በቦረና የእንስሳት ሃኪሞች ከአንድ ላም ሆድ ውስጥ 50 ኪሎ የሚመዝን ፕላስቲክ አወጡ

የጤና ባለሙያዎች

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን 6 የእንስሳት ሃኪሞች ከአንዲት ላም ሆድ ውስጥ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፕላስቲክ በቀዶ ህክምና አስወገዱ።

ከጤና ባለሙያዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ፍራኦል ዋቆ፤ “ላሚቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች” ሲሉ ከቀዶ ህክምናው በኋላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ፍራኦል “ከብቶች የሚግጡት ሳር ሲያጡ ወይም በሰውነታቸው ውስጥ የንጥረ ነገር እጥረት ሲያጋጥማቸው ፕላስቲክ ሊበሉ ይችላሉ” ያሉ ሲሆን ጨምረውም፤ ሰዎች ፕላስቲክ የሚያስወግዱበት መንገድ ለቁም እንስሳት ጤና ችግር እየሆነ ነው” ብለዋል።

ከላሚቷ ሆድ ውስጥ የወጣው 50 ኪ.ግ የሚመዝነው ፕላስቲክ
የምስሉ መግለጫ, ከላሚቷ ሆድ ውስጥ የወጣው 50 ኪ.ግ የሚመዝነው ፕላስቲክ

50 ኪሎ ግራም ፕላስቲክ የተወገደላት ላም ባለቤት የሆኑት አቶ አሬሪ ጨሪ በተመሳሳይ ከዚህ ቀደምም ፕላስቲክ የተመገበች ሌላ ላም ወደ ጤና ባለሙያዎቹ አምጥቶ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፕላስቲክ ከሆዷ ወጥቶ ነበር።

“ከዚህ ቀደም ረድተነው ስለነበረ፤ ስለሚያምነን ነው ይህችን ላም ይዞ በድጋሚ የመጣው” ይላሉ ዶ/ር ፍራኦል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙት የቦረና ሕዝብ አርብቶ አደሮች ሲሆኑ፤ መተዳደሪያቸው የተመሰረተው በእንስሳቶቻቸው ላይ ነው።