ኮቪድ እና ሌሎች ተህዋሲያን ከቤተ ሙከራ እንዴት ሾልከው ሊወጡ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከሰሞኑ ስለኮቪድ አነሳስ እያነሳሱ ነው።
ተህዋሲው ከቤተ ሙከራ እንዳመለጠ በአያሌው ጠርጥረዋል። ነገሩ ከጥርጣሬም ከፍ ያለ ይመስላል።
ለምሳሌ ዶ/ር ሮበርት ሬድፊልድ ተህዋሲው ከቤተ ሙከራ እንደወጣ ነው በጽኑ የሚያምኑት።
ዶ/ር ሮበርት ተራ ሰው አይደሉም። የአሜሪካ የበሽታ መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) አለቃ የነበሩ ናቸው።
ተህዋሲው ከቻይና ቤተ ሙከራ ወጥቶ ነው ሚሊዮኖችን የፈጀው ብለው ማመንን መርጠዋል።
ይህን መላምት በማመን ረገድ ዶ/ር ሮበርት ብቻቸውን አይደሉም።
የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ኃላፊ ክሪስቶፈር ሬይም መላምቱን ይጋራሉ፤ ያላንዳች ማመንታት።
ክሪስቶፈር ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ “መሥሪያ ቤቴ ባደረገው ምርመራ የደመደመው ተህዋሲው ከቻይና ቤተ ሙከራ ሾልኮ ሳይወጣ እንዳልቀረ ነው” ብለዋል።
ታዲያ አነዚህ ባለሥልጣናት ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ይህን ለማለት ያበቃቸው ምንድነው?
ቢያንስ በቂ ጊዜ ወስደው፣ በቂ ምርመራ አድርገው እዚህ ለድምዳሜ የቀረበ መላምት ላይ እንደደረሱ ይገመታል።
ለመሆኑ ከዚህ ቀደም አደገኛ ተህዋሲያን ከቤተ ሙከራ አምልጠው ሕዝብ ፈጅተው ያውቃሉ?
ከቤተ ሙከራ ያመለጠው የፈንጣጣ ተህዋሲ
አዎ! ከዚህ ቀደም ያመለጡ ተህዋሲያን አሉ።
አንዱ ለምሳሌ ፈንጣጣ ነው።
የፈንጣጣ ተህዋሲ ጉድ አፍልቶ ያውቃል።
ነገር ግን በ1977 (እአአ) ወዲህ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል ነው የሚባለው። ከመጥፋቱ በፊት ግን ሕዝብ አጥፍቷል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ብቻ 300 ሚሊዮን ሕዝብ የጨረሰ ገዳይ ተህዋሲ ነበር።
አንድ ወቅት ከቤተ ሙከራ አመለጠና አዲስ ሽብር ፈጠረ።
ነገሩን ለመረዳት የ40 ዓመቷ ጃኔት ፓርከርን ታሪክ በአጭሩ ማወቅ ያሻል።
ወ/ሮ ጃኔት በበርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ የሕክምና ፎቶ ባለሙያ ነበረች። መቼ? በፈረንጆቹ 1978።
በቤተ ሙከራ ክፍል ሳለች ተህዋሲ አምልጦ ያዛት። እንዴት ያዛት? እስከዛሬ አይታወቅም።
“ብቻ ልክ ተህዋሲው ከቤተ ሙከራ እንደያዛት ሲታወቅ ሽብር ሆነ። በበርሚንግሃም ብቻ አይደለም ጭንቅ የሆነው። በዓለም ጤና ድርጅት፣ በብሪታኒያ መንግሥት ዘንድም ፍርሃት ረበበ” ይላሉ ፕሮፌሰር አላስዴር ጌዴስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሮፌሰሩ ይህ ሲሆን በበርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ የተላላፊ በሽታዎች ክፍል ኃላፊ ነበሩ። የዛሬ 40 ምናምን ዓመት ነው ታዲያ።
ፈንጣጣ እጅግ ተዛማች ተህዋሲ ነው። ለዚያም ነው 300 ሚሊዮን ሕዝብ የጨረሰው።
ለምሳሌ ከያዛቸው ሰዎች ከሦስቱ አንዱን ይገድላል።
ታዲያ ይሄ ተህዋሲ ከምድረ እንግሊዝ ጠፋ በተባለ በዓመቱ ነበር ከበርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ ከምርምር ቤተ ሙከራ ሾልኮ አገር ያሸበረው።
ወ/ሮ ጃኔት ፓርከር እንዴት እንደተያዘች አሁንም ድረስ ግልጽ ያለ መረጃ የለም።
ይሁንና ቤተ ሙከራ ሳለች የተከሰተ እንደሆነ የሚጠረጥር የለም።
ተህዋሲው በሦስት መንገድ ሊሆን ይችላል ያመለጠው፤ እንዲሁ በአየር፣ ወይ በአንዳች ንክኪ ወይ ደግሞ በተበከሉ የቤተ ሙከራ መሣሪያዎች አማካይነት።
ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ጥብቅ ጥበቃ የሚደረገውም ለዚሁ ነው። በጥንቃቄ ጉድለት በምርምር ላይ ያለ ተህዋሲ ካመለጠ ሕዝብ ይፈጃል።
ወ/ሮ ፓርከር ጠፍቷል፣ ቤተ ሙከራ ውስጥ ብቻ ነው ያለው በተባለ ተህዋሲ መያዟ ከታወቀ በኋላ ከፍተኛ ጥበቃ እና ክትትል ተደረገላት፣ ለይቶ ማቆያ ገባች። እናቷ ብቻ ተያዙ።
ወ/ሮ ፓርከር ትንሽ ቆይታ ሞተች። እናታቸው ለጊዜው ተረፉ።
የወ/ሮ ፓርከር አባት አቶ ፍሬድሪክ ደግሞ በ77 ዓመታቸው የልጃቸው በአጭር መቀጨት፣ በተለይም ደግሞ ሞተ በተባለ ተህዋሲ እንዳትሆን ሆና በመሞቷ ልባቸው ተሰበረ። ይኸው ሐዘን ያመጣው የልብ ድካም ገደላቸው።
ከአባት እና ልጅ በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሞቱ። የበርሚንግሃም ዩኒቨርስቲ የፈንጣጣ ተህዋሲ ቤተ ሙከራ ኃላፊ ደግሞ ራሳቸውን አጠፉ።
ምናልባት የኮቪድ ተህዋሲም እንደ ፈንጣጣ ከቤተ ሙከራ አምልጦ ይሆን ዓለምን ያንቀጠቀጠው?
ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው ተህዋሲያን
የበርሚንግሃም አደጋ ከተከሰተ በኋላ ዓለም ከእንግዲህ ትምህርት ወስጃለሁ አለ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከእንግዲህ የፈንጣጣ ምርምር ክምችት የሚኖረው በአትላንታ አሜሪካ የሲዲሲ ማዕከል እና በሳይቤሪያ ሩሲያ ውስጥ ብቻ ነው ብሎ ከአገሮች ጋር ተፈራረመ።
እነዚህ ሁለቱ ቤተ ሙከራዎች ብቻ የተመረጡት ጥበቃቸው አስተማማኝ ነው፤ ተህዋሲ በምንም አያመልጥም ተብሎ ነው።
ይሁንና እነሱም ቢሆኑ ከአስደንጋጭ አጋጣሚ አላመለጡም።
በፈረንጆቹ 2014 ለምሳሌ አንድ የሲዲሲ ሠራተኛ አንትራክስ ናሙናን በተገቢው ሁኔታ ሳያመክን ይቀርና በቤተ ሙከራው ያሉ ሠራተኞችን ለአደጋ አጋልጦ ነበር።
በኋላ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ተደረገና ክስተቱ ሞት ሳያስከትል ተያዘ።
አሁን አሁን በተለይ ከኮቪድ በኋላ በአደጉ አገራት የሚገኙ የቤተ ሙከራ ማዕከሎች ተህዋሲ በእንዝህላልነት እንዳያመልጥ ከፍተኛ ጥበቃ ማድረግ ጀምረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሌሎች አደገኛ አጋጣሚዎች
ጥበቃ ቢጠናከርም ታዲያ ችግር ማጋጠሙ መቼ ይቀራል?
በተለይ በቤተ ሙከራ የሚሠሩ ሠራተኞች እና በቤተ ሙከራው አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም አደጋ ላይ ናቸው።
ለምሳሌ በፈረንሳይ አንድ ቤተ ሙከራ ኤሚሊ ጁሜይን የተባለች ሳይንቲስት በሰው ልጆች ሲጄዲ (CJD) የሚባል በሽታን የሚያመጣ፣ በእንሰሳት ደግሞ ቢኤስኢ (BSE) የተባለ ደዌን ለሚያስከትል ተህዋሲ ተጋለጠችና ከ10 ዓመት በኋላ ሞተች።
ገና በ33 ዓመቷ ተቀጠፈች።
ደግነቱ ተህዋሲው እሷን ቀጠፈ እንጂ ከቤተ ሙከራ አላመለጠም።
ይሁንና እሷ በተህዋሲው እንደተያዘች ቢታወቅም ለዚያ የሚሆን ክትባት ባለመፈልሰፉ ሕይወቷን የሚታደግ አልነበረም።
በሰሜን ምዕራብ ቻይና፣ ላንዡ ከተማ ደግሞ በአንድ የምርምር ጣቢያ እንዲሁ አንድ ተህዋሲ ሾልኮ የ10 ሺህ ሰዎችን ጤና አደጋ ላይ ጥሎ ያውቃል።
ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካል ማጽጃዎች ዝቃጭን ለማከም ይውሉ ነበር በዚያ አካባቢ። ከዚያ ተረፈ ምርት ደግሞ በሩሴላ የተባለ የእንሰሳት ባክቴሪያን ለማከም ክትባት ተሠራ።
ይህ ክትባት ታዲያ ሌላ ጣጣ ይዞ መጣ።
በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ጉንፋን ቢጤ ይይዛቸው ጀመር። ራሴን አመመኝ፣ ፈለጠኝ ማለት አበዙ።
ከዚህ ቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነገር እንደሆነ ታወቀ። ብዙዎች ካሳ ተከፈላቸው።
በኋላ ይሄ ኬሚካል በቀዝቀዛው ጦርነት ጊዜ ባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ ለመሥራት አሜሪካ እና ባላንጣዋ ሶቭየት ኅብረት ተጠቅመውበታል።
ይሄ ሁሉ ሐተታ ምን ለማለት ነው፤ ተህዋሲዎች ከቤተ ሙከራዎች አያመልጡም አይባልም።
ምናልባት አሜሪካ ከሰሞኑ ተህዋሲው ከቻይና ቤተ ሙከራ አምልጦ ነው ለዚሁ ሁሉ የዳረገን ስትል ነገሩ በባላንጣ ላይ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ብቻ ላይሆን ይችላል።
በእርግጥም ኮቪድ ተህዋሲ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ሽፍታ ተህዋሲ ሊሆንም ይችላል፤ በእንዝህላልነት ይሁን በሌላ ባይታወቅም።












