በጠብታ መልክ በአፍንጫ የሚሰጥ የኮቪድ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ተፈቀደ

የጠብታው ክትባት

የፎቶው ባለመብት, BHARAT BIOTECH / TWITTER

የምስሉ መግለጫ, የጠብታ ክትባት

በርካታ ሕዝብ ቦሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያጣችው ሕንድ በጠብታ መልክ በአፍንጫ የሚሰጥ የኮቪድ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጠች።

‘ኢንኮቫክ’ በመባል የሚታወቀውና በሃራት ባዮቴክ በተባለው ድርጅት የተመረተው ክትባት በጠብታ መልክ በአፍንጫ የሚሰጥ ሲሆን፣ በአፍንጫችን ውስጥ ያሉት ሕብረ ህዋሳት ቫይረሱ በሚያጋጥማቸው ጊዜ በተፈጥሯዊ ሂደት እንዲከላከሉ ያነቃቃል።

ባለፈው መስከረም ወር ቻይና እንደ ስፕሬይ የሚረጭ እና በትንፋሽ የሚወሰድ የኮቪድ መከላከያ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መፍቀዷ ይታወቃል።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሕንዱ በአፍንጫ የሚወሰደው የኮቪድ ክትባት የኮሮናቫይረስ ወደ ሰውነት በሚገባባቸው በአፍንጫ እና በላይኛው የመተንፈሻ ክፍል ላይ ተጨማሪ በሽታውን የመከላከል አቅምን ይፈጥራል።

በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ ያሉ የምርምር ቡድኖች በአፍንጫ ውስጥ የሚረጩ የኮቪድ መከላከያ ክትባቶችን እየሞከሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ባለፈው ኅዳር ወር የሕንድ የመድኃኒቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ኢንኮቫክ የተባለውን ይህ ክትባት ሁለት ጊዜ የተከተቡ አዋቂ ሰዎች እንደማጠናከሪያ ክትባት እንዲወስዱት ፈቅዶ የነበር ሲሆን፣ ታኅሣሥ ላይ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ክትባትንት እንዲሰጥ አድርጓል።

ይህንን በጠብታ መልክ በአፍንጫ የሚሰጠውን ክትባት ለመውሰድ ለአንድ ጊዜ 10 ዶላር ያህል የሚያስከፍል ሲሆን፣ በ28 ቀናት ልዩነት ሁለተኛው መወሰድ አለበት። ሕንድ ውስጥ በመንግሥት በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች ውስጥ እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል።

ይህ ኢኖቫክ የተባለው የጠብታ ክትባት በሰውነት ውስጥ ያለው ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት የኮሮናቫይረስን እንዲያውቀውና ወደ ሰውነት በሚገባ ጊዜ ተባዝቶ በሽታን እንዳያስከትል ያደርገዋል ተብሏል።

የክትባቱ አምራች በሃራታ ባዮቴክ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ክሪሽና ኤላ፣ ክትባቱ ለመስጠት ሲሪንጅም ሆነ መርፌ ስለማያስፈልገው “ለመስጠት ቀላል” ከመሆኑ በተጨማሪ በመርፌ ከሚሰጡት ጋር ሲነጻጸር ሰፋ ያለ በሽታን የመከላከል አቅምን ይፈጥራል ብለዋል።

እስካሁን ድረስ ሕንድ ከሁለት ቢሊየን በላይ የኮቪድ ክትባቶችን የሰጠች ሲሆን፣ 70 በመቶ በላይ ዜጎቿ ቢያንስ ሁለት ጊዜ መከተባቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶም በሕንድ ለሕክምና ባለሙያዎች፣ የሕዝብ አገልግሎት ለሚሰጡ ዜጎች እና ከ60 ዓመት በላይ ሆነው ተደራራቢ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች የማጠናከሪያ ክትባት መስጠት ተጀምሯል።

ይህም ሦስተኛ ዙር ክትባት ወደ ቀሪው የአገሪቱ ዜጋ እየተስፋፋ ነው ተብሏል።