ጣሊያናውያን የገና እና አዲሰ ዓመት በዓልን በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ያሳልፋሉ ተባለ

ጣሊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጣሊያን በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ከገና በዓል እስከ አዲስ ዓመት ድረስ የሚዘልቅ የእንቅስቃሴ ገደብ አስተላለፈች።

አውሮፓውያኑ የገና በዓላቸውን ታኅሣሥ 16 እንዲሁም የዘመን መለወጫ በዓልን ታኅሣሥ 23 ያከብራሉ።

የእንቅስቃሴ ገደቡ ተጥሎ በሚቆይበት ወቅት መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ዝግ ይሆናሉ። ጣሊያናውያንም ከቤታቸው መውጣት የሚችሉት ወደ ሥራ ገበታቸው ለመሄድ አልያም የሕክምና አገልግሎት ካስፈለጋቸው ብቻ ነው።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚንሰትር ጁሴፔ ኮንቴ አስተዳደራቸው በበዓላት ወቅት የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ ውሳኔ ማስተላለፉ ቀላል አልነበረም ብለዋል።

“በገና በዓል ወቅት የሰዎች እንቅስቃሴ ሲጨምር በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ያሻቅባል የሚል ስጋት በመኖሩ” ይህን ውሳኔ ለመወሰን መገደዳቸውን ጠቅላይ ሚንሰትሩ አስረድተዋል።

ከእንቅስቃሴ ገደቡ በተጨማሪ በጣሊያን ተጥሎ የሚገኘው የሰዓት እላፊ ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል።

በተቀረው አውሮፓስ?

በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በቤተ-መንግሥታቸው እራሳቸውን ለይተው ይገኛሉ።

ማክሮን ድካም፣ ራስ ምታት እና ደረቅ ሳል እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባሳለፍነው ሳምንት በአውሮፓ ሕብረት ስብሰባ ላይ የተገናኙት የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚንሰትር ኢጎር ማቶቪች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።

በስብሰባው የተሳቱፉ የቤልጄም፣ ስፔን እና ፖርቹጋል መሪዎች ለጥንቃቄ እራሳቸውን ለይተው እንደሚያቆዩ አስታውቀዋል።

የገና በዓል መቅረቡን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ አገራት ጥብቅ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎችን እያወጡ ይገኛሉ።

ኔዘርላንድስ እና ጀርመን ለመጪዎቹ 10 ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ኦስትሪያ በበኩሏ ከገና በዓል በኋላ የዜጎችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስታውቃለች። የስዊድን ባለስልጣናት በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ ዜጎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል።

በምግብ ቤቶች ከአራት ሰዎች በላይ በአንድ ላይ እንዳይቀመጡ እንዲሁም የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥም መመሪያ አስተላልፋለች።