ከታማሚዎች ጸጉር የሚሰራ የጥርስ ሳሙና ጥርስን ለማከም ሊውል እንደሚችል ተመራማሪዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, King’s College London
የጥርስ ሕመም ካለባቸው ሰዎች ጸጉር የተሰራ የጥርስ ሳሙና የተበላሹ ጥርሶችን ለመጠገን እና ለመከላከል እንደሚረዳ ተመራማሪዎች ገለጹ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ኪንግስ ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪዎች በፀጉር፣ በቆዳ እንዲሁም እንደ በግ ባሉ እንስሳት ጸጉር ውስጥ የሚገኘው ኬራቲን የተባለ ፕሮቲን የጥርስ ሽፋን እንዲጠገን እና የጥርስ መበስበስን እንዲቆም እንደሚያደርግ ደርሰውበታል።
የኬራቲን ንጥረ ነገር በምራቅ ውስጥ ከሚገኙት ማዕድናት ጋር በሚገናኝበት ጊዜ የተፈጥሯዊውን የላይኛው ጥርስ ክፍል አወቃቀር እና ተግባርን በመኮረጅ ጥርስን የሚከላከል መዋቅር እንደሚፈጥር ጥናታቸው አሳይቷል።
በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የፒኤችዲ ተመራማሪ እና የጥናቱ የመጀመሪያ ጸሐፊ የሆኑት ሳራ ጋሜያ "ኬራቲን አሁን ጥቅም ላይ ለሚውሉ የጥርስ ሕክምናዎች ሌላ አማራጭ ይሰጣል" ብለዋል።
ተመራማሪዋ፤ "ይህ ቴክኖሎጂ በባዮሎጂ እና በጥርስ ሕክምና መካከል ያለውን ልዩነት በመቀነስ ተፈጥሯዊ ሂደቶችን የሚያንጸባርቅ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ ባዮማትሪያል ያቀርባል" ሲሉም አክለዋል።
"እንደ ጸጉር እና ቆዳ ካሉ ስነ ሕይወታዊ ውጋጆች በዘላቂነት የሚገኝ ከመሆኑም በላይ፤ በተለምዶ በጥርስ ሕክምና ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ መርዛማ እና ዘላቂ ያልሆኑ የፕላስቲክ ሙሌቶችን ያስወግዳል" ሲሉም በስራ ላይ ካለው የሕክምና ዘዴ የሚለይበትንም ምክንያት አስረድተዋል።
ተመራማሪዎቹ 'አድቫንስድ ኸልዝ ኬር ማቴሪያል' በተባለው ፎረም ላይ በታተመው ጥናታቸው እንዳመለከቱት በምርምሩ ወቅት ከበግ ጸጉር ላይ ኬራቲንን አውጥተዋል።
ኬራቲን በጥርስ ወለል ላይ ሲለጠፍ እና በምራቅ ውስጥ በተፈጥሮ ከሚገኙት ማዕድናት ጋር ሲገናኝ የተደራጀ እና ክሪስታል መሰል መዋቅር የሚፈጥር ሲሆን፣ ይህ መዋቅርን ተፈጥሯዊውን የጥርስ የላይኛው ክፍል አወቃቀር እና ተግባርን የሚያስመስል ነው።

የፎቶው ባለመብት, King’s College London
ተመራማሪዎች እንደገለጹት ከሆነ የሚፈጠረው መዋቅር ከጊዜ በኋላ የካልሲየም እና የፎስፌት አዮኖችን መሳብ ይቀጥላል፤ ይህም ጥርሱን የሚከላከል ሽፋን እንዲፈጠር ያደርጋል።
አሲዳማ ምግቦች እና መጠጦች፣ ደካማ የአፍ ንጽህና እንዲሁም እርጅና የጥርስ የላይኛው ክፍል እንዲበላሽ እና እንዲበሰብስ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ይህም የጥርስ ስሱ መሆንን፣ሕመም መፈጠርን እና በመጨረሻም የጥርስ መውለቅን ያስከትላል።
በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን ከፍተኛ ጸሀፊ እና የፕሮስቶዶንቲክስ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ሸሪፍ ኤልሻርካዊ፤ "ከአጥንት እና ከፀጉር ተቃራኒ በሆነ መልኩ የጥርስ የላይኛው ክፍል መልሶ አይፈጠርም፤ አንዴ ከጠፋ እስከመጨረሻው ሄደ ማለት ነው" ብለዋል።
አሁን የተገኙ "የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶች የበሽታውን ምልክቶች ከማከም ባሻገር የራሱ ሰውነትን አካል በመጠቀም ባዮሎጂያዊ ተግባራት እንድናስተካክል የሚያደርገን አስደሳች ዘመን እየመጣ ነው" ሲሉም አዲሱን ግኝት ገልጸዋል።
"በቀጣይ ስራዎች እና በትክክለኛው የኢንዱስትሪ አጋርነት በቅርቡ እንደ ጸጉር መቁረጥ ካለው ቀላል ነገር ጠንካራ እና ጤናማ ፈገግታዎችን ልንፈጥር እንችላለን" ሲሉም ተስፋቸውን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, King’s College London















