የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትዊተር ላይ ያሰፈረው መልዕክት እና ምስል አፍሪካውያንን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በተመለከተ በትዊተር ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ እና ምስል ከአፍሪካውያን ተቃውሞ ገጠመው።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በትዊተር ገጹ ላይ ላቭሮቭን ለመወረፍ የተጠቀመበት አገላለጽ የአፍሪካ አህጉርን በአንድ ነገር ዙሪያ አጠቃሎ የተመለከተ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት “የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ አፍሪካ ውስጥ ናቸው፤ [በምስል/ኢሞጂ አቦሸማኔ/ሊዮፓርድ] ግን ሊያዩ አይደለም፤ ነገር ግን አጥብቀው የዩክሬን አጋሮች “የሩሲያ የሆነ ነገር ሁሉ ለማውደም ይፈልጋሉ ብለዋል” ሲል አስፍሯል።
በርካታ ሰዎች ይህ አገላለጽም ከዱር እንስሳት ውጪ የሩሲያውን ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ አፍሪካ አህጉር እንዲመጡ የሚያደርጋቸው ነገር የለም የሚል አንደምታ ያለው ነው በሚል ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
ከእነዚህም መካከል የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ቃል አቀባይ የሆኑት ኤባ ካሎንዶ “የአፍሪካ አህጉር፣ ሕዝቧ እና የዱር እንስሳቶቿ ለእናንተ ቀልድ ናቸው?” ሲሉ መረር ያለ ጥያቄ አንስተዋል።
ካሎንዶ ጨምረውም የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በቅርቡየአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ወደሆነችው ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር በማስታወስ፣ “ሚኒስትሯ የመጡት እንስሳትን ለማየት ነበር?” በማለት አስፍረዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሁለት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መንግሥ እና ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል።
ሌላ ግለሰብ ደግሞ ከዚያው የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መልዕክት ስርኮፊ የቦሃ የተባለ ግለሰብ “አፍሪካ የዱር እንስሳትን ከምትመለከቱባት ቦታ በላይ መሆኗን ስንት ጊዜ እንገራችሁ?” ብሏል።
“አውሮፓ ውስጥ በምታካሂዱት ጦርነት ውስጥ በተቀናቃኛችሁ ላይ መልካአ ምድራዊ የበላይነትን ለማግኘት ስትሉ አፍሪካን በአንድ አስቀያሚ ዕይታ ስር መፈረጅ፣ አፍሪካዊ ወዳጅን እንድታገኙ አያደርጋችሁም” ስትል ዘይነብ ኡስማን ተቃውሞዋን ገልጻለች።
የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበሯ አስተያየትን ተከትሎ የጀርመን የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እዚያው ትዊተር ላይ ባሰፈረው ምላሽ “ያነሱትን ነጥብ ተቀብለናል፤ ይቅርታ” በማለት የትዊት መልዕክቱ አፍሪካውያንን ለማስቀየም የተላመ እንዳልሆነ በመግለጽ ለማስረዳት ሞክሯል።
አቦሸማኔ/ሊዮፓርድን የተጠቀሙት ጀርመን ሰራሾቹን ታንኮች እንደሆነ በመግለጽ ለአፍሪካውያን አጋሮቻቸውን ዋጋ እንደሚሰጡ ገልጿል።
ጀርመን ከሩሲያ ጋር ውጊያ ላይ ላሉት የዩክሬን ኃይሎች ዘመናዊ የተባሉትን ሌዮፓርድ 2 የውጊያ ታንኮች ለመስጠት መወሰኗ ይታወቃል።
ኤባ ካሎንዶም ቆጣ ባለ ምላሻቸው “የቅርታ አትጠይቁ። ጥንቃቄ ብቻ አድርጉ። እንደምናከብራችሁ እናንተም አክብሩን” በማለት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን መክረዋል።
ሩሲያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ወረራ በዩክሬን ላይ ከከፈተች በኋላ ከጀርመን እና ከሌሎች ምዕራባውያን አገራት ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ ይታወቃል።
ምዕራባውያኑ የአፍሪካ አገራት የሩሲያን ወረራ እንዲያወግዙ ቢፈልጉም አብዛኞቹ ገለልተኛ አቋም ይዘዋል። በዚህም የአፍሪካ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት ሩሲያም ሆነ ምዕራባውያኑ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭም በዚህ ሳምንት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን፣ ይህም በስድስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።












