ምልክት የማያሳየው እና ሰባ በመቶ ሴቶች የሚገጥማቸው የማሕፀን ግድግዳ እጢ

የማሕፀን እጢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከ75 እስከ 80 በመቶ የሆኑ ሴቶች ሕመሙ ይገጥማቸዋል።

ምልክት ሳያሳይ በመቆየት ይታወቃል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተለያየ መጠን ያላቸው የማሕፀን ግድግዳ እጢዎች በቀዶ ሕክምና መውጣታቸው ዜና ሲነገር ይሰማል።

አምና በዱራሜ 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ በቀዶ ሕክምና መውጣቱን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ ምንድን ነው? እንዴት ይከሰታል? ሕክምናዎቹስ ምንድን ናቸው? ስንል የማሕፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሞገስ በርዬን አነጋግረናል።

ዶ/ር ሞገስ በማሕፀን እና ጽንስ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው።

በተለያየ መንገድ የማሕፀን ግድግዳ እጢን ማከም እና እጢን ለማስወገድ ሙሉ ማሕፀንን በቀዶ ሕክምና ማውጣትን ጨምሮ ዶ/ር ሞገስ የተለያዩ የማሕፀን ግድግዳ እጢ ሕክምናዎችን ሰጥተዋል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ በእንግሊዘኛ ዩትራይን ፋይብሮይድስ (Uterine Fibroids) ወይም ማዮማስ (Myomas) ይባላል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ ምንድን ነው? የሚለውን ለመረዳት የማሕፀን ክፍሎችን ከማየት እንጀምር።

የማሕፀን በር፣ የማሕፀን ግድግዳ፣ የማሕፀን ትቦ እና የማሕፀን ፍሬ ናቸው ክፍሎቹ።

የማሕፀን ግድግዳ የራሱ ክፍሎች አሉት። የወር አበባ ሆኖ የሚፈሰው አካል አለ። ከእሱ ጀርባ የማሕፀን ጡንቻ አለ። ከማሕጸን ጡንቻ ጀርባ ደግሞ ሌላ ሽፋን አለ። ይህ ሽፋን የውጭ እና የመጨረሻው አካል ነው።

“የማሕፀን ግድግድ እጢ የሚወጣው ወይም የሚበቅለው ከጡንቻው አካል ነው” ይላሉ ዶ/ር ሞገስ።

አንድ የማሕፀን ጡንቻ ሕዋስ እየተባዛ “እንደ ድንች ዓይነት ሆኖ በተለያየ መጠን ይገኛል” ሲሉ ያስረዳሉ።

በጣም ዘገምተኛ የሆነ ዕድገት ቢኖረውም ዕድገቱ እየጨመረ ይሄዳል። እጢው የተለያዩ መጠኖችን ይይዛል።

መንስኤው ምንድን ነው?

ዶ/ር ሞገስ እንደሚሉት የማሕፀን እጢ መንስኤ እና አጋላጭ የሚባሉት የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው።

መንስኤውን ስንመለከት፣ የማሕፀን ግድግዳ አንድ ሕዋስ ራሱን በማባዛት የተለያየ መጠን እንዲደርስ የሚያደርገው የሆርሞን መጠን መዛባትን እናገኛለን።

ሕዋሱ እንዲባዛ እና እንዲያድግ የሚያደርገው የፕሮጀስትሮን ሆርሞን መጨመር ነው።

መባዛት ከጀመረ በኋላ መጠኑ እንዲጨምር የሚያደርገው የኤስትሮጅን ሆርሞን ልኬት እንደሆነ የሕክምና ባለሙያው ያስረዳሉ።

በተፈጥሮ የሆርሞን መዛባት (Polycystic ovarian syndrome) የሚባል ሕመም አለ።

ኤስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን ሆርሞኖች መጠንን በሰውነት ውስጥ ሊጨምሩ የሚችሉ እንደሆኑ ይናገራሉ።

ተጋላጭነትን ስናይ፣ አንደኛው በወሊድ ዕድሜ ክልል ውስጥ መሆን (ከ20ዎቹ እስከ 40ዎቹ) ነው።

“ዋነኛ የሚባለው በዚህ የወሊድ ዕድሜ ክልል ውስጥ መሆን ነው። ብዙዎች ግን መኖር አለመኖሩን አያውቁም። ለሌላ ሕክምና አልትራሳውንድ ሲነሱ ብዙ ሴቶች የማሕፀን ግድግዳቸው ላይ የተለያየ መጠን ያለው እጢ ይገኛል” ሲሉ ያብራራሉ።

አብዛኞቹ ምልክት እጢዎች ላይኖራቸው ቢችልም ትንሽም ቢሆን የማሕፀን ግድግዳ እጢ አላችሁ ይባላሉ።

ሌላው የወር አበባቸው ቀድሞ የመጣ ሴቶች ተጋላጭነት ነው።

ዶ/ር ሞገስ እንደሚሉት፣ ብዙ እርግዝና ያልነበራቸው ሴቶች ወይም መኻን ሴቶችም ተጋላጭ ይባላሉ።

ሌላው ከመጠን ያለፈ ውፍረት (Obesity) ያላቸው ሴቶች ተጋላጭነት ነው።

በተጨማሪም በዘር የሚመጣ ተጋላጭነትም አለ። ጥቁሮችን፣ ነጮችን፣ እስያውያንን እንዲሁም ሌሎችም የዘር ዓይነቶችን በማነጻጸር የተሠሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የጥቁር ሴቶች ተጋላጭነት ይጨምራል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ

የፎቶው ባለመብት, BSIP

ምን ያህል ሴቶች ላይ ይከሰታል?

ዶ/ር ሞገስ እንደሚሉት፣ ከ100 ሴቶች መካከል ከ10 እስከ 15 የሚሆኑት የማሕፀን ግድግዳ እጢ ይገኝባቸዋል። እነዚህ ምልክት የሚታይባቸው ናቸው።

ምልክት የማይታይባቸውን ስንመለከት፣ 100 ሴቶች አልትራሳውንድ ቢነሱ እስከ 70 በመቶው ይኖርባቸዋል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ ምልክት “የካንሰር ምልክት አይደለም” ይላሉ ሐኪሙ።

እጢዎችን ‘ሞኝ’ እጢ እና የካንሰር እጢ ብለን መክፈል እንችላለን።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ ‘ሞኝ’ እጢ የሚባለው ነው።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ምልክቶቹ ከሰው ሰው ይለያያሉ።

“በአብዛኞች ላይ የማሕፀን ግድግዳ እጢ ሲከሰት መጀመሪያ ላይ የሚቀመጠው ምልክት ምንም ምልክት አለኖሩ ነው” ይላሉ ባለሙያው።

እነዚህም ምንም ምልክት የሌላቸው (Asymptomatic) ይባላሉ።

ባለሙያዎች በሌላ ሕክምና ወቅት ነው እጢ እንዳለባቸው የሚነግሯቸው።

ምልክት አይተው ወደ ሕክምና የሚሄዱ ሴቶችን ብንመለከት በዋናነት የሚታዩት ምልክቶች ቀጣዮቹ ናቸው።

ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት የሚገጥማቸው ምልክት የወር አበባ መዛባት ነው።

የወር አበባ ማነስ ወይም መብዛት፣ አልያም ያለ ጊዜ ቶሎ ቶሎ መምጣት ሊሆን ይችላል።

ብዙዎቹ የወር አበባ መጠን መብዛት ይገጥማቸዋል። ይህም “እስከ ደም ማነስ” እንደሚያደርስ ባለሙያው ይናገራሉ።

የወር አበባ መጠን ቢዛባም ባይዛባም የወር አበባቸው ሲመጣ ከፍተኛ የሆነ ሕመም የሚገጥማቸውም አሉ።

በወር አበባ ወቅት ውስን ሕመም የሚገጥማቸው ቢኖሩም፣ የማሕፀን ግድግዳ እጢ ምልክት የሚባለው መንቀሳቀስ፣ ከቤት መውጣት ወይም ሥራ መሄድ የማያስችል ከእምብርት በታች የሚሰማ ጽኑ ሕመም ነው። ዲስሜኖሪያ (Dysmenorrhea) ይባላል።

የማሕፀን እጢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሌላው ምልክት ከመጠኑ ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም የእጢውን መጠን፣ ያለበትን ቦታ እና ብዛቱን ያማከለ ነው።

ከአንድ በላይ እጢዎች ሊኖሩ ይችላል። መጠናቸው የተለያየ ከሦስት እስከ ሃያ የሚደርሱ እጢዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

“ስለዚህ ስለ ምልክት ስናወራ ከመጠኑ፣ ከቁጥሩ እና ካለበት የማሕፀን ክፍል ተነስቶ ነው የሚታየው” ይላሉ ዶ/ር ሞገስ።

ከእጢ መጠን መጨመር ጋር በተያያዘ የሚመጣ ምልክት የመጫን (Pressure symptom) ነው። አንዳንዶች ከእምብርት በታች የመክበድ ስሜት ይገጥማቸዋል።

አንዳንዶች የእጢው መጠን ወደላይ እያደገ ሲመጣ ሆዳቸው የመሙላት ስሜት ይሰማቸዋል። የሆድ ማበጥም ይታያል።

ከማበጥም አልፎ ወደ ሽንት ቱቦ አካባቢ፣ የማሕፀን ጀርባ ማለፊያው ላይ ተጭኖ የሚይዝ ስሜት እንዳለ ይገልጻሉ።

እጢው የሽንት መተላለፊያ ቱቦዎችን ከዘጋቸው ኩላሊት ውሃ ቋጥሮ እንዲይዝ ሊያደርግ ይችላል።

አንጀትን ተጭኖ የሚይዝ ስለሆነም የሆድ ድርቀት (Constipation) ሊያመጣ ይችላል።

የሽንት ፊኛን የሚጫን ከሆነ ደግሞ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት ይገጥማል። ትንሽ ሽንት እየወጣ ብዙ ጊዜ ያመላልሳል።

ወደ ማሕፀን በር እጢው ተጠግቶ ካለ ደግሞ ሽንት ቶሎ ቶሎ ከመምጣቱም በተጨማሪ የሸንት አለመውጣት (Urinary retention) ይገጥማል። በቱቦ ታግዞ እስከ መሽናት ያደርሳል።

የማሕፀን ግድግዳ እጢ እና መኻንነት

ዶ/ር ሞገስ እንደሚሉት የማሕፀን ግድግዳ እጢ መኻንነት ሊያመጣ ይችላል።

“መኻን ሴት ስትመጣ መጀመሪያ የማሕፀን ግድግዳ እጢ ነው ብለን አናስብም። ሌሎች መኻንነት የሚያመጡ አሉ ወይስ የሉም? የሚለው ከተመረመረ በኋላ ብቸኛው ግኝት ከማሕፀን ግድግዳ እጢ ጋር የተያያዘ ከሆነ መኻንነቱን ያመጣው እሱ ነው ተብሎ ይወሰዳል” ይላሉ።

መኻን ከሆኑ ሴቶች መካከል ከሁለት እስከ አራት በመቶው መኻን የሆኑት በማሕፀን ግድግዳ ዕጢ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

እጢው የበቀለው የማሕፀን ቱቦ መግቢያ ላይ ከሆነ ወይም ለማሕፀን በር ቀረብ ብሎ ከሆነ ያለው የወንድ ዘር ፍሬ እንዳያልፍ ሊያደርግ ይችላል።

“ወጣ ያሉ” ምልክት የሚባሉት ከስንት አንድ ሴቶች ላይ የሚገኙ ናቸው።

ቀይ የደም ሕዋስ መብዛት አንደኛው ነው።

ከሆድ ማበጥ ውጪ እጢው የሚበቅልበት ቦታ ከማሕፀን ግድግዳ ጡንቻዎች ወደ ብልት ከንፈር ድረስ ሊመጣ እንደሚችል ሐኪሙ ያስረዳሉ።

እጢው አብጦ ብልት ከንፍር ላይ ሊገኝም ይችላል።

የማሕፀን እጢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትኛው ዓይነት እጢ የበለጠ ያሰጋል?

ሲምፕተማቲክ ማዮማ (Symptomatic myoma) ምልክት የሚያሳይ የማሕፀን እጢ ነው።

ምልክት ሲያሳይ ጤና ላይ እና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሯል ማለት ነው።

“ይሄ ከመጠኑ ጋር የሚገናኝ አይደለም። መጠኑ ትንሽ ሆኖም ምልክት ሊያሳይ ይችላል” ሲሉ ሐኪሙ ያብራራሉ።

በእርግጥ መጠኑ በጨመረ ቁጥር ምልክቶች የመታየታቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።

ነገር ግን ቁጥራቸው ብዙ ሆኖ መጠናቸው ከአራት እስከ አምስት ሴንቲ ሜትር ሲሆን ከፍተኛ ደም መፍሰስ ሊያመጡ ይችላሉ።

ከፍተኛ ደም መፍሰስ ካመጡ፣ የሽንት ፊኛ ከዘጉ እንዲሁም መጠናቸው ከስምንት ሴንቲ ሜትር በላይ ሆኖ ሕመም የሚያመጡ ከሆነ “የግድ ሕክምና ያስፈልጋል” ይላሉ።

መጠናቸው ከስምንት ሴንቲ ሜትር በታች ሆኖ ምልክት የማያሳዩ ከሆነ “ተጨማሪ ሕክምና አያስፈልግም። ክትትል ግን ያስፈልጋል” ይላሉ ባለሙያው።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሴቶች በስድስት ወር ወይም በዓመት አልትራሳውንድ መነሳት ያስፈልጋል። በምርመራው እጢው ምን ያህል ጨምሯል? የሚለው ይታያል።

የትኛዋ ሴት ምልክት እንደምታሳይ ወይም ምን ዓይነት ምልክት እንደምታሳይ ስለማይታወቅ “ቀድመው ወደ ሕክምና እንዲሄዱ እመክራለሁ።”

የእጢ መጠን እና ብዛት

በአማካይ አንድ እጢ ብቻ ሲኖር ትንሽ ቁጥር ይባላል።

ዶ/ር ሞገስ የማሕፀን ግድግዳ እጢዎች “እንደ ድንች ዓይነት” ሲሉ ይገልጿቸዋል።

መጠናቸው በአማካይ ሁለት ወይም ሦስት ሴንቲ ሜትር ሊሆን ይችላል። እነዚህ በብዛት ምልክት አይኖራቸውም።

በአብዛኛው ከስምንት ሴንቲ ሜትር በላይ ሆኖ ቁጥራቸው ከሦስት በላይ ሲሆን ምልክት ይታያል።

ሦስት ወይም አራት ሆነው በዚህ መጠን ሲገኙ የወር አበባ መብዛት ሊመጣ ይችላል።

“ብዙ የሚባለው እስከ ሃያ ወይም ሠላሳ ሲደርስ ነው” የሚሉት ዶ/ር ሞገስ እንደሚያስረዱት ከሆነ፣ መጠናቸው አንሶ በማሕፀን የተለያየ ግድግዳ የሚበቅሉ ናቸው።

አንዳንድ ሴቶች ላይ እጢው አንድ ብቻ ሆኖ እስከ 25 ኪሎ ግራም ሊደርስም ይችላል።

ምርመራ እስከሚደረግ ድረስ ማን ላይ የትኛው መጠን እና ብዛት እንደሚኖር ማወቅ እንደማይቻል ያክላሉ።

የማሕፀን እጢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕክምና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ ሕክምናው ስንመጣ፣ ሕክምና የሚደረገው ምልክቱን ለሚያሳዩ ሴቶች እንደሆነ የማሕፀን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ይናገራሉ።

ሕክምናው እንደ ሕመሙ ምልክት፣ ጥንካሬ እና የእጢው መጠን ይወሰናል።

ብዙ ደም ፈሶ እስከ ደም ማነስ (Anemia) ሲያደርስ የግድ እጢው በቀዶ ሕክምና መውጣት ይኖርበታል።

ምልክት ከሌለ ግን “በክትትል ደረጃ” እንደሚቆይ ያስረዳሉ።

ምልክት ከታየ በኋላ የመጀመሪያው አማራጭ በመድኃኒት ማከም ነው።

ለምሳሌ የወር አበባ መዛበት ተከስቶ ቀላል ሕመም ካለ የሆርሞን ማስተካከያ መድኃኒቶች ይሰጣሉ።

የወር አበባ ሕመም ከሆነ ደግሞ የሕመም ማስታገሻዎች ይሰጣሉ።

የእጢው መጠን እንዲቀንስ የሚሰጡ የሆርሞን መድኃኒቶችም አሉ። ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚወሰዱ ናቸው።

መድኃኒቶች እጢው መጠኑ እንዲቀንስ እና ወደ ቀዶ ሕክምና እንዳይገባ ያደርጋሉ።

“እነዚህ የሆርሞን መድኃኒቶች እንደ መሸጋገሪያ ናቸው። እጢውን መጠኑን ያሳንሱታል። መጠኑ ካነሰ ለቀዶ ሕክምና ይቀላል። ማለትም የሚፈሰው የደም መጠን እንዲቀንስ እና በቀዶ ሕክምና የሚገጥም የጎንዮሽ ጉዳት እንዲቀንስም ያግዛል” ይላሉ ሐኪሙ።

ዕድሜዋ ወደ 40ዎቹ እየተጠጋ ላለች ሴት መድኃኒት በመስጠት እጢው መጠኑ እንዲቀንስ (እንዲሟሟ) ማድረግ ይቻላል።

ሌላው የቀዶ ሕክምና አማራጭ ነው።

ይህ የሚወሰነው ሴቲቷ መውለድ ትፈልጋለች ወይስ አትፈልግም? በሚለው እንደሆነ ይገልጻሉ።

“መውለድ ካልፈለገች ወይም ወልዳ ከጨረሰች፣ የተሻለ የሚባለው አማራጭ ሙሉ ማሕፀንን ማውጣት ነው። መውለድ የምትፈልግ ከሆነ እጢውን ብቻ ፈልፍሎ ማውጣት (myomectomy) አማራጭ ነው” ሲሉ ያብራራሉ።

አንዳንድ ጊዜ ልጅ ፈልገውም እጢው የበቀለበት ቦታ እና መጠኑ እጢውን ብቻ ለማውጣት የማይፈቅድ ከሆነ (ለምሳሌ ወደ ማሕፀን በር በትልቁ የበቀለ ከሆነ) እጢውን ፈልፍሎ ከማውጣት ይልቅ ሙሉ ማሕፀንን ማውጣት ይቀላል።

ይህ የሚደረገው የሚፈሰው ደም እና በቦታው የሚጎዱ የሰውነት ክፍሎች ከፍተኛ ስለሚሆኑ ነው።

የተወሰኑ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ፣ በማሕጸን የውስጥ በኩል የበቀለ እጢ ሆኖ በቀላሉ የሚገኝ ከሆነ (Hysteroscopy) ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይቻላል።

እጢው በጣም ትልቅ ሆኖ በሆድ በኩል መገባት ካለበት የላፓራስኮፒ (Laparoscopy) ቀዶ ሕክምና ይደረጋል።

በጨረር እጢው ያለበት ቦታ መድረስ ከተቻለ በጨረር ሙቀት እንዲቀልጥ (እንዲሟሟ) ማድረግን (Magnetic resonance) ጨምሮ ሌሎችም ዘመኑ የደረሰባቸው የቀዶ ሕክምና ዓይነቶች አሉ።

ምልክት አልባነት

የማሕፀን ግድግዳ እጢ ምልክት አልባነቱ “ምልክቱ” እንደሆነ ዶ/ር ሞገስ ይናገራሉ።

ስለ ቅድመ ጥንቃቄ ለማውራት ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ነው።

ለምሳሌ ከማሕፀን በር ካንሰር እና ከማሕፀን ፍሬ ካንሰር ጋር የሚመሳሰል አይደለም።

እነዚህ ሕመሞች በየጊዜው መመርመርን (Screening) ሲጠይቁ፣ የማሕፀን ግድግዳ እጢ ግን ይህን አይጠይቅም።

በየጊዜው መመርመር “ከወጪም፣ ከሥነ ልቦና ጫናም፣ በሽታው ከሚያመጣው ጉዳት ጋር ካለመመጣጠን አንጻር አይመከርም” ይላሉ ዶ/ር ሞገስ።

የዓለም ጤና ድርጅትም እንደ ማሕፀን ካንሰር ያለ ቅድመ ምርመራን ለማሕፀን ግድግዳ እጢ አይመክርም።

ዕጢው እንዳይመጣ ምን ይደረግ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ መከላከል እንደማይቻል ነው ያስረዱት።

“መኻንነት በተፈጥሮ የሚመጣ ነው። የወር አበባ በጊዜ መምጣትም በተፈጥሮ የሚመጣ ነው። ሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠንም በተፈጥሮ የሚመጣ ነው። ዘርንም መቀየር አይቻልም” ይላሉ።

ሆኖም ግን ወደ አመጋገብ ስንመጣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት መቀነስን ይመክራሉ። ከማሕፀን ግድግዳ እጢም ለከፉ ሌሎች ሕመሞች ተጋላጭ ስለሚያደርግ አመጋገብን ማስተካል ይመከራል።

ሌላው ሕመም ሲሰማ በፍጥነት ወደ ሕክምና መሄድ ነው።

“የወር አበባዬ ይበዛል፣ ሕመም ይሰማኛል” እያሉ ጊዜ ከመውሰድ በፍጥነት ወደ ሕክምና መሄድን ሐኪሙ ይመክራሉ።

“ማኅበረሰባችን ወደ ሕክምና መሄድ አያዘወትርም። እጢው በጣም ከፍ ብሎ ሆድ ማበጥ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ መጠበቅ አያስፈልግም” ይላሉ።

ሕመሙን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያደርሰው ወደ ሕክምና ሄዶ አለመታየት እንደሆነም ያስረግጣሉ።

የእጢው መጠን ማደግ ወይም ማነስ በቀዶ ሕክምና የሚፈጠረውን ችግር ከፍ ከማድረጉ ውጪ እንደ ሌሎች እጢዎች “ገዳይ” ተብሎ የሚቀመጥ አይደለም ሲሉም ያስረዳሉ።