ስለ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኤክስቢቢ.1.5 ምን እናውቃለን? ምን ያህልስ አስጊ ነው?

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲስ የኮሮናቫይረስ ንዑስ-ዝርያ (sub-variant) አሜሪካ ውስጥ ስጋት ሆኗል። በከፍተኛ መጠንም እየተሰራጨ ነው። ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደምም እየታየ ነው።

ኤክስቢቢ.1.5 የተባለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን ቅጥያ ነው። ከኦሚክሮን ቀድሞ አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ እና ዴልታ የተባሉ የቫይረሱ ዝርያዎች ነበሩ።

እአአ በ2021 መባቻ የተስፋፋው ኦሚክሮን ከሌሎቹ ዝርያዎች ጠንካራ ሲሆን፣ ከእሱ በላይ በፍጥነት የሚስፋፉ ሌሎች ንዑስ-ዝርያዎችንም ፈጥሯል።

የአዲሱ ኤክስቢቢ.1.5 ዝርያ ምልክቶች ከኦሚክሮን ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ ቢታመንም እርግጠኛ ለመሆን ጊዜው ገና ነው።

በቫይረሱ የተያዙ ብዙ ሰዎች እንደ ጉንፋን ያለ ምልክት ነው የሚያሳዩት።

አዲሱ ዝርያ ከቀድሞዎቹ ይጠነክራል?

አዲሱ ዝርያ የተገኘው ኤክስቢቢ ከተባለ ሌላ ዝርያ ሲሆን፣ ይህም ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ እየተሰራጨ ነበር።

በወቅቱ በጤና ተቋም አመራሮች “አስጊ ዝርያ” አልተባለም ነበር።

ኤክስቢቢ የሰዎችን በሽታ የመቋቋም አቅም የሚያሸንፍ ጉልበት ቢኖረውም፣ የሰዎችን ሕዋስ መጉዳት ሳይቻለው ቀርቷል።

በለንደኑ ኢምፔርያል ኮሌጅ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ዌንዲ ባርክሌይ እንዳሉት፣ ኤክስቢቢ.1.5 የዘረ መል ለውጡ (mutation) ኤፍ486ፒ ይባላል።

ኤክስቢቢ ያልቻለውን የሰዎችን ሕዋስ ማጥቃትን አዲሱ ዝርያ የሚያስችለው የዘረ መል ለውጥ አለው። ይህም በሽታ የመቋቋም አቅምን ይረታል። ስለዚህም ሕመሙ በቀላሉ ይሰራጫል።

የዝርያው ዝግመተ ለውጥ፣ የተጋላጩን ሰው በሽታን የመከላከል አቅም ማጥቃት የሚችልበትን መንገድ የሚያሻሽልበት እንደሆነ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ሳይንቲስቶች በዚህ ሳምንት እንዳሉት፣ አዲሱ ዝርያ እስካሁን ከታዩት ንዑስ-ዝርያዎች በተለየ የማደግ አቅም አለው።

ዝርያው ከሌሎቹ የኦሚክሮን ዝርያዎች አንጻር የበለጠ አስጊ ወይም ጠንካራ ስለመሆኑ ግን ምንም ጠቋሚ መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የቤተ ሙከራ ምርምሮችን፣ የሆስፒታል መረጃ እና በዝርያው የመያዝ መጠንን በቅርበት እንደሚከታተል ገልጿል።

አዲሱ ዝርያ የት እየተሰራጨ ነው?

በአሜሪካ ከ40 በመቶ በላይ የኮሮናቫይረስ ሕመሞች መነሻቸው አዲሱ ዝርያ እንደሆነ ተገልጿል። በአገሪቱ ጉልህ ቦታ ያለው ዝርያም ሆኗል።

ኅዳር መጀመሪያ ላይ የኦሚክሮን ዝርያዎችን በልጦ በበሽታው ከተያዙ 4 በመቶው በዚህ ዝርያ ምክንያት መሆኑ ሪፖርት ተደርጓል።

በአሜሪካ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።

ዩኬ አምና አምስት የኦሚክሮን ማዕበሎች አልፋለች። በቀጣይም ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

በዩኬ በኮሮናቫይረስ ከሚያዙ 25 ሰዎች አንዱ በአዲሱ ዝርያ እንደሚታመም ሳግነር የተባለው ተቋም ጠቁሟል።

በኢስት አንግሊያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ፖል ሀንተር፣ አዲሱ ዝርያ ማዕበል ሊያስነሳ የሚችል ከሆነ የሚታየው በቀጣዩ ወር ነው።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና ተቋም እንደሚለው ከኮሮናቫይረስ ጎን ለጎን ጉንፋንም ፈታኝ ሆኗል።

አዲሱ ዝርያ ሳይንቲስቶችን አስግቷል?

ፕሮፌሰር ዌንዲ እንደሚሉት፣ አዲሱ ዝርያ በኮሮናቫይረስ ክትባት አማካይነት የተኘውን የመከላከል አቅም ይሰብራል የሚል ስጋት የላቸውም።

ሆኖም ግን ከክትባቱ ውስን ጥቅም የሚያገኙ ለሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ሰዎችን ሊጎዳ እንደሚችል ይገምታሉ።

ፕ/ር ፖል በበኩላቸው፣ አዲሱ ዝርያ “ሆስፒታል የሚያስገባ ወይም የሚገድል” ስለመሆኑ አስካሁን ምንም ማስረጃ አልተገኘም።

ከቻይና ሌሎች ዝርያዎች ሊወጡ ይችላሉ የሚለው ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸው፣ አዲሱ ዝርያ ግን መነሻው አሜሪካ እንደሆነ አስረድተዋል።

የለንደን ስኩል ኦፍ ሀይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜድስን ባልደረባ የሆኑት ፕ/ር ዴቪድ ሄይማን፣ ስለ አዲሱ ዝርያ ገና መሠራት ያለባቸው ጥናቶች እንዳሉ ያስረዳሉ።

የክትባት ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸውና በሽታ የመከላከል አቅም ባዳበሩ እንደ ዩኬ ባሉ አገሮች የሚያሳድረው ተጽዕኖ ውስን እንደሚሆን አክለዋል።

እንደ ቻይና ያሉ የክትባት መጠን ውስን በሆነባቸው አገራት የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያው ይሰጋሉ።

“ለበሽታው ባልተጋለጠ ሕዝብ ውስጥ ዝርያው ምን ዓይነት ባህሪይ እንደሚኖረው እንዲታወቅ ቻይና በበሽታው ስለተያዙ ሰዎች መረጃ ማጋራት አለባት” ብለዋል።