በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ዓለማችን 1.3 ቢሊየን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ መሸከም ትችል ይሆን?

የፕላስቲክ ቆሻሻዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም መንግሥታት ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ የማይሆኑ ከሆነ 1.3 ቢሊየን ቶን የሚመዝን ፕላስቲክ በጎርጎሳውያኑ 2040 በምድር ላይ እና በውሃ አካላት ላይ ሊገኝ እንደሚችል ተጠቁሟል።

ይህ መረጃ ይፋ የሆነው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት አጠቃላይ የዓለም የፕላስቲክ አጠቃቀም ችግርና መጠን ምን እንደሚመስል በተደረገ ጥናት ላይ ነው።

ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ኮስታስ ቬሊስ እንደሚሉት ቁጥሩ እጅግ አስፈሪ ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ የሰው ልጅ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ምጥቀትና ስልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል።

'' በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ሊኖር ስለሚችለው ጉዳት ጠቅለል ያለ ጥናት ሲሰራ ይሄ የመጀመሪያው ሲሆን የፕላስቲክ ክምሩ ምን ያክል መጠን እንደሚኖረው ማሰብ ከባድ ነው። ምናልባትም አጠቃላይ ዩኬን 1.5 እጥፍ የመሸፈን አቅም ያለው ሊሆን ይችላል'' ብለዋል ዶክተር ኮስታስ።

አክለውም ፕላስቲክ ጥቅም ላይ የሚውልበት መጠን እና አወጋገዱ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተለያየ መሆኑ መረጃዎች በቀላሉ እንዳይገኙ ያደርጋል። ''እርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ሁሉም የዓለማችን አገራት ፕላስቲክን መጠቀም ከሚገባቸው በላይ ይጠቀማሉ።''

የተወሳሰበውን የፕላስቲክ ክምችት ለመከታተልም አጥኚዎቹ በዓለማችን ላይ ያለውን የፕላስቲክ አመራረት፣ አጠቃቀምና አወጋገድ ላይ በትኩረት ሰርተዋል። በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 1.3 ቢሊየን ቶን ፕላስቲክ ምድራችንን ሊወራት እንደሚችል የደረሱበት።

በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑትና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት ዊኒ ላው ለቢቢሲ እንደገለጹት በ2040 ወደ ባህር የሚገባውን የፕላስቲክ መጠን እስከ 80 በመቶ ድረስ መቀነስ ይቻላል።

ለዚህም ይረዳሉ ብለው ያስቀመጧቸው ምክረ ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸወ።

  • የፕላስቲክ ውጤቶችን ምርትና አጠቃም መቀነስ
  • ፕላስቲክን በወረቀትና መበስበስ በሚችሉ ምርቶች መቀየር
  • ምርቶችን ለአስተሻሸግና መልሶ ለመጠቀም ምቹ አድርጎ መስራት
  • በተለይ ደግሞ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ያለውን የፕላስቲክ አወጋገድ ማስተካከልና በተገቢውው መንገድ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ
  • መልሶ ጥቅም ላይ መዋል የማይችሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ማስወገድ የሚችሉ ማዕከላትን መቋቋም
  • የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ወደ ድሀ አገራት መላክ ማቆም

ይህኛውን ጥናት ጨምሮ በተሰሩ ሌሎች ጥናቶችም በግልጽ እንደተቀመጠው የፕላስቲክ ምርቶች በውሃ አካላትና እንስሳት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

እስከ 700 አይነት የባህር እንስሳት እና ንጹህ ውሃ ላይ የሚኖሩ ከ50 በላይ የአሳ ዝርያዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ፕላስቲክ ተመግበዋል ወይም በሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል።

በተጨማሪም የፕላስቲክ ብክለት የሰዎችን ሕይወት እጅጉን ከባድ እያደረገው መጥቷል። በቀላሉ ማስተዋል የሚቻሉ ብዙ ጉዳቶችም አሉት። ለምሳሌ የውሀ መውረጃዎችን መድፈን፣ ለተለያዩ ባክቴሪያዎችና ጎጂ ተህዋሲያን ምቹ የመራቢያ ቦታ መሆን፣ ተክሎች እንዳያድጉ ማድረግ እና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ ጉዳቶች አሉት።

ምንም እንኳን የፕላስቲክ ምርቶችን በማስወገድ ሂደት ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም በዓለማችን የሚገኙትና 11 ሚሊየን የሚደርሱ የፕላስቲክ ምርቶች ሰብሳቢዎች ተገቢውን ስልጠናና አቅርቦት አያገኙም።

በዚህም ምክንያት መወገድ የሚገባቸውን ምርቶች በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል ከሚችሉት መለየትና በአግባቡ ማስወገድ አይችሉም። በተጨማሪም ፕላስቲኮቹን በድጋሚ ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የሚያገኙት ድጋፍ በእጅጉ አነስተኛ ነው።

የሊድስ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ኮስታስ ቬሊስ እንደሚሉት ፕላስቲክ ሰብሳቢዎች ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ናቸው። '' እነዚህ ፕላስቲክ ሰብሳቢዎች ባይኖሩ ኖሮ አሁን ከምናየው በላይ በርካታ ጉዳት ሊደርስ ይችል ነበር።''

ተመራማሪዎቹ በሰበሰቡት መረጃ መሰረት የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በአሳ ማጥመድ፣ በቱሪዝምና በመርከብ ጉዞ ላይ በሚያደርሱት ጫና ብቻ ዓለማችን በየዓመቱ እስከ 13 ቢሊየን ዶላር ታጣለች።