በዝቅተኛ የፈተና ውጤት ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አሠራር ለመከተል ተገደደ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education
የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያበቃ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አሠራር ሊከተል መሆኑ ተነገረ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በማስመልከት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ላይ ለፈተናው ከተቀመጡት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከአራት በመቶ በታች እንደሆኑ አስታውቀዋል።
የተመዘገበውን ውጤት “አስደንጋጭ” ያሉት ሚኒስትሩ ፈተናውን ከወሰዱት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ወደ 30 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት ብለዋል።
በተደጋጋሚ በብሔራዊው ፈተና ይከሰታል ሲባል የቆየውን የፈተና ስርቆት ለማስወገድ በሚል የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዕቅድ መሠረት ተማሪዎቹ ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መውሰዳቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ከነበረው የፈተና አሰጣጥ በተለየ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች በተለያየ ጊዜ በተናጠል ፈተናውን ወስደዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ተግባራዊ በተደረገው አዲስ አሠራር መሠረት በፈተና ወቅት ምንም ዓይነት ስርቆት እንዳልተፈጸመ ገልጸው፣ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ውጤትም በፈተና ወቅት የኮርጁ ተማሪዎችን ሳያካትት በሥርዓቱ መሠረት የተፈኑ ተማሪዎች ብቻ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።
ለፈተናው ለመሳተፍ በአጠቃላይ 985,384 ተማሪዎች ተመዝግበው ተፈትነው ውጤት የተያዘላቸው ተማሪዎች ደግሞ 896,520 ናቸው ተብሏል።
ከእነዚህም ውስጥ ለፈተናው ተመዝግበው ያልተፈተኑ 77,098 ተማሪዎች እንዲሁም 20,170 የሚሆኑት ደግሞ በፈተናው ላይ ተገኝተው “በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉ እና ፈተናውን ትተው የሄዱ” መሆናቸው ተገልጿል።
እነዚህም በአማራ ክልል በፈተናው ወቅት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ 12 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ላለመውሰድ ወስነው ትተው መውጣታቸው ይታወሳል።
ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደማይቀላቀሉ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጤታቸው መሠረት ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል ለቀጣይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያገኙ ይሠራል ተብሏል።
በመቶኛ ሲሰላ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ተፈታኞች ከ50 በመቶ ባላይ ውጤት በማስመዝገብ ከማኅበራዊ ሳይንስ አቻዎቻቸው የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል።
ከ339,642 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል 6.8 በመቶው እንዲሁም የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተናን ከወሰዱት 556,878 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 1.3 በመቶው ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ አስመዝግበዋል።
በዚህም መሠረት ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ 30 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማም ገብተው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ይሆናል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅምን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “የተሻለ ውጤት ያመጡት ተመርጠው ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ የሚደረግ ቢሆንም እነዚህ ተማሪዎች በቀጥታ የዩኒቨርስቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንደማይሆኑ” ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከዚያ ይልቅ ግን ተማሪዎቹ ደካማ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲማሩ ተደርገው፤ የሚሰጣቸውን የመመዘኛ ፈተና የሚያልፉ ከሆነ የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ይጀምራሉ ብለዋል ሚኒስትሩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ አሁን ለታየው የተማሪዎች የውጤት ማስቆልቆል “ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው” ብለዋል።
ለዚህም ከመንግሥት እና ሁሉም የትምህርት ማኅበረሰቡ መሆኑን በመግለጽ፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ አጠቃላዩን የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለ ጠቁመዋል።












