ስለኮቪድ ክትባቶች ውጤት እና የጎንዮሽ ጉዳት እሰካሁን ምን እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ክትባቱ በዋነኛነት በዓለም ዙሪያ የሆስፒታሎችን መግባትን እና የሞትን መጠን ለመቀነስ ያለመ ነው። በወረርሽኙ ላይ የሚካሄደውን ጦርነት ግን ገና ዓለም በአሸናፊነት አልወጣውም።
የ90 ዓመቷ እንግሊዛዊት ማርጋሬት ኪናን ከሙከራዎች በኋላ የኮቪድ ክትባት የወሰዱ የመጀመሪያዋ ሰው ሆነዋል።
ከዚያን ወዲህ 13 ቢሊዮን የኮሮናቫይረስ ክትባቶች በዓለም ዙሪያ ተሰጥተዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ለማጠናከሪያ የሚሰጠውን ክትባት የወሰዱ ናቸው።
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት በኋላ በነበሩት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ምን ተማርን? መረጃዎች ስለ ክትባቶቹ ውጤታማነት ምን ያሳያሉ? ስለ የጎንዮሽ ጉዳቶቸስ ምን ይታወቃል?
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለኮቪድ መከላከያነት እንዲሰጡ ፈቃድ ያገኙ ክትባቶች በዋናነት ሆስፒታል መግባትን እና የሞት መጠንን የመቀነስ ሚና አላቸው።
ያለ እነዚህ ክትባቶች በጤና ቀውሱ የተጎዱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ያለ ይሆን ነበር።
በጣም የከፉ የጎንዮሽ ጉዳቶች መቀነሳቸውን የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት ይገልጻሉ።
አሁን ከእነዚህ መግለጫዎች በስተጀርባ ያለውን እንመርምር።
ተግባራዊ ውጤቶች
ክትባት ብዙ ሕዝብ መድረስ ከጀመረ ወዲህ፣ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ ሆስፒታል መግባት እና የሞት መጠን በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
እንደ ኦሚክሮን በጣም ተላላፊ የሆኑ የቫይረሱ ዝርያዎች ቢበዙም፣ ክትባቱ ብዙ ሰዎች በጠና እንዳይታመሙ ወይም እንዳይሞቱ አግዟል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ በታተመ የዳሰሳ ጥናት የኮመንዌልዝ ፈንድ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው በዬል ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ሳይንቲስቶችን አንድ ወሳኝ ጥያቄ እንዲመልሱ ጋበዞ ነበር።
“የኮቪድ ክትባቶች ባይኖሩን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር?” የሚል ጥያቄ ነው የተነሳው።
ውጤቶቹ እንደሚያመለክቱት በአሜሪካ ብቻ 18.5 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ሰበብ ሆስፒታል የሚገቡ ሲሆን፣ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በኮቪድ ለሞት ይዳረጉ ነበር።
የአሜሪካ የክትባት መርሃ ግብር ለህክምና ወጪዎች 1.15 ትሪሊየን ዶላር ማዳን መቻሉን ያሳያል። ይህ ወጪ ክትባት ባይኖር ለበሽታው የሚወጣ ተጨማሪ የሕክምና ገንዘብ ነው።
“ከታኅሣሥ 12 ቀን 2020 (እአአ) ጀምሮ አሜሪካ ውስጥ 82 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 4.8 ሚሊዮኖች ደግሞ ሆስፒታል ለመግባት ተገደዋል። 798,000 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ሪፖርት ተደርጓል።
“በሌላ አነጋገር ክትባት ባይኖር አሜሪካ 1.5 እጥፍ ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ይያዙባት ነበር፣ 3.8 እጥፍ ሆስፒታል የሚተኙ እና 4.1 እጥፍ ተጨማሪ ሞት ያጋጥማት ነበር” ይላሉ አጥኚዎቹ።
የብራዚል የክትባት ማኅበር (ኤስቢአይኤም) ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢዛቤላ ባላላይ እንዳሉት “የኮቪድ ክትባት ለብዙ ሰዎች በመሞት እና በመዳን መካከል ያለውን ልዩነት አሳይቷል።”
የዶክተር ባላላይ አገር ብራዚል፤ በቫይረሱ በጣም ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ክትባቶች እንዴት እንደሚሰሩም ጥሩ ማሳያ ነች።
በጥር 2021 የመጀመሪያዎቹ ክትባቶች ሲጸድቁ ብራዚል ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ ከፍተኛው ጉዳት ላይ እየደረሰች ነበር።
ባለፈው ዓመት በመጋቢት መጨረሻ እና በሚያዝያ ወር መጀመሪያ መካከል በኮቪድ የሞቱት ሰዎች ዕለታዊ አማካይ ቁጥር ከ3,000 በላይ ደርሶ ነበር። አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በቀን 72,000 እንደደረሰም የብሔራዊ የጤና ምክር ቤት አስታወቋል።
ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ እና የተከተቡ ብራዚላውያን መጠን ሲጨምር የሟቾች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ጀመረ።
የኦሚክሮን ዝርያ በመከሰቱ እነዚህ ቁጥሮች በጥር 2022 እንደገና ጨምሯል። በዚህ አዲስ ዝርያ ምክንያት ዕለታዊ የሞት መጠን 950 ሲሆን ከቀዳሚው አንድ ሦስተኛ ያነሰ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶቹስ?
“ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እና ብዙ የኮቪድ ክትባቶች ሲሰጡ ስለ ደኅንነታቸው የበለጠ እርግጠኛ እንሆናለን” ያሉት ዶ/ር ባላላይ ናቸው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተቆጣጣሪ ድርጅቶች እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋማት ከክትባት በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ አሉታዊ ክስተቶችን ለመከታተል እና ለመመርመር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) “ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች በጣም ጥቂት ናቸው” በማለት ገልጿል። ከክትባት በኋላ ከተለመዱት የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል፡
- በተከተቡበት ቦታ ላይ ህመም መኖር፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት ህመም፣ ትኩሳት፣ የህመም ስሜትወይም መታመም ናቸው።
“ከእነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል አብዛኞቹ ቀላል እና ከአንድ ሳምንት ላነሰ ጊዜ የሚቆዩ ናቸው” ሲል የብሪታንያ መንግሥት ተናግሯል።
ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶቹስ? የቅርብ ጊዜ ቁጥሮችስ ምን ይላሉ? በጣም ወቅታዊ የሆነው መረጃ የተሰናዳው በአሜሪካው የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ነው።
እንደ ሲዲሲ ዘገባ ከሆነ እስካሁን የሚታወቁት በጣም ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚከተሉት ናቸው።
- አናፊላክሲስ (ከክትባት በኋላ የሚከሰት ከባድ አለርጂ)፡ ከአንድ ሚሊዮን ክትባት አምስት ያህል ያጋጥማል።
ከጆንሰን ክትባት ጋር በተያያዘ ከአንድ ሚሊዮን ክትባት አራት ያህል። የፋይዘር ክትባት በወሰዱ ወጣቶች ላይ ማዮካርዳይተስ እና ፐርካርዳይትስ (የልብ መቆጣት) አጋጥሞ ነበር።
ሲዲሲ እንዳለው “ብዙዎቹ ማዮካርዳይተስ ወይም ፐርካርዳይትስ ያለባቸው ታካሚዎች ለመድኃኒት እና ለእረፍት ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በፍጥነትም ይሻላቸዋል።”
"በደኅንነት ቁጥጥር ሥርዓቶች ላይ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች እና ግምገማዎች፣ ክትባቶቹ ችግር የማያስከትሉ መሆናቸውን ያሳያሉ” ሲል አክሏል።
ሞትን በተመለከተ አሜሪካ ውስጥ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቱ እስከ ታኅሣሥ 07 ቀን 2022 ድረስ ከተሰጡ 657 ሚሊዮን ክትባቶች 17,800 ሰዎች ከክትባት በኋላ (ወይም ከጠቅላላው 0.0027 በመቶ) ሕይወታቸው አልፏል።
ነገር ግን የክትባቱ አሰጣጥ ለዚህ ሞት ቀጥተኛ መንስኤው ስለመሆኑ ምንም አልተገለጸም።
የህክምና መዛግብትን እና የአስከሬን ምርመራዎችን በመተንተን ከጆንሰን ክትባት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ሰዎች ብቻ ተገኝተዋል።
ዶ/ር ባላላይ ምንም አይነት መድኃኒት፣ ክትባት ወይም አሠራር ከአደጋ ነጻ እንዳልሆነ አበክረው ተናግረዋል።
“እነዚህ ሁሉ ቁጥሮች የሚያሳዩት የክትባት ጥቅሙ አልፎ አልፎ ከሚፈጠሩ ችግሮች እጅግ የላቀ መሆኑን ነው” ይላሉ።
ቀጥሎስ ምን ይመጣል?
የመጀመሪያዎቹ የኮቪድ-19 ክትባቶች ከተገኙ ከሁለት ዓመት በኋላም ቢሆን ኮሮናቫይረስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር አሁንም ብዙ ፈተናዎች አሉ።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ ክትባት በመስጠት በጣም ወደ ኋላ የቀሩ አገራት አሉ” ሲሉ የተላላፊ በሽታዎች ጥናት ተመራማሪው አንድሬ ሪባስ ፍሬይታስ ተናግረዋል።
ሄይቲን በምሳሌ ብንወስድ 2 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ብቻ ነው ሁለቱን የመጀመሪያ ክትባቶች የወሰደው። እንደ አልጄሪያ (15 በመቶ)፣ ማሊ (12 በመቶ)፣ ኮንጎ (4 በመቶ) እና የመን (2 በመቶ) ባሉ አገራትም ቁጥሩ ዝቅተኛ ነው።
“ይህ በጣም ትልቅ አሳሳቢ ነገር ነው። ምክንያቱም ኃይለኛ ተላላፊ ቫይረስን ማቆየት የበለጠ ተላላፊ ወይም በሽታ አምጪ ዝርያዎች የመከሰት አደጋን ያመላክታል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።












