ወላጆች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩት ዘላቂ ጫና

ወላጆች በሚጨቃጨቁበት ቤት ውስጥ ያለእስያዊ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ወላጆቼ ያስጨንቁኝ ነበር። በየቀኑ በሚባል ደረጃ አለቅስ ነበር። በዚህ ምክንያት ችላ እላቸው ጀመር” ይህንን ከሴት ልጅ መስማት የተለመደ አይደለም።

ሳሪካ ግን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው ለዓመታት “መጥፎ ባህሪ” ከነበራቸው ወላጆቿ ጋር የነበራት ግንኙነት በአእምሮዋ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባት በኋላ መሆኑን ትናገራለች።

“በተለይ በእርግዝናዬ ወራት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። ያልተወለደው ልጄም ለቅሶዬን ሰምቶ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ” ስትል የማሌዢያ ነዋሪ የሆነችው የ30 ዓመቷ ወጣት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሳሪካ ከወላጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ገድባለች። ከእናት እና ከአባቷ ራሷን ለማራቅ መወሰኗ ግን ቀላል አልነበረም።

“ሁሌም የጥፋተኝነት ስሜቱ እንዳለ ነው” ትላለች።

ሳሪካ ብቻ አይደለችም እንዲህ ዓይነት ታሪክ ያላት።

“አባቴን በእርግጠኝነት ራስ ወዳድ ብዬ ልገልጸው እችላለሁ። ክፉኛ የበላይነት የተጠናወተው ተቆጣጣሪ ነው። ትምህርት ቤት ተገኝቶልኝ አያውቅም። ለምርቃቴ ጭምር አልተገኘም። ሁልጊዜ ምክንያት ነበረው” ስትል ኬንያዊዋ አሽሊ ትናግራለች።

የ25 ዓመቷ ወጣት እንደገለጸችው ከሆነ አባቷ ከጎኗ ባይኖርም፤ ሁልጊዜ በሚባል ደረጃ ግን ስለ እርሷ ያማርራል።

“ከመርዛማ ባህሪው እንድጠበቅ የረዳችኝ እናቴ ነች። ከክፉ ባህሪው የምትችለውን ነገር ሁሉ አድርጋ ጠብቃኛለች” ስትል አሽሊ ለቢቢሲ ተናግራለች።

አክላም “ትዳራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ያበቃለት ቢሆንም እናቴ ግን ሁሉን ችላ አብራው ኖራለች። ትዳርን መፍታት እንደ ምዕራባውያኑ በአፍሪካ አገራት ቀላል አይደለም” ስትል ታክላለች።

“አሁን ላይ የሆነ ነገር እንድገዛለት ሲፈልግ ይደውልና ሥራ አግኝቼ እንደሆነ ይጠይቀኛል።”

አፍሪካዊት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኬንያዊቷ አሽሊ እና ከማሌዢያ የሆነችው ሳሪካ፤ በሺህዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው ቢኖሩም ሁለቱም ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አላቸው።

እንደ ሁለቱ ሴቶች ገለጻ ወላጆቻቸውን በሚፈለጉበት ጊዜ አያገኟቸውም። ይሁን እንጂ ሊቆጣጠሯቸው ይሞክራሉ። በሙያዊ፣ በማኅበራዊ እና በፍቅር ሕይወታቸው ጣልቃ በመግባት ሊወስኑላቸው ይሞክራሉ።

ብዙልጆች ከወላጆቻቸው ጋር እንዴት ግንኙነታቸውን እንዳቋረጡ የሚገልጹ ቪዲዮዎችን በቲክ ቶክ እና በሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ያጋራሉ።

ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የማያቋርጥ የጥፋተኝነት ስሜት እና ፍርሃትን በፈጠረባቸው በወላጆቻቸው “በመጥፎ” ባህሪ ምክንያት ግንኙነት ማቋረጣቸውን ይገልጻሉ።

የብሪቲሽ የካውንስሊንግ እና ሳይኮቴራፒ ማኅበር (ቢኤሲፒ) አባል የሆኑት የሥነ አእምሮ ባለሙያዋ አዮ አዴስዮዬ “በክፉ ወላጆች ለሚደርስ ጉዳት የባለሙያ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል” ይላሉ።

መጥፎ ወላጅ ወይም በእንግሊዘኛው 'ቶክሲክ' ወላጅ የሚለው ቃል ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። ግን ምን ማለት ነው?

‘ክፉ’ ወይም ‘መጥፎ’ ወላጅ ምን ዓይነት ነው?

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ገለጻ አዎንታዊ የልጆች አስተዳደግ በሥነ ሥርዓት ላይ ወይም በአኗኗር ዘይቤ ላይ የተገደበ አይደለም።

አዎንታዊ አስተዳደግ እምነት ነው፤ የሕይወት መንገድም ነው።

“ልጆች በክብር መያዝ አለባቸው። ከጥቃት፣ ከውርደት እና ከፍርሃት ነፃ ሆነው በአክብሮት መያዝ አለባቸው። በፍቅር እየተበረታቱ ሊመሩ ይገባል” ይላል ዩኒሴፍ።

“ለክፉ” ወይም “ለመጥፎ” ወላጅነት ይፋዊ የሆነት ትርጉም ባይሰጠውም፤ “ከአዎንታዊ ወላጅነት” ተቃራኒ የሆኑ አሉታዊ ባህሪያትን ስብስብ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል።

የሥነ አእምሮ ባለሙያዋ አዮ አዴስዮዬ “አዎንታዊ ያልሆነ ባህሪ በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆን ክፉ ብለን እንሰይመዋለን።”

ለምሳሌ ልጅዎን ፍቅረኛ እንዳላት ወይም እንዳለው መጠየቅ በራሱ ችግር አይደለም። ይሁን እንጂ ጥያቄው የመቆጣጠር ወይም የማንጓጠጥ ስሜት ካለው ለልጅ ትልቅ አሉታዊ ትርጉም ይኖረዋል።

“አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ይህን የሚያደርጉት ሳያውቁ ነው። ምን እንደሚሠሩ ሳያውቁ፣ በራሳቸው ግንዛቤ፣ እውቀት እና ትምህርት ማነስ የሚያደርጉት ነው” በማለት አዴስዮዬ ያስረዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2013 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በልጅነታቸው ከፍ ያለ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች በአዋቂነታቸው ወቅት እንደ ከፍተኛ ኮሌስትሮል፣ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ ላሉ አንዳንድ የጤና አደጋዎችን የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

ደስተኛ እናትና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተቆጣጣሪነት፣ ራስ ወዳድነት እና ሌሎችም

አዴስዮዬ በምታማክርበት ወቅት ሁለቱ በብዛት ተደጋግመው የሚነሱ የመጥፎ ወላጅነት ባህሪያትን ትጠቅሳለች።

የመጀመሪያው ውስጥ የሚካተቱት በልጃቸው የትምህርት፣ የሥራ ሕይወት ወይም ፆታዊ ግንኙነት ምርጫዎች ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ተቆጣጣሪ ወላጆች ናቸው።

ሁለተኛዎቹ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጡት ለልጆቻቸው ሳይሆን ለራሳቸው ነው። እነዚህ ሁለት ዓይነት ባህሪያት ብዙውን ጊዜ ይደራረባሉ ብላለች።

ይሁን እንጂ የክፉ ወላጅ ዓይነቶች ዝርዝር በዚህ ብቻ የሚቆም አለመሆኑን መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ሳይኮሎጂስት አሊሰን ኮርነር ትገልጻለች።

ከዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ጡረታ ከወጣች በኋላ፣ የራሷን ድረ ገጽ (myhorridparent.com) አስተዋውቃለች። ይህም በክፉ ወላጆች ስር ያደጉ ልጆችን ለመምከር ያለመ ድረ ገጽ ነው።

እንደ እርሷ ከሆነ ከክፉ ወላጅ ዓይነቶች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡

  • ክፉኛ ተቆጣጣሪ እናቶች - ልጆችን ሳይጠይቁ ለልጆች ውሳኔዎችን የሚወስኑ
  • ተናዳጅ እናቶች - ልጆች ከሚያደርጉት እያንዳንዱ ነገር ስህተት የሚያወጡ እና ልጆቻቸው ስህተቱን እንዲያውቁት የሚያደርጉ
  • ምቀኛ እናቶች - በሕይወታቸው ውስጥ የሆነ ነገር የጎደላቸው እና ያጡትን ነገር በልጆቻቸው ውስጥ መኖር የሚፈልጉ
  • ተፎካካሪ አባቶች - ልጆች ከእነሱ የተሻለ ሲሠሩ ትችት የሚያበዙ መጥፎ የሚሆኑ እና ሁሉንም ነገር ሊተቹ የሚችሉ
  • ተናዳጅ አባቶች - ተቆጪ፣ ግልፍተኛ እና በትንሽ ነገር የሚናደዱ
  • ሚናቸውን አሳልፈው የሚሰጡ አባቶች - እያንዳንዱን ውሳኔ እና ኃላፊነት ለእናቶች የሚተዉ

አሊሰን ኮርነር እንደምትለው ከሆነ ከዓለም ዙሪያ የምታገኛቸውን “ልብ የሚሰብሩ እና አሳዛኝ ታሪኮችን” በማዳመጥ አስፈላጊ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሆኑ ውሳኔዎችን ለመወሰን ጭምር እርዳታ በመስጠት ተጎጂዎችን ትረዳለች።

“ይህን ያህል መጥፎ ሊሆን ይችላል” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ማህበራዊ ሚዲያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በባህል የተከለከለ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሳሪካ ስለ ጉዳዩ ከቤተሰቦቿ የቅርብ ወዳጅ ከሆነ ከሦስተኛ ሰው ጋር ለመነጋገር ሞክራ ነበር።

“አንዲህ ነሽ፣ እንዲያ ነሽ በሚል ፍርድ የማይሰጥ” ሰው ጋር በጉዳዩ ለማውራት ያደረገችው ጥረት ካለመሳካቱም በላይ ሁሉም ጥፋተኛ አደረጓት።

“ባህላችን ልጆች የተሳሳቱ እንደሆኑ እንድናስብ አድርጎናል። ወላጆች ደግሞ ሁልጊዜም ትክክል ናቸው። ሰዎች ብዙውን ጊዜ እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም ይላሉ" ስትል አክላለች።

በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ምሑሩ ፕሮፌሰር ቼሪስ ሹን ቺንግ ቻን በበኩላቸው የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለክስተቱ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል።

ለምሳሌ ቻይና ስትተገብረው የነበረው የአንድ ልጅ ፖሊሲ አብዛኞቹ ወላጆች አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልዱ ይገደብ ነበር። ይህ ደግሞ ወላጆቻቸው የእኔ የሚሉት ሌላ ሰው እንዳይኖራቸው በማድረግ በልጆች ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል።

“ወላጆቻቸው ብዙ መስዋዕትነት ስለከፈሉ ወይም ሁሉንም ነገር ስላደረጉላቸው ልጆቹ ወላጆቻቸው የሚጠብቁትን ነገር ለማሟላት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገባሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይም ወላጆች ትዳራቸው የፈረሰ ከሆነ ወይም አባት ከጋብቻ ውጪ የሆነ ግንኙነት ካለው ብዙ ወላጆች ከልጆች ስሜታዊ ድጋፍን ይፈልጋሉ ሲሉ ፕሮፌሰር ቻን ያስረዳሉ።

“ይህ የክፉ የወላጅነት ዓይነት ነው ብዬ አስባለሁ። ልጆችም ስለጉዳዩ በግልጽ መናገር የበለጠ ከባድ ይሆንባቸዋል። በእነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንድ ልጆች ለእናቶቻቸው እንደ አማካሪ ይሆናሉ” ብለዋል።

እንደ አዮ አዴስዮዬ ገለጻ በዚህ ዓይነት መልኩ ያደጉ አዋቂ ታካሚዎቿ ላይ ከሚታዩት የረዥም ጊዜ ተጽዕኖዎች መካከል አንዳንዶቹ ለራስ ክብር መስጠት፣ ሥር የሰደደ ውርደት፣ ራስን መተቸት እና ራስን አለመቻል፣ ያለማቋረጥ ሰዎችን ለማስደሰት መሞከር፤ እርዳታ ለመጠየቅ መቸገር እና በፍቅር ግንኙነቶች ውስጥ ደኅንነት ያለመሰማት ናቸው።

የተጨነቀች ሴት በስልክ ስታወራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመጥፎ ወላጅነትን ጫና እንዴት መቋቋም ይቻላል

ሳሪካ ከጋብቻዋ በኋላ ከወላጆቿ ጋር የነበራት ግንኙነት በጣም ተበላሸ። ለዚህ ምክንያት የሆነው የመሠረተችው ትዳር ወላጆቿ ያልተቀበሉት በመሆኑ ነው ትላለች።

“ወላጆቼ ሁሉንም ነገር አድርገውልኛል። እኔ ምንም አላደረኩላቸውም። አባቴ ደጋግሞ 'ቤተሰብሽን አዋርደሻል’ ይለኛል። ምናልባትም ተሳስቻለሁ ብዬ አስቤ የነበረበት ወቅት ነበር” ስትል አክላ ተናግራለች።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ላሉ ሕጻናት እና ወጣቶች የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚያደርገው የኢኖቬቲንግ ማይንድ መሥራች የሆኑት ዶ/ር አሻ ፓቴል እንደገለጹት ከሆነ ልጆች ክፉ ወላጆች እንዳላቸው አምነው መቀበላቸው ትክክል ቢሆንም፤ የራስን ደኅንነት ማስቀደም ግን ወሳኝ ነው።

“የእናንተን የአእምሮ ጤንነት ማንም አይጠብቅም” ሲሉ አክለዋል።

“ይህንን ማድረግ የሚችለው ግለሰቡ ብቻ ነው።”

አዮ አዴስዮዬ እንዳሉት ከወላጆች ጋር አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ ሳይገቡ ልጆቻቸው ሕጻን እንዳልሆኑ ለራሳቸው እውቅና በመስጠት ጥብቅ ድንበር ማበጀት አለባቸው።

“የሚቀረው ነገር ይህ ይመስለኛል። ይህንን በሥራዬ ወቅት ብዙ አይቻለሁ። ወደ ልጅነት ተመልሰህ ትልቅ ሰው መሆንህን ትረሳለህ።”

አሽሊ ይህንን ምክር ተከትላ ለአእምሮ ደኅንነቷ ቅድሚያ በመስጠት ከአባቷ ጋር ግልጽ የሆነ ድንበር ማስመርን መርጣለች። ሳሪካ አሁን አዲስ ለወለደቻት ሴት ልጇ ጥሩ ወላጅ ለመሆን ቆርጣለች።

“እንደ ወላጆቼ መሆን አልፈልግም። እሷን ልረዳት፣ ምርጡን ነገር ሁሉ ልሰጣት እና በሕይወቷ ላይ እንድትወስን እፈቅድላታለሁ” ብላለች።