በሲንጋፖር ተማሪዎች ፈተና እንዲያጭበረበሩ ያደረገች ሴት እንድትያዝ ኢንተርፖል ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, INTERPOL
ሲንጋፖር ውስጥ በተፈጸመ ውስብስብ የፈተና ማጭበርበር እጇ አለበት የተባለችው ሴት እንድትያዝ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ጥሪ አቀረበ።
የ57 ዓመቷ ፖህ ዩዋን ኒይ ስልክ እና ኢርፎን በመጠቀም ተማሪዎች የፈተና ውጤት እንዲያጭበረብሩ የሚያደርግ መዋቅር ዘርግታ ነበር ተብሏል። ሦስት ተባባሪዎቿ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ግለሰቧ ቀደም ሲል የአስጠኚዎች ማዕከል ኃላፊት ነበረች። የተፈረደባትን የአራት ዓመት እስራት ካለፈው መስከረም ትጀምራለች ተብሎ ቢጠበቅም አስካሁን እጇን አልሰጠችም።
ግለሰቧ ከሴንጋፖር ኮብልላለች ተብሎ ይታሰባል።
የአገሪቱ ፖሊስ የእስር ማዘዣ አውጥቶባታል። ለኢንተርፖል ጥቆማ ካደረጉም በኋላ ኢንተርፖል “ቀይ ማስጠንቀቂያ” አውጥቷል። ያለችበትን የሚያውቁ እንዲያሳውቁም ጠይቋል።
‘ፖኒ’ በሚል ስም የምትጠራው ግለሰብ የወጣባት “ቀይ ማስጠንቀቂያ” በመላው ዓለም ያሉ የሕግ አካላት ያለችበትን እንዲፈልጉና እንዲይዟት ይሁንታ ይሰጣል።
እአአ በ2016 በሲንጋፖር የተካሄዱ ሦስት ብሔራዊ ፈተናዎች ላይ ነው ማጭበርበር የተፈጸመው።
የፖህ የጥናት ማዕከል ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 20 የሆኑ ቻይናዊ ስድስት ተማሪዎችን ያስጠና ነበር። እነዚህም ፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤት ለመግባት የሚያስፈልጋቸውን ውጤት ለማግኘት ነበር ፈተና የሚወስዱት።
ለእያንዳንዱ ተማሪ 6,100 ዶላር ተከፍሎ የነበረ ሲሆን፣ ውጤት ካላመጡ ገንዘቡ እንደሚመለስ ተገልጾም ነበር።
ተማሪዎቹ ከቆዳቸው ጋር የሚመሳሰል ሄድፎን አድርገው በተለያዩ የፈተና ማዕከሎች ፈተናውን ወስደዋል። ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ብሉቱዝ ሰውነታቸው ላይ ተለጥፎ በልብስ እንዲሸፈን ተደርጓል።
የዚህች ግለሰብ የቀድሞ አጋር የሆነችው የ30 ዓመቷ ታን ጂያ ያን በግሏ ይህንን ፈተና ወስዳለች። ስልክ ደረቷ ላይ ተለጥፎ ነበር ፈተናውን እንድትወስድ የተደረገው።
ፌስታይም የተባለውን የግንኙነት መተግበሪያ በመጠቀም ታን በቀጥታ የፈተና ጥያቄዎቹን ለፖህ አስተላልፋለች።
በማስጠኛ ማዕከሉ የነበሩ የፖህ ተቀጣሪ ፌንግ ሪዋን እና የፖህ የእህት ልጅ ፊዮና ፖህ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጥተው ለቻይናውያኑ ተማሪዎች ኢርፎን ተጠቅመው ነግረዋቸዋል።
“መልሱን ሲናገሩ ከሰማሁ ዝም ስል፣ ካልሰማዋቸሁ ግን የሳል ድምጽ አሰማ ነበር” ሲል አንድ ተማሪ ቃሉን ሰጥቷል።
አንድ የፈተና ገምጋሚ ያልተለመደ ድምጽ ሲሰሙ ከተፈታኞቹ አንዱን አናግረዋል። ተማሪውም ፈተናውን እያጭበረበሩ እንደሆነ ወዲያው ተናግሯል።
አንደኛው ተማሪ ማጭበርበር ባይፈልግም አስጠኚዎቹ እንዳስገደዱት ተናግሯል።
በ2020 ፖህ፣ ተቀጣሪዋ እና የእህቷ ልጅ በ27 የማጭበርበር ክሶች ተፈርዶባቸዋል። እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ታስረዋል።
ራሳቸውን እንዲከላከሉ ዳኛ ዕድል ቢሰጣቸውም ዝምታን መርጠዋል።
በ2019 ታን የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።
በፍርድ ሂደቱ ላይ “ተማሪዎች አጭበርብረው የፈተና ውጤት መግዛታቸው ያሳዝናል። የታማኝነት መርህን ይጥሳል። ሀብታሞች በገንዘባቸው የፈተና ውጤት ሊገዙ አይገባም” ሲሉ ነበር ዳኛው የተናገሩት።
ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፈተናው ውጤት ሲጭበረበር የመጀመሪያው አይደለም። በ2016 በታይላንድ የሕክምና ተማሪዎች በካሜራ እና ስማርት ሰዓት በመጠቀም ለማጭበርበር ሞክረዋል።












