ሳይንቲስቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው ልጅ ቆዳ ዲኤንኤ ፅንስ ፈጠሩ

የፎቶው ባለመብት, OHSU/Christine Torres Hicks
የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው የቆዳ ሴል የተወሰደ ዲኤንኤን ተጠቅመው ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር በማዳቀል ፅንስ መፍጠራቸውን ገለጹ።
አዲሱ ግኝት በእርጅና ወይም በበሽታ ምክንያት የሚከሰት መካንነትን ለማስቀርት የሚችል ነው ተብሏል።
ይህም በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ህዋሶች በመጠቀም መሥራት እንደሚቻል ተነግሯል።
ዘዴው ከፍተኛ የሆነ ማሻሻያ የሚፈልግ በመሆኑ በሕክምና ተቋማት ጥቅም ላይ ለመዋል አስር ዓመት ሊወስድ ይችላል።
ባለሙያዎች ይህ አስደናቂ እመርታ ነው ቢሉም፣ ሳይንሱ ምን እየሠራ እንደሆነ ከሕዝብ ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።
የሰው ልጅ የሚጸነሰው የወንድ የዘር ፍሬ ከሴቷ እንቁላል ጋር በሚገናኝበት ወቅት ነው።
ፅንስ ለመፍጠር ተዋህደው ከዘጠኝ ወራት በኋላ ልጅ ይወለዳል።
አሁን ላይ ሳይንቲስቶች ይህንን አካሄድ እየቀየሩ ነው። አዲሱ ሙከራ የሚጀምረው በሰው ቆዳ ነው።
የኦሪገን ጤና እና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት ሰውነትን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን የጄኔቲክ ኮድ ቅጂ የያዘውን ኒውክለስን ከቆዳ ሕዋስ ውስጥ ወስደዋል።
ይህም የጄኔቲክ መመሪያው በተወገደው የለጋሽ እንቁላል ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል።
እአአ በ1996 በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ዶሊ የተሰኘውን በግ ለመፍጠር ጥቅም ላይ የዋለውን ክሎኒንግ የተሰኘውን ቴክኒክ ተግበራዊ በማድርግ የሚከናወን ነው።

የፎቶው ባለመብት, OHSU
ይሁን እንጂ ይህ እንቁላል ቀደም ሲል ሙሉ የክሮሞዞም ስብስብ ስላለው በወንዱ የዘር ፍሬ ለመራባት ዝግጁ አይሆንም።
ከእያንዳንዱ ወላጆች 23ቱን የዲኤንኤ ጥቅሎች በድምሩ 46 የሚወረስ ሲሆን ይህንን ደግሞ እንቁላሉ አስቀድሞ የሚይዘው ነው።
ስለዚህ ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነው እንቁላሉ ግማሹን ክሮሞዞም እንዲያስወግድ ማድረግ ነው። ተመራማሪዎቹ ሂደቱን "ሚቶሜይዮስስ" ሲሉ ሰይመውታል (ቃሉ ሚቶሲስ እና ሚዮሲስ ከሚባሉ እና ሴሎች የሚከፋፈሉባቸው ሁለት መንገዶች የሚያሳዩ ናቸው)።
ኔቸር ኮሙኒኬሽንስ በተባለው መጽሔት ላይ የታተመው ጥናቱ 82 ዝግጁ የሆኑ እንቁላሎች መሠራታቸውን ያሳያል። እነዚህም በወንድ ዘር ፍሬ የዳበሩ ሲሆን አንዳንዶቹም ወደ ፅንስ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከስድስት ቀን በላይ የተዘጋጁ ግን አልነበሩም።
የኦሪገን ጤና እና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የፅንስ ሴል እና የጂን ሕክምና ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሹክራት ሚታሊፖቭ "የማይቻል ነው ተብሎ የሚታሰበውን ነገር አሳክተናል" ብለዋል።
እንቁላሉ በዘፈቀደ የትኛውን ክሮሞዞም እንደሚጥል የሚመርጥ በመሆኑ ቴክኒኩ ዝግጁ ነው ለማለት አይቻልም። በሽታን ለመከላከል ከሚረዱት ከ23 ዓይነቶች ውስጥ አንዱን መያዝ ያስፈልገዋል። ነገር ግን አንዳንዴ ከሁለቱ መካከል ሁለቱን ወይንም ምንም ላይኖረው ይችላል።
ደካማ የስኬት መጠን (9 በመቶ) ያለው ሲሆን ክሮሞዞምቹ ዲኤንኤቸውን እንደገና የሚያደራጁበትን አስፈላጊ ሂደት ያመጣሉ።
በዘርፉ ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን ያተረፉት ፕሮፌሰር ሚታሊፖቭ "ሂደቱን ፍጹም ማድረግ አለብን" ብለዋል።
"እኔ እንደማስበው ከሆነ መጪው ጊዜ ወደዚያ የሚሄድ ይመስለኛል። ምክንያቱም ልጅ መውለድ የማይችሉ ታካሚዎች እየበዙ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, OHSU/Christine Torres Hicks
ይህ ቴክኖሎጂ ኢንቪትሮ ጌምቶጄኔሲስ በመባል የሚታወቀው እና ከሰውነት ውጭ የወንድ የዘር ፍሬ እና እንቁላል ለማምረት የሚደረግ የጥናት መስክ አካል ነው።
ሂደቱ ገና በሳይንሳዊ ምርመራ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ዓላማው ደግሞ የሚጠቀሙበት የወንዴ ዘር ወይም እንቁላል የሌላቸው ጥንዶች አይቪኤፍ (ኢን ቪትሮ ፈርትላይዜሽን) መጠቀም ስለማይችሉ እነሱን ለመርዳት ነው።
ምርምሩ እንቁላል የሌላቸው በዕድሜ የገፉ ሴቶችን፤ በቂ የወንድ የዘር ፍሬ የማያገኙ ወንዶች ወይም የካንሰር ሕክምና መካን ያደረጋቸውን ሰዎች ሊረዳቸው ይችላል።
ምርምሩ ለወላጅነት ምንነት አዲስ ትርጓሜ የሚያሰጠው ይሆናል ተብሏል። ይፋ የሆነው ዘዴ የሴትን የቆዳ ሴሎች መጠቀም የለበትም። የወንድንም መጠቀም ይችላል።
ይህም የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ከሁለቱም አጋሮች ጋር በዘረመል ግንኙነት ያላቸው ልጆች እንዲወልዱ በር ይከፍታል። ለምሳሌ የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶቹ ወንዶች ከሆኑ የአንደኛው ወንድ ቆዳ እንቁላሉን ለመሥራት ሊያገለግል ይችላል። ቀጥሎም ከወንድ አጋሩ የወንድ የዘር ፍሬ ጋር ይጠቀሙበታል።
የኦሪገን ጤና እና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባዋ ፕሮፌሰር ፓውላ አማቶ "ይህ ዘዴ በእንቁላል ወይም በወንድ ዘር እጥረት ምክንያት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት መካን ለሆኑ ሰዎች ተስፋ ከመስጠቱ በተጨማሪ የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ከሁለቱም ጋር በዘር የሚተሳሰር ልጅ እንዲወልዱ ያስችላል" ብለዋል።
የኅብረተሰብ አመኔታን መገንባት
በሃል ዩኒቨርሲቲ የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ሮጀር ስቱርሚ ምርምሩን "ጠቃሚ" እና "አስደሳች" ነው ብለው ገልጸውታል።
"በተመሳሳይ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ምርምር በተመለከተ ከሕዝብ ጋር ቀጣይነት ያለው ግልጽ ውይይት አስፈላጊነት እንዲኖር ይፈልጋል" ሲሉ አክለዋል።
"እንዲህ ባሉት ምርምሮች ዙሪያ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና የህዝብ አመኔታን ለመፍጠር የተጠናከረ የቁጥጥር አስፈላጊነትን ያሳዩናል።"
በኤድንበርግ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ተዋልዶ ጤና ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሪቻርድ አንደርሰን በበኩላቸው አዳዲስ እንቁላሎችን ማፍራት መቻል "ትልቅ ለውጥ ነው" ብለዋል።
"በጣም አስፈላጊ የደህንነት ስጋቶች ቢኖሩም ግን ይህ ጥናት ብዙ ሴቶች ከራሳቸው ዘረመል ልጆች እንዲኖራቸው ለመርዳት የሚያግዝ እርምጃ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።















