ከመገልገያ እቃዎች ወደ ሰውነታችን የሚገቡት ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣቶች በጤናችን ላይ የደቀኑት አደጋ

በሆዱ ተኝቶ በፕላስቲክ የተቀመጠ አበባን የሚመለከት ሰው

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

ጥቃቅን ፕላስቲኮች (ማይክሮ ፕላስቲክስ) በአጥንታችን ውስጥ ሳይቀር ተገኝተዋል።

ነገር ግን ግን በጤናችን ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራሉ? በሰውነታችን ላይ ስለሚያደርጉት ነገር የምናውቀው ነገር ምንድን ነው?

ከለንደን በስተሰሜን በሄርትፎርድሻየር በሚገኝ ስፍራ በዓለም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ የግብርና ምርምር እና ሙከራ ማዕከል ይገኛል።

በቪክቶሪያ መኳንንት እና ባላባት ጆን ቤኔት ሎውስ የተጀመረው፣ በኋላም ለዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያዎች ፈር ቀዳጅ የሆነው ይህ ግለሰብ የመጀመሪያ ዓላማው የስንዴ ምርትን ለማሳደግ የተለያዩ ሀሳቦችን መሞከር ነበር።

ነገር ግን ያለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እገዛ መረጃን ለማከማቸት ብቸኛው መንገድ የደረቀ የስንዴ ዘርን፣ ገለባን እና የአፈር ናሙናዎችን ከማሳ ላይ ሰብስቦ በጠርሙስ ማሸግ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1843 ሲጀመር፣ ሎውስ ይህ የምርምር ባህል ለ182 ዓመታት እንደሚቆይ ቅንጣት ታክል ሀሳብ አልነበረውም።

ይህም አስደናቂ የናሙናዎች ስብስብ ፈጠረ።

አሁን በሃርፐንደን በሚገኘው በሮተምስታድ የምርምር ተቋም ውስጥ የተቀመጠው ስብስቡ፣ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ በምድሪቱ ላይ ያመጣውን ብዙ ለውጦችን ያሳያል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንዲ ማክዶናልድ የአሁን የሮተምስተድ ምርምር ማኅደር ጠባቂ እና ባልደረባዎቹ ፍቅራቸውን ለመግለጽ "ጠርሙስ ጠባቂ" ሲሉ በቅጽል ስም ይጠሩታል።

በ1940ዎቹ እና 50ዎቹ ውስጥ የተሰበሰቡ ናሙናዎች ራዲዮአክቲቭ አሻራዎችን የሚገኝባቸው ነበሩ።

ይህም በዘመኑ የነበረውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ የሚያንፀባርቅ ነው።

ነገር ግን በእነዚህ በጥንታዊ አፈር በተሞሉ ጠርሙሶች ውስጥ ሌላ ያልታሰበ መረጃ ተገኘ። የመጀመሪያው የጥቃቅንፕላስቲኮች (microplastics) ቅንጣት በአፈር ውስጥ ተገኘ።

አንድ ግምት በዓመት እስከ 52,000 ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ልንጠቀም እንችላለን።

ምንም እንኳ ትክክለኛው አሃዝን ለመናገር አዳጋች ቢሆንም፣ በከፍተኛ መጠን ወደ አካላችን እየገቡ መሆኑ ግልጽ ነው።

በምንመገበው፣ በምንጠጣው፣ ወይም ከምንተነፍሰው አየር ውስጥ ጥቃቅን ፕላስቲኮች በሁሉም ቦታ ይገኛሉ።

ከሰውነት ፈሳሾች ከምራቅ እና ከደም እስከ አክታ እና የጡት ወተት፣ ጉበት፣ ኩላሊት፣ ጣፊያ፣ አንጎል እና አጥንታችን ውስጥ ይገኛሉ።

እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች አንድ ጥያቄን ያጭራሉ፤ ይህ ሁሉ ፕላስቲክ በጤናችን ላይ ምን እያደረገ ነው?

በሮታምስቴድ የምርምር ተቋም ውስጥ በተቀመጡት ናሙናዎች ውስጥ፣ ማክዶናልድ የፕላስቲክ ዘመን ከመጀመሩ በፊት እና በኋላ ግልጽ የሆነ የመለያ መስመር እንዳለ ተናግሯል።

"በሕብረተሰቡ ዘንድ በ1920ዎቹ አካባቢ ፕላስቲኮች በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ትልቅ ጭማሪን እናያለን" ብሏል።

"አንዳንዶች በከባቢ አየር ክምችት አማካኝነት ወደ አፈር ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ነው፤ እና ጥቃቅን ፕላስቲኮች ከትራክተር ጎማዎች ላይ እየተቀረፉ ከአፈር ጋር መዋሃዳቸውንም መገመትም ትችላላችሁ።"

የልብ እና የሳምባ ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሰዎች በታሪክ ከታዩት ጊዜያት ሁሉ በበለጠ ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ይመገባል፤ ይተነፍሳል ተብሎ ይታሰባል። በ2024 በታተመ ጥናት፣ ሳይንቲስቶች ከ1990 ጀምሮ የእነዚህ ቅንጣቶች ፍጆታ በስድስት እጥፍ ጨምሯል ይላሉ።

በተለይም በአሜሪካ፣ በቻይና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የተወሰኑ አካባቢዎች፣ በሰሜን አፍሪካ እና በስካንዲኔቪያ አገራት ይህ ቁጥር ከፍ ብሎ ተመዝግቧል።

ነገር ግን ጤንነታችንን እንዴት እንደሚጎዱ ማወቁ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል።

ይህንን ለማወቅ አንዱ መንገድ በሕክምና ክበቦች ውስጥ ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚከናወነው በተላላፊ በሽታዎች ላይ ነው።

ሳይንቲስቶች በሰው አካል ላይ ያለውን ተጽእኖ በተሻለ ሁኔታ ለመርዳት ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ሆን ብለው በበሽታ አምጪ ተሕዋስያን በማስያዝ እና በመከታተል የምርምር ሥራዎቻቸውን ያከናውናሉ።

ስለዚህም በ2025 መጀመሪያ ላይ፣ ስምንት በጎ ፈቃደኞች በማዕከላዊ ለንደን ውስጥ ወደሚገኝ ቤተ ሙከራ ገቡ።

ምንም እንኳ አነስተኛ እና ትንሽ ክፍያ የሚሰጣቸው ቢሆንም በሙሉ ፈቃደኝነት ጥቃቅን የፕላስቲክ ቅንጣቶችን የያዘ ፈሳሽ ጠጡ።

በሚንዴሮ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ይህ ልዩ ጥናት፣ በአነስተኛ ጥቃቅን ላይ በዚህ ሁኔታ የተደረገ የመጀመሪያ ጥናት ተደርጎ መወሰድ የሚችል ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ውጤቱ ይፋ አልሆነም።

ምርምሩን በበላይነት የመሩት የኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪ ስቴፋኒ ራይት እንዳሉት፣ ጽንሰ ሃሳቡ ብዙዎቻችን ሳናውቅ ይህንን ትክክለኛ ሙከራ በየቀኑ በራሳችን አካል ላይ እያደረግን ነው።

ቡድኑ ብዙዎቻችን ጥቃቅን ፕላስቲኮችን የምንወስድበትን አንዳንድ የተለመዱ መንገዶችን፣ ለምሳሌ በፕላስቲክ የታሸጉ የሻይ ቅጠል በሙቅ ውሃ ውስጥ መንከር ወይም ፈሳሾችን በማይክሮዌቭ በፕላስቲክ ዕቃ ውስጥ ማሞቅን ለይቷል።

በጎ ፍቃደኞቹ ፈሳሹን እንዲጠጡ ከመጠየቃቸው እና ቀጥሎ የሚሆነውን ለመከታተል ከመሞከራቸው በፊት ስለ ሁኔታው ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ራይት "ማሞቅ እና ሙቅ ውሃ ፕላስቲክን ወደ ሰውነታችን ለማስገባት በጣም መጥፎው ሁኔታ መሆናቸውን እናውቃለን። እና ይህም ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ከተለመዱት የፕላስቲክ እቃዎች በማስወጣት ወደ ሰውነታችን እንዲገቡ ያመቻቻል" ብለዋል።

"ስለዚህ ከእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ወስደን ምን ያህሉ የፕላስቲክ ቅንጣቶች በአንጀታቸው ውስጥ ገብተው ወደ ደማችን እንደሚሰርፁ ለማየት እንሞክራለን።"

ይህንን ለመገምገም፣ ራይት በ10 ሰዓታት ውስጥ የፈቃደኞቹን ደም በተደጋጋሚ ጊዜያት ለክተዋል።

መረጃው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ በሚታተምበት ጊዜ በፕላስቲክ የታሸገን ሻይ ቅጠል ሙቅ ውሃ ውስጥ መንከር ወይም የተዘጋጀ ምግብን በማይክሮዌቭ ማሞቅ ምን ያህል ጥቃቅን ፕላስቲኮች ወደ ሰውነታችን እንዲገቡ እንደሚያደርግ የመጀመሪያውን ተጨባጭ መረጃ ይሰጣል።

በራይት ዕይታ፣ እንዲህ ያለው መረጃ በተራ ሰው ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና አደጋ የበለጠ ለመረዳት መንገድ ይከፍታል።

ደማችን ውስጥ ሰርገው የሚገቡት የጥቃቅን ፕላስቲክ ዓይነቶች ትናንሽ ቅንጣቶች እንደሆኑ ተንብየዋል።

ነገር ግን በእንስሳት እና በላብራቶሪ ብልቃጦች ውስጥ የተለያዩ ምርመራዎች ቢደረጉም፣ የጥቃቅን ፕላስቲክ መጠን በአንድ ጤናማ ሰው ላይ ምን ጉዳት እንደሚያደርስ ምንም መረጃ የለንም ማለት ይቻላል።

ውሃ የሚጠጣ ሰው እና የተለያዩ የአካል ክፍሎቹ

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

የምስሉ መግለጫ, አንድ ሊትር የፕላስቲክ ውሃ እስከ 240 ሺህ የሚደርሱ የተለያየ መጠን ያላቸው የተለያዩ የፕላስቲክ ቅንጣቶችን ሊይዝ ይችላል

ራይት "በሰውነት ውስጥ ምን ያህል ፕላስቲክ እንደሚቆይ መረዳት አለብን" ይላሉ።

"የበለጠ የሚያሰጋው ፕላስቲኩ የሚከማችበት ቦታ እና የሆነ ቦታ እየተጠራቀመ ከሆነ ነው። ምናልባት ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ ሊሰባብረው አይችልም። ይህ እንደ እብጠት ወይም ጠባሳ የረጅም ጊዜ ችግሮች ያስከትላል፤ ይህም የአካል ክፍሎች በትክክል እንዳይሠሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።"

እነዚህ ጥያቄዎች አሁን ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው፤ ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ውስጥ አንዳንድ አስደንጋጭ ጥናቶች ወጥተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2024 መገባደጃ ላይ የቻይና ተመራማሪዎች የመገጣጠሚያ ቀዶ ሕክምና ባደረጉ ሰዎች አጥንት እና ጡንቻዎች ውስጥ ጥቃቅን ፕላስቲኮችን አግኝተዋል።

እነዚህ ፕላስቲኮች ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆነው ይሆናል የሚል ስጋት ነበራቸው።

ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ አንዳንድ ፕላስቲኮች የአጥንት እና የጡንቻ ሴሎችን ዕድገት ሊያዘገዩ ይችላሉ።

ቀደም ሲል በ2024 የጣሊያን ሳይንቲስቶች በልብ ሕመምተኞች የአንገት ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ላይ ጥቃቅን ፕላስቲኮች አግኝተዋል።

እነዚህ ፕላስቲኮች ከጤና ሁኔታ ጋር የተቆራኙ ናቸው። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ ፕላስቲክ ያለባቸው ሰዎች በስትሮክ፣ በልብ ድካም የመጠቃት ወይም በድንገት የመሞት ዕድላቸው በ4.5 እጥፍ ይጨምራል።

ከዚያም በየካቲት 2025 ተመራማሪዎች በሞቱ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ፕላስቲክ አግኝተዋል።

በጣም የሚያስደንቀው ክፍል የመርሳት ችግር ያለባቸው ሰዎች በአእምሯቸው ውስጥ ከሌሎቹ ይልቅ እስከ 10 እጥፍ የሚበልጥ ፕላስቲክ ነበራቸው።

ጥናቱን የመሩት ሳይንቲስት ማቲው ካምፐን "ደነገጥን" ብለዋል።

ካምፐን አንጎል ለኃይል ስብ ስለሚያስፈልገው በደም ውስጥ ከሚገኙ ቅባቶች ጋር በመጣበቅ ጥቃቅን የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ወደ አንጎል ሊገቡ እንደሚችሉ ያስባሉ።

በተለይም በስብ የበለፀጉ አካባቢዎች አእምሮ ለፕላስቲክ ምቹ ቦታ እንደሆነም ተናግሯል። አንጎል ቀስ በቀስ ቆሻሻን ያስወግዳል። የመርሳት ችግር ባለባቸው ሰዎች የመከላከያ ሥርዓቱ (የደም አንጎል ሽፋን) ደካማ ነው፤ ስለዚህ ፕላስቲክ በቀላሉ ሊገባ ይችላል።

የሰው ልጅ ከፊል የአካል ክፍልን የሚያሳይ ንድፍ

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ተመራማሪዎች በአጥንት እና በአጥንት ጡንቻ ናሙናዎች ውስጥ ማይክሮፕላስቲኮችን አግኝተዋል

በአንገት ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ላይ ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ያገኙት ካምፐን እና የጣሊያን ሳይንቲስቶች እነዚህ ፕላስቲኮች በቀጥታ የመርሳት በሽታ ወይም የልብ ሕመም ያስከትላሉ ብለው አይደመድሙም።

ይልቁንም ጥቃቅን ፕላስቲኮች ከሌሎች ጎጂ ነገሮች ጋር በመተባበር ለብዙ ዓመታት ጤናችንን ቀስ በቀስ ሊጎዱ ይችላል ብለው ያስባሉ።

ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡት የብክለት ኤክስፐርት የሆኑት ፋይ ኩሴሮ ጥቃቅን ፕላስቲኮች በግልጽ ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትለው አስቤስቶስ አይደሉም ብለዋል።

ነገር ግን ቀስ በቀስ ሴሎችን ሊያበላሹ እና በሰውነት ላይ ጭንቀት ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ይህም ሰዎችን የበለጠ ለሕመም ይዳርጋቸዋል።

ቃሉ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ጥቃቅን የፕላስቲክ ክፍሎችን ስለሚሸፍን 'ማይክሮፕላስቲክን' ማጥናት ከባድ ነው። ለምሳሌ አንድ ሊትር የታሸገ ውሃ እስከ 240 ሺህ የሚደርሱ የተለያዩ የፕላስቲክ ዓይነቶች ለምሳሌ እንደ ናይሎን ወይም ፖሊቲሪሬን ያሉ የፕላስቲክ ቅንጣቶች ሊኖሩት ይችላል።

ከኦስትሪያ የመጡት የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ቬሬና ፒችለር ብዙ ዓይነት የፕላስቲክ ዓይነቶች እንዳሉ እና በተለያየ መንገድ እንደሚሰባበሩ ይናገራሉ።

አክለውም "ማይክሮፕላስቲክ" በጣም ሰፊ ቃል ነው፤ እና ሁሉንም ዓይነቶች አያብራራም ብለዋል።

ሌላው የተመራማሪዎች ችግር ማይክሮፕላስቲክ እያንዳንዱን ሰው በተለያየ መንገድ ሊጎዳ መቻሉ ነው።

አንዳንድ ፕላስቲኮች ጎጂ ኬሚካሎችን ከአካባቢው ሊወስዱ ወይም ከባድ ብረቶችን ሊሸከሙ ይችላሉ።

ሌሎች በሰውነት ውስጥ በሆርሞኖች ውስጥ ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ። ናኖፕላስቲክ የሚባሉት ትናንሽ ቅንጣቶች ወደ ሴሎች ሊገቡ እና የበለጠ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ።

እግርን የሚያሳይ የሰውነት ንድፍ

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

የምስሉ መግለጫ, አንዳንድ ማይክሮፕላስቲኮች ፀረ ተህዋሲያን የመቋቋም ዘረመል ላላቸው እንደ ማዐዕከል ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ እነዚህም ከባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች ጋር መስተጋብር ሊፈጥሩ የሚችሉ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ይሰጣሉ

ማይክሮፕላስቲኮች የሚባሉት አንዳንድ ጥቃቅን የፕላስቲክ ቁርጥራጮች እንደ ባክቴሪያ፣ ቫይረሶች፣ ፈንገሶች ወይም ጥገኛ ተሕዋሲያን ያሉ ጀርሞች መድኃኒትን ለመቋቋም የሚረዱ ልዩ ዘረመሎችን ሊሸከሙ ይችላሉ።

ኩሴሮ በአንታርክቲካ የሚገኝ ፕሮጀክትን እየመራ ከመዝናኛ መርከቦች የሚወጣውን ቆሻሻ እና ምን ዓይነት ማይክሮፕላስቲኮች እንዳሉ፣ እነዚህን ዘረመሎች የሚሸከሙ ከሆነ ለመለየት ጥናት ያደርጋል።

አንታርክቲካ ይህንን ለማጥናት ተመራጭ ቦታ ነው። ምክንያቱም እነዚህ የመከላከያ ዘረመሎች ጥቂት ስላሉ፣ በቀላሉ ስሪታቸውን ለመመልከት ያስችላል።

በጣሊያን የሚኖሩት ዶክተር እና ተመራማሪ ራፋኤሌ ማርፌላ ሁለቱም ማይክሮፕላስቲክ እና ናኖፕላስቲክስ የሚባሉ ትናንሽ ቁርጥራጮች ሰዎች በፍጥነት እንዲያረጁ ያደርጋሉ ብለው ያስባሉ።

ይህ ሊሆን የቻለው የደም ሥሮችን ስለሚጎዱ፣ ቀጣይነት ያለው ዝቅተኛ ደረጃ የሰውነት መቆጣትን ስለሚያስከትሉ እና ሴሎች እንዴት ዘረመል (ዲኤንኤ) ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ጎጂ ሞለኪውሎችን በመፍጠር ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ሳይንቲስቶች በባሕር ወፎች ላይ ይህን የመሰለ ጉዳት አስቀድመው አይተዋል፤ እና ማርፌላ በሰዎች ላይም ሊከሰት ይችላል ብለው ያስባሉ።

ሌላው ተመራማሪ ፒችለር ናሙናዎቹ በሰው ልጅ ዓይነ ምድር ውስጥ መገኘታቸውን ካወቁ በኋላ ስለ ማይክሮፕላስቲኮች ፍላጎት አደረባቸው።

ከአንጀት ካንሰር መጨመር ጋር የተገናኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመጠየቅ ምርምር የሚያደርጉት ፒችለር፣ ጥናታቸው በአሁኑ ጊዜ በሰውነት ውስጥ የማይክሮፕላስቲኮች መከማቸት ለካንሰር ሊያጋልጥ እንደሚችል ያላቸውን ጥርጣሬ ከፍ አድርጎታል።