እንግሊዝ ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ቁሶችን ልታግድ ነው

ፕላስቲክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእንግሊዝ መንግሥት "በፕላስቲክ ላይ ጦርነት" ማወጁን ተከትሎ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ቢላዎች፣ ሳህኖች እና ኩባያዎችን ለማገድ ማቀዱን አስታወቀ።

የአገሪቱ ሚኒስትሮች እርምጃው የቆሻሻን መጠን ለመቀነስ ብሎም በውቅያኖሶች ውስጥ ያለውን የፕላስቲክ ክምር ለመቆጣጠር የሚረዳ ነው ብለዋል።

በፖሊሲው ላይ በመጪው ጥቂት ወራት ውስጥ ምክክር ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ከተጠቀሱት ቁሶች በተጨማሪ ሌሎች ቁሳቁሶች ሊካተቱ እንደሚችሉም ተነግሯል።

የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች አስቸኳይ እና ሰፊ እርምጃ ያስፈልጋል በሚል ጫና እያደረጉ ነው።

ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለውን የፕላስቲክ መቁረጫ ለመከልከል አቅደው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ሰንብተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት በሐምሌ ወር ተመሳሳይ የእገዳ ሐሳብ በማውጣት የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና ሲያደርግ ቆይቷል።

በእንግሊዝ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በዓመት በአማካይ 18 ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሳህኖችን እንዲሁም 37 ሌሎች እቃዎችን እንደሚጠቀም የመንግሥት አሃዞች ይጠቁማሉ።

ሚኒስትሮቹ ይህንን የፕላስቲክ ብክለት ለመከላል ያሰበውን ይህንን ሕግ በመጪው ዓመት ሚያዚያ እንዲጸድቅ እየሠሩ ነው።

በተለይም በፕላስቲክ ማሸጊያዎች ላይ ግብር ለመጣልና የፕላስቲክ እቃዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ተቀማጭ ገንዘብን የመመለስ ዘዴን ለመተግበር አስበዋል።

"ሁሉም ሰው ፕላስቲክ በአካባቢያችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አይቷል፤ እናም በመናፈሻ ሰፍራዎች እና በባሕር ዳርቻዎቻችን በግዴለሽነት የተጣሉ ፕላስቲኮችን ለማጽዳት ያግዛል" ሲሉ የአገሪቱ አካባቢ ጥበቃ ዋና ጸሐፊ ጆርጅ ኦስቲ ተናግረዋል።

አክለውም የተለያዩ መሻሻሎች እንደታዩ እና እነዚህ አዳዲስ ዕቅዶች በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ፕላስቲኮችን አላስፈላጊ አጠቃቀምን ለማጥፋት እንደሚረዱ ተናግረዋል።

ነገር ግን ይህ አዲስ እገዳ ሕግ ለመሆን አንድ ዓመት ሊወስድ ይችላል። የአካባቢ ጥበቃ አንቂዎች መንግሥት በፍጥነት እንዲንቀሳቀስ እያሳሰቡ ይገኛሉ።