ የሚያሳየው ሂፖካምፐስ ሕጻናት አንድ ዓመት ገደማ ሲሞላቸው አንድ ዓይነት የማስታወስ ችሎታን መመስረት መቻሉን ነው።

ፈገግ ያለ ሕጻን

የፎቶው ባለመብት, KDP via Getty Images

ትውስታዎቹ የት ጠፉ?

ፕሮፌሰር ተርክ ብራውን እንዳሉት የጥናት ቡድናቸው ሕጻናት በሂፖካምፐስ ውስጥ ትዝታ እየፈጠሩ መሆኑን ለማረጋገጥ "የመጀመሪያው እርምጃ" ነው። ሆኖም አሁንም ብዙ ተጨማሪ ምርምር ሥራዎች ያስፈልጋሉ።

"ትዝታዎቹን እያከማቸናቸው ከሆነ፤ አሁን የት ናቸው የሚል አስገራሚ ጥያቄ ያስነሳል? አሁንስ አሉ? ልንደርስባቸውስ እንችላለን?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

እአአ በ 2023 የታተመ ጥናት እንዳመለከተው በጨቅላነታቸው ከውስብስብ ስፍራ መውጣት የተማሩ አይጦች ይህንን ችሎታቸውን በአዋቂነታቸው ወቅት ረስተውታል። በመጀመሪያው ስልጠና ለተሳተፉት የሂፖካምፐስ ክፍላቸውን በሰው ሠራሽ መንገድ በማንቃት ያንን ትውስታ መመለስ ይችላል።

ሕጻናት ትውስታ ፈጥረው በኋለኛው ሕይወታቸው ዘመን ደብዝዞ እንደሆነ ግን አልታወቀም።

በዩናይትድ ኪንግደም በዌስትሚኒስተር ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሳይኮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ካትሪን ላቭዴይ ጨቅላ ሕፃናት ቢያንስ በሚናገሩበት ጊዜ ትውስታዎችን የመፍጠር ችሎታ እንዳላቸው ያምናሉ።

"ልጆች ከመዋዕለ ሕፃናት ሲመለሱ የሚነግሩን ነገር አለ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ያንን መግለጽ አይችሉም። ስለዚህ ትውስታዎች ቢኖሩም አብረው አይቀጥሉም" ሲሉ ይከራከራሉ።

"ጥያቄው እነዚያን ትዝታዎች በጊዜ ሂደት ምን ያህል እናጣቸዋለን፣ በጣም በፍጥነት እየደበዘዙ እንደሆነ እና እስከ ምን ድረስ በትክክል እነሱን ማሰላሰል እና ስለእነርሱ ማሰብ የምንችልባቸው የንቃተ ህሊና ትውስታዎች ይኖሩናል የሚለው ነው" ብለዋል።

በሕጻናት ላይ ምርምር ሲከናወን

የፎቶው ባለመብት, 160/90

የውሸት ትውስታ ሊሆን ይችላልን?

ስለሕጻናት ትውስታ ያለንን ግንዛቤ ይበልጥ የሚያወሳስበው ሌላኛው ጉዳይ ሰዎች የመጀመሪያ ትዝታቸን ነው ብለው የሚያስቡት ነገር በትክክልም የቀዳሚው መሆኑን ለማረጋገጥ "ከሞላ ጎደል የማይቻል" ሊሆን ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰር ላቭዴይ።

አንዳንዶቻችን ለምሳሌ ሕጻን ወይም አልጋ ላይ ሳለን አንድ የተወሰነ ክስተትን እናስታውስ ይሆናል።

ፕሮፌሰር ላቭዴይ እንዲህ ያሉት ትውስታዎች የእውነተኛ ተሞክሮዎች ትዝታዎች ሊሆኑ አይችሉም ይላሉ።

"የማስታወስ ችሎታ ሁሌም የሚታደስ ነው። አንድ ሰው የሆነ ነገር ቢነግርህ እና ስለእሱ በቂ መረጃ ካገኘህ አእምሮህ እውነት ነው ብሎ የሚሰማውን ነገር እንደገና መገንባት ይችላል" ብለዋል።

"በእርግጥ እየተመለከትን ያለነው ንቃተ ህሊና ነው። ንቃተ ህሊናን ለመለካት አስቸጋሪ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ፕሮፌሰር ተርክ ብራውን በበኩላቸው በጨቅላ ሕጻናት የመርሳት ችግር ዙሪያ ያለው ምሥጢር ስለ እኛ ማንነት የሚናገረውን ነው ብለው ያስባሉ።

"ስለ ማንነታችን ነው። በሕይወታችን የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነገሮችን የማናስታውስበት ጊዜ አለ የሚለው ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸውን አስተሳሰብ በእውነት የሚፈታተን ይመስለኛል" ብለዋል።

ሳይክል የሚያሽከረክር ልጅ

የፎቶው ባለመብት, ullstein bild via Getty Images