የምድራችን ሰው ሠራሽ ቁሶች ክብደት ከሰው፣ ከእንስሳትና ከእጽዋት ሊበልጥ ተቃርቧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕላስቲክ፣ ጡብ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ብረታ ብረት እና ሌሎችም በመላው ዓለም ያሉ ሰው ሠራሽ ቁሳቁሶች ያስቡ።
ከዚያም ምድር ላይ የሚገኙ የሰው ልጆች፣ እንስሳት እና እጽዋትን ያስቡ።
በምድር ላይ ከሰው ሠራሹ ቁሳቁስ እና ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች የየትኛው ክብደት የሚበልጥ ይመስልዎታል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ በዚህ ዓመት ማገባደጃ ቁሳቁሶች ባጠቃላይ ሲደመሩ ከሰው ልጆች፣ እንስሳት እና እጽዋት በድምር ክብደት ይበልጣሉ።
የሰው ሠራሽ ቁሳቁስ ክብደት ከሰው ልጆች፣ እንስሳትና እጽዋት ሲበልጥ በታሪክ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የሰው ሠራሽ ቁሳቁሶች ክብደት በግምት አንድ ቴራቶን ይሆናል።
ይህ ማለት በየሳምንቱ ከእያንዳንዱ ሰው የሰውነት ክብደት በላይ የሚመዝን ቁስ ይመረታል ማለት ነው።
አሃዙን የሠሩት በእስራኤል፤ ዊዝማን ኢንስቲትዩት የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ናቸው።
ጥናቱን የመሩት ዶ/ር ሮን ሚሎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የጥናታቸው ውጤት የሰው ልጆች ዓለምን በምን መንገድ እየለወጡ እንደሆነ ይጠቁማል።
"ምን ያህል ነገር ጥቅም ላይ እንደምናውል እንድናስብ ያነሳሳል። ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ነገሮችን ማመጣጠን እንደሚያስፈልግም ያሳያል" ብለዋል።
የፕላስቲክ ውሃ መያዣ፣ ለመንገድና ሕንጻ ግንባታ የሚውል ጡብ ወዘተ. . . የሰው ልጅ የሚያመርተው ቁሳቁስ እጅግ እጅግ ብዙ ነው።
የቁስ መጠን በየ20 ዓመቱ እየተበራከተ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል የሰው ልጆች፣ የእንስሳት እና እጽዋት ክብደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደን መመናመኑና ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ከምድረ ገጽ እየጠፉ መምጣታቸው ነው።
ሳይንቲስቶች የቁሳቁስ ክብደት ሕይወት ካላቸው ነገሮች ክብደት በላይ እንደሚሆን ይጠብቁ ነበር። መላ ምታቸው እውነት የሚሆነው ደግሞ ባለንበት የፈረንጆች ዓመት 2020 መጨረሻ ላይ ነው።
አውራ ጎዳናዎቻችን፣ ሕንጻዎቻችን፣ ማሽኖቻችን እና ሌሎችም ቁሳቁሶች ሲደመሩ ከእኛ ከሰው ልጆች የሚበልጥበት ጊዜ ቀርቧል።
አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠልን በ2040 የሰው ሠራሽ ቁሳቁስ መጠን ከሰዎች፣ እንስሳት እና እጽዋት ሦስት እጥፍ ሊበልጥ ይችላል።
ይህ ማለት ከ20 ዓመታት በኋላ የቁሳቁስ መጠን 1.1 ቴራቶን ይደርሳል ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ የሰው ልጆች በየዓመቱ 30 ጊጋቶን ቁሳቁስ እያመረቱ ይቀጥላሉ።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ የሰው ልጅ ምድር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከሚሊዮን ዓመታት በኋላ በአለት ላይ የሚታይበት ዘመን (Anthropocene) ስለመድረሱ አንድ ማሳያ ነው።
የዚህ ሂደት ጅማሮ በ1950ዎቹ እንደሆነ ይነገራል።
ይህ በሳይንሳዊ አጠራሩ "Great Acceleration" የሚባለው ሂደት የሕዝብ ቁጥርና የሰው ልጆች ቁሳቁስን ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መንገድ መለወጥ የጀመረበት ነው።












