2021 ቀዝቃዛ የአየር ጸባይ የሚመዘገብበት ይሆናል ተባለ

ቅዝቃዜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ኪንግደም የአየር ጸባይ ትንበያ ባለሙያዎች መጪው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2021 ከቅርብ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በመላው ዓለም ቀዝቃዝ ያለ የአየር ሁኔታ የሚመዘገብበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን በርካታ የዓለማችን ክፍሎች ቀዝቀዝ ያሉ ጊዜያትን የሚያሳልፉ ቢሆንም የግሪንሃውስ ጋሶች ልቀት ግን አሁንም ትልቁ የአየር ጸባይን ለውጥን የሚያስከትል ምክንያት ሆኖ እንደሚቀጥል ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የአየር ጸባይ ትንበያ ባለሙያዎች እንደሚሉት አዲሱ ዓመት ከኢንደስትሪያል አብዮት በፊት ዓለም ከነበራት ሙቀት በ1 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ያለ ይሆናል።

በዚህ መጠን ከፍ ያል የአየር ጸባይ ለውጥ ሲመዘገብ ይህ ለሰባተኛ ተከታታይ ዓመት ነው።

በአውሮፓውያኑ 2021 የምድር የሙቀት መጠን በ0.91 ሴልሺየስ እና 1.15 ሴልሺየስ መሀል እንደሚሆንና ይህም ከ1850 እስከ 1900 ባሉት ዓመታት ከነበረው ብልጫ ያለው እንደሆነ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። በእነዚህ ዓመታት የተመዘገበው የምድር ሙቀት ደግሞ 1.03 ሴልሺየስ ነበር።

በ2021 ይመዘገባል ተብሎ የተተነበየው የምድር የሙቀት መጠን ከቅርብ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ቢሆንም ነገሮች እየተሻሻሉ ለመሆናቸው ግን ማሳያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ ባለሙያዎቹ።

ለዝቅተኛው የሙቀት መጠን ምክንያቱ ደግሞ ላ ኒና ነው።

ላ ኒና በማዕከላዊው የፓስፊክ ውቂያኖስ ክፍል የሚታይ ከፍተኛ መጠን ያለው የባህር ወለል ሙቀት ነው።

''በአሁኑ ሰዓት እየተስተዋለ ባለው የላ ኒና ክስተት ምክንያት በአዲሱ ዓመት ዓለማችን ቀዝቀዝ እንደምትል ይገመታል። ነገር ግን በ2011 እና 2000 ላይ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁንም ቢሆን ይህ ሙቀት ከፍተኛ መሆኑን አስተውለናል'' ብለዋል የዩናይትድ ኪንግደም የአየር ጸባይ ትንበያ መስሪያ ቤት ኃላፊው ፕሮፌሰር አዳም ስካፊ።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት እንደ ላ ኒና ያሉ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ዓለምን ቀዝቀዝ የሚያደርጓት ቢሆንም በግሪን ሃውስ ጋሶች ምክንያት የሚበከለው አየር ጉዳይ ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው።

እስካሁን በተሰበሰቡ መረጃዎች መሰረት የአውሮፓውያኑ 2016 በዓለማችን ሞቃቱ ዓመት የተባለ ሲሆን 2020 እና 2019 ደግሞ ይከተላሉ።