የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በኤርትራ ጉብኝት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, shabait
ለቀናት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኙ።
የኤርትራ መንግሥት እንዳስታወቀው የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኤርትራ የተጓዙት ከምክትላቸው ሚኻይል ቦግዳኖቭ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ነው።
ላቭሮቭ በኤርትራ ያደረጉትን የአንድ ቀን ጉብኝት የጀመሩት ከዋና ከተማዋ አሥመራ ሳይሆን በወደብ ከተማዋ ምጽዋ ነበር።
ከምዕራባውያን ጋር የሻከረ ግንኙነት ያልት ኤርትራ ከሩሲያ ጋር ያላት ወዳጅነት እየተጠናከረ ሲሆን፣ ዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩሲያን ደግፈው በይፋ ከቆሙ ጥቂት አገራት መካከል ኤርትራ አንዷ ናት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምጽዋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳሌህ፣ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አማካሪ የማነ ገብረአብ እና በከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አቀባበባል እንደተደረገላቸው ተዘግቧል።
በተያዘው ፕሮግራም መሠረትም ላቭሮቭ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው፣ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር እና በሚመለከቷቸው የአካባቢው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ በነበራቸው ቆይታ ምዕራባውያን በአገራት ላይ እያሳደሩት ስላለው ጫና እንዲሁም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማንሳታቸው ተገልጿል።
በሁለቱ አገራትን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ ላቭሮቭ፣ ሩሲያ ከኤርትራ ጋር በኢነርጂ፣ በማዕድን ማውጣት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስም በበኩላቸው የተጠቀሱት ዘርፎች ኤርትራ ቅድሚያ የምትሰጣቸው የትብብር መስኮች መሆናቸውን ጠቅሰው ለተግባራዊነታቸው እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዚህ ጉብኘታቸው መነሻ ከዋና ከተማዋ ይልቅ የወደብ ከተማዋ ምጽዋን ለምን እንደመረጡ በአንዳንዶች ዘንድ ጥያቄን ቢፈጥርም፣ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ላቭሮቭ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እያደረጉት ባለው ጉብኝት ደቡብ አፍሪካን፣ ኢስዋቲኒን እና አንጎላን ጎብኝተው ነው ወደ ኤርትራ ያቀኑት።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ከወራት በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ አፍሪካ ባደረጉት ጉዞ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መክፈቷን ተከትሎ ከምዕራባውያኑ ከባድ ውግዘት የገጠማት ሲሆን፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ግን ገለልተኛ አቋም ይዘው ቆይተዋል።
በሩሲያ ወታደራዊ እርምጃ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ድምጽ በተሰጠበት ጊዜ አብዛኞቹ ሩሲያን ከመቃወም የተቆጠቡ ሲሆን ጥቂቶች ግን ደግፈዋት ቆመዋል። ከእነዚህም መካከል ኤርትራ አንዷ ናት።












