ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚፈጽሙት ‘መንፈሳዊ ፈዋሾች’

መንፈሳዊ ፈዋሽ ነን በሚሉ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ብዝበዛዎችን በተመለከተ ቢቢሲ አረብኛ በርካታ መረጃዎችን ሰብስቧል።
‘መንፈሳዊ ፈውስ’ (የቅዱስ ቁርዓን ፈውስ) በአረቡ እና በሙስሊሙ ዓለም ህሙማንን ከገጠማቸው የጤና ችግር ለማዳን ጥቅም ላይ ይውላል።
ይህንን የፈውስ አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች ምናልባትም በኢትዮጵያ ‘አዋቂዎች’ ተብለው ከሚጠሩት ጋር ሊስተካከል ይችላል።
በአብዛኛው እነዚህን መንፈሳዊ ፈዋሾችን (አዋቂዎችን) የሚጎበኙት ሴቶች ሲሆኑ ‘ጂኒ’ በመባል ከሚታወቁት እርኩስ መናፍስት ቁራኛ እንደሚያላቅቋቸው በማመን ነው።
ቢቢሲ ከአንድ ዓመት በላይ በሞሮኮ እና በሱዳን የ85 ሴቶችን የምስክርነት ቃል አሰባስቧል።
መንፈሳዊ ፈውስ ታዋቂ በሆነባቸው በእነዚህ አገራት ፈዋሽ የተባሉ ግለሰቦች ያደረሱትን ከትንኮሳ እስከ መድፈር ያሉ ክሶችንም ከሴቶቹ ሰምቷል።
ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች በተጨማሪም ቢቢሲ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ፍርድ ቤቶችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን ጥቃቶቹን አስመልከቶ ያናገረ ሲሆን፣ ጉዳዩን በማጣራትም ወራት አሳልፏል።
ለምርመራ ዘገባውም ቢቢሲ በድብቅ ዘጋቢ ያሰማራ ሲሆን፣ እሷም በአንድ ፈዋሽ ነኝ በሚል ግለሰብ አግባብ ባልሆነ መንገድ ተነክታለች። ግለሰቧም ከስፍራው አምልጣ ወጥታለች።
ማስጠንቀቂያ፡ አንባቢዎች የጽሁፉ ይዘት ዝርዝሮች ሊረብሿቸው ይችላሉ።
በትክክለኛ ስሟ የማንጠራት ዳላል ከጥቂት ዓመታት በፊት ነበር በሞሮኮዋ ካዛብላንካ አቅራቢያ በምትገኝ ከተማ ወደሚገኝ ፈዋሽ (አዋቂ) ያመራችው።
በ20ዎቹ አጋማሽ የነበረችው ዳላል ለነበረባት ጭንቀት እና ድብርት መፍትሄ ለማግኘት ነበር ወደ ስፍራው ያቀናችው። አዋቂው አንድ ያፈቀራት ጂኒም እንደተቆራኛት ነገራት።
ፈዋሹ ከበሸታዋ እንደሚፈውሳትም ነግሯት አንድ ሽቶ የሚመስል ነገር እንድታሸት ጠየቃት። ያነገር አደንዛዥ ዕጽ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት በሙሉ ልብ የምታምነው ዳላል፣ ለዚህም በወቅቱ ራሷን መሳቷን በምክንያትነት ትጠቅሳለች።
ዳላል ከዚህ በፊት የወሲብ ግንኙነት ፈጽማም አታውቅም። ራሷን ከሳተችበት ስትነቃም የውስጥ ሱሪዋ (ፓንቷ) ወልቆ እና ተደፍራ ራሷን አገኘችው።
‘ራቂ’ የሚል ስያሜ ያለውን ፈዋሽን “ምንድን ነው ያደረግከኝ?” በሚልም መጮህ ጀመረች። “አሳፋሪ ነህ” ሌላም ሌላም እያለች “ለምንድን ነው እንዲህ የፈጸምክብኝ?” ስትለውም ግለሰቡ “ጂኒውን ከሰውነትሽ እንዲወጣ ለማድረግ ነው” አላት።
በደረሰባት መደፈርም እፍረት ተሰምቷት ጉዳቷን በውስጧ ያዘች። በደረሰባትም ጥቃት ጥፋተኛ እንደምትባል እርግጠኛ ስለሆነች፣ የተፈጸመባትን ለመናገር አልደፈረችም። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነፍሰ ጡር መሆኗን ተረዳች።
ከፍተኛ ድንጋጤም ተሰማት፤ በወቅቱ ራሷን ለማጥፋት አሰበች።
ለፈዋሹ ስለ እርግዝናዋ ስትነግረው ጂኒው አስረግዟት ሊሆን እንደሚችል ነገራት። ዳላል ከፍተኛ ድንጋጤ እና ያለማመን ስሜት ተጫናት። ልጇንም ወለደች። ነገር ግን ልትመለከታትም ሆነ ልታቅፋት፣ እንዲሁም ስም ልታወጣላች አልፈለገችም። በማደጎም ሰጠቻት።
ቤተሰቦቿ የደረሰባትን ካወቁ እንደሚገድሏትም ለቢቢሲ ተናግራለች። ዳላል ብቻ ሳትሆን ጥቃት የደረሰባቸው ሌሎች ሴቶችም ከዳላል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ገጠመኝ አላቸው። የደረሰባቸውን መደፈር ከተናገሩ ራሳቸው ጥፋተኛ ስለሚደረጉ ለፖሊስ ይቅር እና ለቤተሰቦቻቸው የተናገሩ በጣም ጥቂቶች ናቸው።
ሌላኛው ደግሞ የተፈጸመባቸውን ጥቃት ቢናገሩ ‘ጂኒዎቹ’ ሊበቀሉን ይችላሉ የሚል ስጋትም አላቸው።
በሱዳን ሳውሳን የምትባል ግለሰብ ባሏ ከሁለተኛ ሚስቱ ጋር መኖርን መርጦ ቤቱን ትቶ ወጣ።
በሸሪዓ ሕግ መሠረት ባለቤቷ ይህንን ማድረግ የሚፈቀድለት ሲሆን፣ ከፍተኛ ችግር የገባት ሚስቱ እርዳታን ለማግኘት ወደ አዋቂ ሄደች።
ባለቤቷ እሷን እንዲያፈቅራት እና በተሻለ እንክብካቤ እንዲይዛት ለመጠየቅ ነበር ወደ ፈዋሹ ያመራችው። ነገር ግን አዋቂው የጠየቃት ያላሰበችውን የሕክምና ዓይነት ነበር።
“ከእሱ ጋር ወሲብ ፈጽመን ፈሳሹን በመጠቀም ለባለቤቷ ልትመግበው የምትችለውን መድኃኒት እንደሚያዘጋጅ ነገረኝ” ትላለች።
ፈዋሹ (አዋቂው) ይህንን ሲናገር “ያለ ፍርሃትም” እንደነበር ታስታውሳለች።
“ለፖሊስ ወይም ለፍርድ ቤት፣ አልፎ ተርፎም ለባለቤቴ እንደማልነግረው እርግጠኛ ነበር” በማለት ታስረዳለች።
ሳውሳን የተባለችውን ሳትፈጽም ወዲያውኑ ከስፍራው ወጥታ እንደሄደች እና እንዳልተመለሰችም ተናግራለች።
ግለሰቡ ያላትንም ሪፖርት አላደረገችም።
በሱዳን ወሲባዊ ብዝበዛ እና ጥቃቶች እንደተፈጸማባቸው ለቢቢሲ ከተናገሩት 50 ሴቶች መካከል ሦስቱ ሼክ ኢብራሂም የተባለ የሃይማኖት አባትን በስም ጠቅሰዋል። ስሟን የማንጠቅሳት አንደኛዋ ሴት ወሲብ እንድትፈጽም እንደገፋፋት እና እንደተጠቀመባት ተናግራለች።
ሌላኛዋ ደግሞ አፋፍ የተሰኘች ግለሰብ ለወሲብ ጠይቋት እምቢ ብትል እና ከላይዋ ላይ ልትገፋው ብትሞክርም አለመቻሏን ለቢቢሲ ተናግራለች። በዚህም አቅመ ቢስነት እንደተሰማትም ምስክርነቷን ሰጥታለች።
“በርካቶች ሼኮች እንዲህ ፈጽመዋል ቢባሉ አይቀበሉም። በጭራሽ አያምኑም። እንዴት ምስክሮችንስ ላገኝ እችላለሁ? እሱ የፈጸመብኝን ያየ የለም” ትላለች።

ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሴቶች ጋር እየሰራች የነበረች የቢቢሲ ጋዜጠኛ ህመምተኛ በመምሰል ሼህ ኢብራሂምን ለመጎብኘት ተስማማች።
ሪም ብለን የምንጠራት የቢቢሲ ዘጋቢ መሃን ነኝ በሚል ነበር ወደ አዋቂው ያቀናችው።
ሼክ ኢብራሂም ዱዓ (ጸሎት) እንደሚያደርግላት እና ወደ ቤቷ የምትወስደውም ጸበል (ማህያ) በመባል የሚታወቀውንም ውሃ በጠርሙስ አዘጋጀ። ከዚያም ተጠግቷት እንደተቀመጠ እና እጁን በሆዷ ላይ እንዳደረገው ሪም ትናገራለች።
እጁን ከሆዷ ላይ እንዲያነሳው በምትጠይቅበት ወቅት በልብሷ ላይ እንዳለ ሰውነቷን መደባበስ እና ወደ ብልቷም አካባቢም ሲያንቀሳቅስ ክፍሉን ለቃ ሮጣ ወጣች።
“ያደረገው ነገር ውስጤን አናወጠው” በማለት በኋላ የፈጠረባትን ነገር የምትናገረው ሪም “በጣም የሚረብሽ ዕይታም ነበረው” ብላለች።
በእሷ ላይ ያደረገው ነገር እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የሚጠቁም መሆኑንም ሪም ታስረዳለች።
ቢቢሲ ሪም ስለደረሰባት ነገር ሼክ ኢብራሂምን የጠየቀ ሲሆን፣ እርዳታውን በሚሹ ሴቶች ላይ ትንኮሳ ወይም ጥቃት አለማድረሱን በመናገር በድንገት ቃለ ምልልሱንም አቋርጧል።

ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ሳይፈጸምባቸው እና የአደጋው ስጋት ሳያድርባቸው መንፈሳዊ ፈውስን ለሚፈልጉ አማራጭ እየሰጠች ያለች ሴት ሸይካ ፋጢማ ናት።
በካርቱም አቅራቢያ የምትገኘው ሸይካ ፋጢማ ለሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የፈውስ ማዕከል አላት። ለ30 ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ይህ ማዕከልም ሩቅያ የተሰኘውን ሴቶች ከሌሎች ሴቶች ፈውስ ከሚያገኙባቸው ጥቂት ስፍራዎች አንዱ ነው።
ቢቢሲ ይህንን ስፍራ የጎበኘ ሲሆን፣ በተለያየ መከራ ውስጥ ያሉ ሴቶችንም በዚህ ስፍራ አግኝቷል። ሴቶቹ በሕክምና መሃከል አካባቢያቸውን የሚዘነጉበት እና ራሳቸውንም የሚስቱበት አጋጣሚም ይፈጠራል።
ሸይካ ፋጢማ ሴቶቹ እንዲህ ባለ ተጋላጭ በሆኑበት ሁኔታ እንዴት ሊጠቁ እንደሚችሉ ትናገራለች። በዚህም ሌሎች ፈዋሾች ጥቃቶች ሊያደርሱባቸው አጋጣሚዎችም ይፈጠራል ትላለች።
“በርካታ ሴቶች ወንድ ሼኮች ሰውነታቸውን በሚነካኳቸው እና በሚዳብሷቸው ወቅት ሰይጣኑን እያስወጡ ነው ብለው እንደሚያምኑ ነግረውናል። የሕክምናው አካል እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር” የምትለው ሸይካ ፋጢማ፣ ከሴቶቹ የሚሰማው ነገሮች በጣም አስደንጋጭ እንደሆነም አክላለች።
ቢቢሲ ያለውንም ማስረጃ ሰብስቦ በሞሮኮ እና በሱዳን ያሉ ባለሥልጣናትን አነጋግሯል።
በሱዳን የእስልምና ጉዳዮች ሚኒስቴር የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አላ አቡ ዘይድ፣ ይህን ያህል ሴቶች ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽሞብናል ብለው ለቢቢሲ ሪፖርት ማድረጋቸውን ለማመን ተቸግረው ነበር።
ነገር ግን በመንፈሳዊ ፈውስ ላይ ምንም አይነት ደንብ እና መመሪያ አለመኖሩ ቀውስ እንደሚፈጥር አምነው “ሙያው ሥራ ለሌላቸው ሰዎች መጠቀሚያ እየሆነ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ደንብ እንደነበረ የተናገሩት ኃላፊው፣ በአገሪቱ ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አንጻር በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
በሞሮኮ የእስልምና ጉዳዮች ሚኒስትር አህመድ ቶፊቅ፣ መንፈሳዊ ፈዋሾችን በተመለከተ የተለየ ሕግ አስፈላጊ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
“በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሕጋዊ መንገድ ጣልቃ መግባት ከባድ ነው። መፍትሔው በሃይማኖት አስተምህሮት እና በስብከቶች ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉም መልሰዋል።
ቢቢሲ ሴቶቹ የደረሰባቸውን ጥቃት እና መደፈር በተመለከተ ማስረጃዎችን ለሱዳን እና ለሞሮኮ ባለሥልጣናት ቢያሳይም ምንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ስለዚህ በፈውስ ስም ተደብቀው ጥቃት እያደረሱ ያሉ ግለሰቦችን በተመለከተ ማጋለጥ የሴቶቹ ኃላፊነት ሆኗል።













