ስሟን በሚዲያ ለመጥራት የምትፈራው የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ

ኪም ከልጃቸው ጋር ከወታደሮቻቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ከልጃቸው ጋር ከወታደሮቻቸው ጋር

ሰሜን ኮሪያ የምሥጢር ሙዳይ የሆነች አገር ናት።

ከሚታወቁት ነገሮች የማይታወቁት ይበልጣሉ።

ለምሳሌ ሕዝቡ ምን በልቶ እንደሚያድር እምብዛምም አይታወቅም።

ለምሳሌ መንግሥት ምን ነግዶ ምንዛሪ እንደሚያመጣ እምብዛምም አይታወቅም።

ለምሳሌ የኮቪድ-19 ተህዋሲ ምን ያህል ሕዝብ እንደገደለ በጭራሽ አይታወቅም።

ለምሳሌ የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ በትክክል ማን እንደሆነች የታወቀው በቅርብ ነው።

እንደ ሰሜን ኮሪያ ምሥጢራዊ የሆነ አገር የለም የሚባለው በምክንያት ነው።

ከሰሞኑ ትልቅ መነጋገሪያ የሆነቸው የኪም ሴት ልጅ ናት። ስሟ አይጠቀስም።

የአገሬው ሚዲያ ‘ዕጹብ’ ወይም ‘ተወዳጇ’ እያለ ያሞካሻታል እንጂ ስሟን ግልጥ አድርጎ ቢጠራው ችግር ሊገጥመው ይችላል።

‘ዕጹብዬ ከታላቁ መሪያችን ጋር ታየች’ እያለ ነው ለጊዜው ዘገባ የሚሠራው።

ስሟን ማንም መጥራት አይችልማ፤ ወይም አይደፍርማ።

ለመሆኑ የኪም ልጅ ማን ናት?

አሁን ይቺ ልጅ የኪም ተተኪ እንደምትሆን ብዙዎች ትንቢት መናገር ጀምረዋል።

ምክንያቱም ኪም ያለ ምክንያት ለስንት ዘመን ከሚዲያ አይደብቋትም ነበር።

ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ሴት ልጃቸውን ወደ አደባባይ እንዲያወጧት ያደረጋቸው አንዳች ቁም ነገር ቢኖር ነው ይላሉ ጠርጣሪዎች።

ይቺ የኪም ሴት ልጅ በአገሬው ሚዲያ ስሟ ብቻ አይደለም ያልተጠቀሰው፤ ዕድሜዋም ተጠቅሶ አያውቅም።

የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት (ኬሲኤንኤ) በቅርቡ እንደዘገበው ታላቁ መሪ ኪም እና ሴት ልጁ ‘ዕጹብ’ የአገራቸውን ጀግና ወታደሮችን እና ጀግና ሳይንቲስቶችን አግኝተዋል።

ገናናውን ህዋሶንግ ሚሳኤልንም አብረው ጎብኝተዋል፤ ዳሰውታልም።

የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት በለቀቀው በዚህ የአባትና ልጅ ፎቶ ብዙዎች ተገርመዋል።

ነገር ግን ዜናው ፎቶው በትክክል መቼ እንደተነሳ አይጠቅስም።

ወታደሮች እና ሳይንቲስቶች በኪም እና በሴት ልጃቸው በመጎብኘታቸው ታላቅ ክብር፣ የትየለሌ ኩራት ተሰምቷቸዋል።

“ነፍሳቸው እስክትወጣ ድረስም በደስታ ሰክረዋል” ይላል ዘገባው።

በዚህ አያበቃም ታዲያ። “በኪም እና በልጃቸው መጎብኘት እንዴት ያለ ታላቅ ጸጋ ነው” ሲሉ ተጎብኚዎቹ ገልጸዋል ብሏል ዜናው።

ኪም ከልጃቸው ጋር በሚሳኤል ሙከራ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ከልጃቸው ጋር በሚሳኤል ሙከራ ስፍራ

ተደብቃ የቆየችው የኪም ሴት ልጅ

የኪም ሴት ልጅ ለመጀመርያ ጊዜ መኖሯ የታወቀው በፈረንጆቹ 2013 ነበር።

እንኳንስ ስለ እርሷ ስለ አባቷም የሚታወቀው በጥቂቱ ነበር።

የያኔው ጎረምሳ አባቷ ኪም ሲለው ከሚዲያ ይሰወራል።

የአገር መሪ በመሆኑ ብቻ “አንቱ የሚሰኙት” ኪም ሰሜን ኮሪያን በጎርምስና መምራት የጀመሩ ሰው ናቸው፤ በነጠላ የመጠራታቸው ምሥጢርም ይኸው ነው።

ኪም ቁጣቸው ከመሬት ያደባያል።

የገዛ ጄኔራሎቻቸውን፣ የገዛ አጎታቸውን አስቀልተዋል።

በአገራቸው ለመጣ ቀልድ አያውቁም። ኩ-ር-ት ያሉ አምባገነን እንደሆኑ ነው የሚነገረው።

በሐምሌ 2012 (እአአ) የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን የኪም ባለቤት ማን እንደሆኑ ገለጹ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰሜን ኮሪያ ቀዳማዊት እመቤት ሪ ሶለ ጁ እንደሚባሉ አገሬው ተነገረው።

ይህ የሆነው ታዲያ ኪም በአደባባይ ከሚስታቸው ጋር በታዩ በወሩ ነው።

ከሚስታቸው ጋር በታዩበት የመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት ማንም እመቤቲቱን የኪም ባለቤት ብሎ ለመጥራት የደፈረ አልነበረም።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ባል እና ሚስቱ፣ ማለትም ኪም እና ሪ ልጅ አላቸው ወይስ የላቸውም? የተከበሩ ወ/ሮ ሪ ጸንሰዋል ወይስ? ሁለት ነፍስ ይሆኑ? ወይስ. . . በሚለው ጉዳይ ትንፍሽ ያለ አልነበረም።

ቆየት ብሎ ወ/ሮ ሪ እና ኪም ሦስት ልጆች እንዳሏቸው በሚዲያ ተነገረ። ያው ሕዝቡ ይነገረው ተብሎ ተፈቅዶ መሆን አለበት።

ኪም ከልጃቸው ጋር በሚሳኤል ሙከራ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ከልጃቸው ጋር በሚሳኤል ሙከራ ስፍራ

ከዓመት በኋላ በመስከረም 2013 (እአአ) የቀድሞው ዕውቅ አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ዴኒስ ሮድማን ለ‘ዘ ጋርዲያን’ ጋዜጣ አንድ አዲስ መረጃ ሰጠ።

መረጃው ኪም ሴት ልጅ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነበር።

መታደል ወይም አለመታደል ሆኖ ይህ ጫማውን የሰቀለ ጡረተኛ አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ጥበበኛ፣ በኪም የሚወደድ ብቸኛ አሜሪካዊ ሳይሆን አይቀርም።

ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ወደ ሰሜን ኮሪያ፣ ፒዮንግያንግ ተጋብዟል።

ፊልም ሁሉ ተሠርቶበታል፤ በኪም እና በቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ወለፈንዲ ወዳጅነት።

ሮድማን ታዲያ ያኔ ለዘ ጋርዲያን በሰጠው ቃል፤ “ወዳጄ ኪም ሴት ልጁን አብልጦ የሚወድ ሰው ነው” ሲል አባትነቱን መሰከረ።

የኪምን ሴት ልጅ እንደተወለደች፤ እሱ ራሱ ከእናቷ ወ/ሮ ሪ ተቀብሎ እቅፍ አድርጎ መሳሙንም አረጋገጠ።

ቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ሮድማን ያን ካለ በኋላ ነው የዓለም ሚዲያ “ኪም እኮ ሴት ልጅ አለቻቸው” ብሎ በድፍረት መዘገብ የጀመረው።

ለመጀመሪያ ጊዜ መቼ ታየች?

በዚህ ዓመት ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት አከታትሎ በርከት ያሉ ፎቶዎችን ለቀቀ።

ፎቶዎቹ ኪም እና ሴት ልጃቸውን ያሳያል።

ያን ጊዜ ነው በሕይወት እንዳለች የተረጋገጠው።

አባት እና ልጅ ታዲያ ሚሳኤል ሲዳብሱ፣ ወታደር ሲያንቆጳጵሱ፣ ቀጭን ትዕዛዝ ሲያወርዱ ተወንጫፊ ሚሳኤል ሲመርቁ ነበር የዋሉት።

አባት እና ልጅ የመረቁት ሚሳኤል አገር ብቻ ሳይሆን አህጉር አቋራጭ ነበር።

ደቡብ ኮሪያ ሴዑል የምትገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ጂን ማኔንዚ የምዕራብ ሚዲያም ሆነ የአገሬው ሚዲያ ከሚሳኤሉ ይልቅ በአባት እና ልጅ አብሮ መታየት ዜና ተጠምደው ነበር ብላለች።

በተለይ የአገሬው ሚዲያ የኪምን ሴት ልጅ በማንቆለጳጰስ መጠመዱ ምናልባት ይቺ ልጅ ታላቁ ኪም ለመሪነት እያጯት ይሆን? የሚል ጥርጣሬን ጭሯል።

ኪም ከልጃቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ከልጃቸው ጋር

ለሁለተኛ ጊዜ መቼ ታየች?

የመጀሪያ ፎቶዋ በተለቀቀ በሳምንቱ ሌላ ፎቶ ተደገመ። ዓለም ጉድ አለ።

“ይሄማ አንድ ነገር ታስቦ መሆን አለበት” ተባለ። ይህ የሆነውም በቅርቡ ነበር።

በዚህ ጊዜም ቢሆን ስለ ስሟም ይሁን ዕድሜዋ ትንፍሽ ያለ አልነበረም።

ይሁንና ከመጠሪያ ስሟ ይልቅ “ተዋዳጅዋ” እና “ዕጹብ” የሚለው ቅጽል በዜና አንባቢዎች ዘንድ ጥቅም ላይ ውሏል። መጠሪያ ስሟን የሚያውቀውስ ይኖር ይሆን?

አስተማሪዋስ ቢሆን በስሟ ይጠራት ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

የአሜሪካው ቴሌቪዥን ኤንቢሲ ኔትዎርክ አንድ የአካባቢውን ጉዳዮች አዋቂን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ኪም ከልጃቸው ጋር እጅግ ወሳኝ በሚባል የሚሳኤል ሳይንቲስቶች ጉብኝት ወቅት መገኘት በፍጹም እንደዋዛ የሚታይ አይደለም።

ምናልባት አንድ የተደገሰላት ነገር ይኖር ይሆናል። ለአንድ ታላቅ ተግባር ታጭታም ይሆናል ብሏል የኤንቢሲው ተንታኝ።

ሌሎች ሰሜን ኮሪያን ከማንም በላይ ጠንቅቀን እናውቃለን የሚሉ ተንታኞች ግን፣ ይቺ ልጅ ለታላቅ ሥልጣን ታጭታለች ብሎ ለመናገር ጊዜው ገና ነው ሲሉ ያሳስባሉ።

በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ የጻፉት እና በቅርቡ ሮይተርስ ዘገባ ላይ የተጠቀሱት ቹን ሱ ጂን ደግሞ “በጭራሽ” ይላሉ።

ኪም ከልጃቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, KCNA via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ከልጃቸው ጋር

“በጭራሽ” ምን?

“በጭራሽ ይቺ የኪም ልጅ ለሥልጣን የመታጨት ዕድሏ ዜሮ፣ ከዜሮም በታች ነው” ብለዋል።

የእሳቸው መከራከሪያ ደግሞ የጾታ ጉዳይ ነው።

በሰሜን ኮሪያ ሴት ልጅን ወደ ከፍተኛ ሥልጣን ለማብቃት ጊዜው ገና ባሕል አልሆነም።

ታዲያ ለምን በቴሌቪዥን ታየች? ተብለው ሲጠየቁ “ኪም ሚሳኤል አስተኳሽ አምባገነን መሪ ብቻ ሆነው መታየት አይልጉማ” ብለዋል።

“ልጃቸውን የሚወዱ አፍቃሪ አባት እንደሆኑ ለሕዝብ ማሳየት ስለፈለጉ ብቻ ነው” ይላሉ።

ይቺ ልጅ ለሥልጣን ታጨችም አልታጨች በሰሜን ኮሪያ ከኪም ቀጥሎ የሚጠራው ስም የሴት ነው።

ምክንያቱም የኪም እህት አሁንም ቢሆን አድራጊ ፈጣሪ ናት። ስሟም ኪም ዮ ጁንግ ይባላል።

ከሁለት ዓመት በፊት ኪም ጆንግ ኡን “ታሟል፤ ከዚህ ወዲህ አበቃለት” ሲባል፤ “ውፍረቱ ገደለው” ተብሎ በምዕራብ ሚዲያ ሲሟረትበት በቴሌቪዥን ብቅ ብላ አገሩን ልክ ያስገባች የኪም እህት ዮ ጆንግ አይደለችምን?

እህት ኪም ዮ ጆንግ በቅርቡ ጎረቤት ደቡብ ኮሪያን ከፍ ዝቅ አድርጋ አስጠንቅቃለች። ማንም ምንም አላላትም።

በተደጋጋሚ በደቡብ ኮሪያ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመሰንዘር ማን ይደርስባታል?

ዛቻ ብቻ ሳይሆን ሠራዊት ድንበር ድረስ አስጠግታም ታውቃለች።

አሁን የኪም እህት ሳትሆን የኪም ልጅ ናት መነጋገሪያዋ።

ኪም ጆንግ ኡን ከእህታቸው ኪም ዮ ጁንግ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪም ጆንግ ኡን ከእህታቸው ኪም ዮ ጁንግ ጋር

የኪም ልጅ ለምን መነጋገሪያ ሆነች?

የቢቢሲዋ የሴዑል ዘጋቢ ጂን ማኬንዚ አንድ ነገር ትጠረጥራለች።

ምናልባት ኪም ጤናቸው እምብዛም አስተማማኝ አይደለም። አልፎ አልፎ አመም ያደርጋቸዋል።

ለኪም ሰሜን ኮሪያ አገራቸው ብቻ ሳትሆን ርስታቸው ናት። ርስትን ደግሞ ለልጅ እንጂ ለሌላ አያወርሱም።

ምናልባት ያ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ሰላም የራቀው የኮሪያ ልሳነ ምድር በሴት ቢመራ ሰላም ይወርድ ይሆናል። በሴት ቢሞከርስ?

የኪም ሴት ልጅ ለአቅመ ሥልጣን ደርሳ፣ ከኃይለኛዋ አክስቷ ይልቅ የመሪነት መንበሩን ትረከብ ይሆን?