ሃምሳ በመቶ የሚሆኑትን የዓለማችንን ሴቶች የሚያሰቃየው ‘ሲስት’ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በናይሮቢ የቪዲዮ አርታኢ የሆነችው መሊሳ ዋይሪሙ ያለማቋረጥ ሽንት ሽንት ማለት፣ ስትሸናም የመቆጥቆጥ እና የማቃጠል ስሜት ይሰማት ጀመር።
በዚህ አላበቃም ጀርባዋንም ከፍተኛ ህመም ተሰማት። ህመሙ አላስቆም አላስቀምጥ ሲላት ወደ ህክምና ማዕከል አመራች። የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን (ዩቲአይ) እንደሆነ ተነገራት።
በወቅቱ ዕድሜዋ 21 ዓመት ነበር።
“ዩቲአይ የሚባል ነገር እንዳለ እንኳን አላውቅም ነበር” በማለት ዋይሪሙ ትናገራለች።
ለሰባት ቀናት ያህል በርከት ያሉ አንቲ ባዮቲክ መድኃኒቶች ተሰጣት፣ እንዲሁም ብዙ ውሃ እንድትጠጣ ተመከረች።
ነገር ግን ይሰሟት የነበሩ የህመም ምልክቶች አልቆሙም፤ ጭራሽ አንዳንድ ጊዜ ጠንከር ማለት ጀመሩ። የጀርባዋ ህመም ወደ ሆዷ ተዛመተ። ያለማቋረጥ የድካም ስሜት ይሰማታል፣ ነገር ግን መንጋለልም ሆነ መተኛት ተሳናት። እንቅልፍ ማጣቷ ድካሟን አባባሰው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በሥራዋ ላይ እክል መፍጠር ጀመረ። የህክምና ባለሙያዎች የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመጣባት በወሲብ ምክንያት እንደሆነ ቢነግሯትም በወቅቱ ምንም አይነት የወሲብ ግንኙነት እየፈጸመች አልነበረም። ዶክተሮቹም እያዳመጧት እንዳልነበርም ነው የተሰማት።
ዶክተሮች ህመሟ ይህ ይሆናል በሚል መድኃኒቶችን ቢያዙላትም ችግሩን ሊፈቱት አልቻሉም።
ዋይሪሙ ለዓመታት ያየቻቸው ስድስት ዶክተሮች በዩቲአይ ላይ በቂ የሆነ ሥልጠና ስለሌላቸው ያሳዝኗታል። ከዓመታት በኋላም የራሷን አማራጭ በመውሰድ ምርምሮችን እና መረጃዎችን መሰብሰብ ጀመረች።
በኢንተርኔትም ላይ በርካታ መረጃዎችን አገኘች፤ ይህም ብቻ አይደለም ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸውን ሴቶችም አገኘች።
ይህንን ህመም በተመለከተ ምን ያህል ክፍተት እንዳለ ካየች በኋላ “ዩቲአይ ፍሪ” የሚባል ወትዋች እና ተሟጋች ድርጅትንም አቋቋመች።
ዋይሪሙ የህመም ምልክቶቿ እንዳይባባሱ ለማድረግ አመጋገቧን መቀየር ጀመረች። ከአራት ዓመታት በኋላም የህመም ምልክቶችን መቆጣጠር ብትችልም ችግሩ ግን ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም።
በተደጋጋሚ የሕክምና ባለሙያዎችን የሚያማክሩ እና ህመማቸው ያልዳነ እንደ ዋይሪሙ ያሉ በርካቶች ናቸው። የሚሰጣቸው ሕክምና ለአጭር ጊዜ መፍትሄ ያመጣላቸው ቢኖርም የተወሳሳበ ዩቲአይ ላለባቸው በርካታ ህመምተኞች ግን አይሰራም።
የተወሳሰበ ዩቲአይ የሚባለው አብዛኛውን ጊዜ ሕክምና የማይሳካ ሲሆን፣ በአሜሪካ ብቻ 250 ሺህ ሴቶች በዚህ ህመም ይሰቃያሉ።
በርካታ ህመምተኞች፣ ዶክተሮች እና ተመራማሪዎች መደበኛውም ሆነ የተወሳሰበው ዩቲአይ ላይ የሚደረገው ትግል ለውጥ ባለማሳየቱ ቢያስከፋቸውም፤ አሁንም ተስፋ እንደሰነቁ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙም ያልተረዳነው ኢንፌክሽን
የዩቲአይ (የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን) ምልክቶች ከሚባሉት ውስጥ በሚሸኑበት ወቅት ህመም ወይም ማቃጠል፣ ድንገተኛ የመሽናት ፍላጎት ወይም በተደጋጋሚ መሽናት፣ ደም የተቀላቀለበት የሚስል ወይም መጥፎ ሽታ ያለው ሽንት፣ የጀርባ ወይም የሆድ ህመም፣ ሙቀት ሙቀት ወይም ብርድ ብርድ ማለትን ያጠቃልላል።
በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች ላይ የተደረገው አብዛኛው ምርምር መሠረቱን ያደረገው በአይጦች ላይ በተደረገው ሙከራ ነው። አይጦች በተፈጥሮ ለዚህ በሽታ ስለማይጋለጡ አንዳንድ ባለሙያዎች በምርምሩ አስተማማኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ህመም ምክንያቱ ኢ ኮሊ የተሰኘው ባክቴሪያ ነው። ነገር ግን ሌሎች ባክቴሪያዎችም ሊያመጡት ይችላሉ፤ በዚህ ላይ ያለው ምርምር ውስን ነው። አልፎ ተርፎም ለየት ያሉ የኢ ኮሊ ባክቴሪያ ዝርያዎች ላይ ብዙም እንደማይታወቁ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዩሮሎጂካል ባዮሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጄኒፈር ሮን ይናገራሉ።
ዩቲአይ ሲስት ወይም የፊኛ እብጠትን እንደሚያስከትል በዩናይትድ ኪንግደም ኒውካስል ዩኒቨርስቲ የጤና ባለሙያ የሆኑት ክሪስ ሃርዲንግ ያስረዳሉ። ዩቲአይ (የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን) አይነቶች ብዙ ቢሆንም ሲስት የተለመደው ነው።
ዩቲአይ ሴቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቃ በሽታ ነው። በዓለማችን ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ይጠቃሉ። በተለይም በወጣቶች እና ወሲብ በሚፈጽሙ ሴቶች ላይ እንዲሁም ያረጡ ሴቶች ላይ እንደሚታይ ሮን ይናገራሉ።
ሆኖም ጄኔቲክስ፣ ሆርሞን እንዲሁም የሰውነት ሁኔታም የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ። ሴቶች ከወንዶች ይልቅ አጠር ያሉ የሽንት ቱቦዎች ስላላቸውም ባክቴሪያዎች በቀላሉ ወደ ፊኛቸው በመድረስ ያጠቋቸዋል።
ዩቲአይ ኢንፌክሽን ቢሆንም ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም። ሆኖም ኢንፌክሽኑን ያስከተሉት ባክቴሪያዎች በወሲብ ወቅት ወደ ሌላኛው ሰው ሊዛወሩ ይችላሉ።
ወንዶች በዩቲአይ የሚጠቁት በዕድሜ ከፍ ሲሉ ነው። በተለይም አረጋውያን ወንዶች ይጠቃሉ። በአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ዩቲአይ በጣም ከተለመዱት ኢንፌክሽኖች ዓይነት ዋነኛው ነው።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዩቲአይ 150 ሚሊዮን ሰዎችን የሚያጠቃ ሲሆን፤ በተለይም በዓለማችን ያሉ ሰዎች በዕድሜ እየበለጸጉ በሄዱ ቁጥር የመስፋፋቱም ሁኔታ እንደሚያሻቅብ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሴት የመሆን አካል ተደርጎ የሚታየው ኢንፌክሽን
ዩቲአይ በበርካታ ሴቶች በመከሰታቸው እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜም የተወሳሰቡ ባለመሆናቸው በርካታ የጤና ባለሙያዎች መደበኛ ሴት የመሆን የሕይወት አካል አድርገው በማየትም ክትትል አያደርጉም። ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀላል የነበሩ ህመሞች ሲወሳሰቡ እና አደጋም ሲጋርጡ የሚታዩት ብዙ ናቸው።
ልክ እንደ ዋይሪሙ ቢያንስ 25 በመቶ የሚሆኑት የዩቲአይ ኬዞች ወደ ውስብስብ እና በተደጋጋሚ የማጋጠም ሁኔታ ይቀየራሉ።
ቢያንስ በስድስት ወራት ሁለት ጊዜ ወይም በዓመት ሦስት ጊዜ ኢንፌክሽኑ የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ አንዳንዶች ከዚህ በበለጠ ይደጋገምባቸዋል። ከተደጋጋሚ ዩቲአይ በተጨማሪ ስር የሰደደ ወይም ወደማይድን ዩቲአይ ይቀየራል።
አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ የህመም ምልክቶች ጋር ሙሉ ሕይወታቸውን ለማሳለፍ የሚገደዱ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ግን ብዙም እውቅና ሲሰጠው አይታይም።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ምርመራዎች
ቀላል ዩቲአይ ቢሆን እንኳን በአብዛኛውን ጊዜ በምርመራ አይገኝም። ዩቲአይን ለመመርመር የተለመደው ዘዴ መመርመሪያውን ሽንት ውስጥ በመንከር እንዲሁም ዩሪን ካልቸር ተብሎ የሚጠራው ምርመራ ነው። ነገር ግን እነዚህ ምርመራዎች ሁልጊዜም አያስተማምኑም።
በአንጻሩ አዲስ የሞለኪውላር ምርመራዎች ዩቲአይን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም በሽታ አምጭ ተህዋሲያንን በመለየት ውጤታማ ቢሆኑም ውድ ናቸው። በተለምዶ የሚደረጉት የሽንት ምርመራዎች ርካሽ ቢሆኑም በአብዛኛውን ጊዜ የተሳሳቱ ናቸው።
ዩሪን ካልቸር ተብሎ የሚጠራው ከሽንት ናሙና የተወሰደ ባክቴሪያን በላብራቶሪ ውስጥ በማሳደግ የሚደረግ ሲሆን፣ ይህ ምርመራ በ1950ዎቹ የኩላሊት ህመም ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶችን ለመመርመር የተዘጋጀ ነው።
በሌላ አገላለጽ የዩቲአይ የተለመደው ምርመራ ጊዜው ካለፈበት እና ለዩቲአይ ተብሎ ካልተዘጋጀ የሚደረግ ነው።
ጊዜ ያለፈበት ትምህርት
ልክ እንደ ምርመራው፤ የሕክምና ትምህርቱም ጊዜ ያለፈበት ነው። ሃርዲንግ የሕክምና ተማሪ በነበረበት ወቅት የሽንት ፊኛ ጽዱ እና ከባክቴሪያም ነጻ መሆኑን ነበር የተማረው። ይህ በርካቶች የተሳሳቱበት እሳቤ በሽንት ፊኛ ውስጥ ባክቴሪያዎች እንዴት ገቡ ለሚለው ግራ መጋባትን አስከትሏል።
ዛሬም ድረስ ሽንት ከባክቴሪያ ነጻ ነው ብለው በስህተት የሚያምኑ የሕክምና ተማሪዎችን ሮን ያስተምራል።
ተመራማሪዎች በዩቲአይ ላይ ያላቸው ማስረጃዎች በቂ አለመሆኑን ቢያውቁም፣ ይህ መረጃ በህክምናዎች ላይ ተግባራዊ እንደማይሆኑ ስር የሰደደ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ዘመቻ ዳይሬክተር የሆኑት ካሮሊን አንድሪው ይናገራሉ።
ስር የሰደደ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ወይም ተደጋጋሚ ዩቲአይ ላለባቸው ሰዎች በተለምዶ ከሚደረጉ ምርመራዎች በላቀ መልኩ በህመም ምልክቶቻቸው ላይ የተመሠረተ ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ይናገራሉ።
“የሴቶችን ህመም ሆነ የህመም ምልክቶቻቸውን በቁም ነገር መውሰድ ይገባል” በማለት ሮን ይናገራሉ።
ዩቲአይ ለምን ችላ ተባለ ለሚለው ሮን የሚሰጣቸውም ምክንያቶች የሴቶች በሽታ ተብሎ ስለሚታመን፣ አረጋውያንን ቢያጠቃም የከፋ ነው ተብሎ ስለማታሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ምንም እንኳን ዩቲአይ ገዳይ ባለመሆናቸው እንደሌሎች ኢንፌክሽኖች ተመሳሳይ የገንዘብ ድጋፍ እና ትኩረት አይሰጣቸውም። ነገር ግን ዩቲአይ የኩላሊት እና የሌሎች ኢንፌክሽኖች ምክንያት በመሆን ሞት ሊያስከትል ይችላል።
“የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ተገቢው የሆነ ሕክምና የማያገኝ ከሆነ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በርካቶች አይገነዘቡም” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንቲባዮቲክ (የፀረ- ተህዋስያን) ችግር
ትክክለኛውን ምርመራ አግኝተው ዩቲአይ መሆኑ የታወቀላቸው ዕድለኛ ሴቶች ሕክምናው ቀላል አይሆንም።
በተለይም በእንግሊዝ ዩቲአይ ለያዛቸው ሴቶች መድኃኒት የሚሰጣቸው ለሦስት ቀናት ብቻ ሲሆን፣ ውስብስብ ዩቲአይ ላለባቸው ወንዶች ደግሞ ሰባት ቀናት ነው።
ይህ በወንዶች እና በሴቶች መካከል የሚታየው የሕክምና ልዩነት ለአንዳንዶች ተስፋ አስቆራጭ ነው። ሮን ለሴቶች ለሦስት ቀናት የሚሰጡ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በቂ እንዳልሆኑ ያምናሉ።
በዋነኝነት መድኃኒቶች በሦስት ቀናት እንዲወሰኑ የተደረጉት ፀረ ተህዋሲያኑ መድኃኒቶቹን የመቋቋም ሁኔታ እንዳያዳብሩ ነው። ይህ ትክክል ቢሆንም በህመሙ የሚሰቃዩ ሴቶችን ችላ ያለ ነው ሲሉ ሮን ይከራከራሉ።
በተለይም በቂ ባልሆነ ሕክምና ኢንፌክሽኖቹ ስር የሚሰዱ ወይም ተደጋጋሚ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ጠንከር ያሉ ባክቴሪያዎች የሚደበቁበት ሁኔታም አለ።
በእነዚህ ሁኔታዎች ተጨማሪ አንቲባዮቲክ ሊያስፈልግ ይችላል። ተደጋጋሚ ዩቲአይም ሲሆን ህመምተኞች ረዘም ላለ ጊዜ የሚወሰድ አንቲባዮቲክስ ይሰጣቸዋል።
የወደፊት ተስፋዎች
የዩቲአይን ምርመራ እና ሕክምና ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ውጤታማነት ላይ የታየውንም ክፍተት ለማሻሻል እና ከሰውነት ጋር በተሻለ መንገድ የሚዋሃድበትን ሁኔታ ለመጨመር እየሞከሩ ነው።
ባለፈው ዓመት የመድኃኒት አምራች ኩባንያው ጂኤስኬ በአፍ የሚወሰድ አንቲባዮቲክ ላይ ተስፋ ሰጪ የሙከራ ውጤቶችን መዝግቧል። መድኃኒቱ ዕውቅና ካገኘም ያልተወሳሰቡ ዩቲአዮችን ለማከም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የተሠራ የመጀመሪያው አንቲባዮቲክ ይሆናል።
በተጨማሪም በሴት ብልት የሚገባ የኤስትሮጅን ሆርሞን ተጨማሪ መድኃኒት ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ ሲሆን፣ እየተዘጋጁ ያሉ የዩቲአይ ክትባቶችም ተስፋን ሰጥተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሽንት ቱቦ ላይ መሠረታዊ ምርምሮችም ቀጥለዋል።
ምርምሮቹ ለዘመናት በአይጥ ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሮን እና የሥራ ባልደረቦቹ የሰውን ፊኛ በ3ዲ ሞዴል ቀርጸው እውነተኛውን የአካል ክፍል ዝርጋታ እና ፍሰትን በማስመሰል እንዲሁም በእውነተኛ ሽንትም እየሰሩ ይገኛሉ። ይህም የወደፊቱን ሁኔታ ብሩህ አድርጎታል።












