የኪም ጆንግ ኡን እህትና የሰሜን ኮሪያዋ ኃያል ሴት ማን ናት?

ኪም ዮ ጆንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኪም ዮ ጆንግ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው መታየት የጀመረችው። ኪም ዮ ጆንግ ትባላለች። የታላቁና ክንደ ብርቱው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት የኪም ጁንግ ኡን ታናሽ እህት ናት።

ኪም ከእህት ወንድሞቹ ማንንም እንደሷ ያቀረበው ሰው የለም።

የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መዋቅር ግልጽ አይደለም።

ማን የማን አለቃ እንደሆነ በገሀድ አይታወቅም። ሆኖም ከወጣቱ መሪ ኪም በላይ ምንም የለም። እሱ ፈላጭ ቆራጭ ነው። ሁሉም ሰው ከእሱ በታች ነው። ከእሱ በታች ከሆኑት መካከል፣ ከበታቾች መካከል ደግሞ የበላይ የሆነች አንዲት ሴት አለች፤ ስሟም ኪም ዮ ጆንግ ነው።

ለዚህ ዘገባ እህት ኪም እያልን እንጠራታለን።

ለመሆኑ እህት ኪም ማን ናት?

እህት ኪም የታላቁ መሪ የኪም ቀጥተኛ ታናሹ ናት።

ለመጀመርያ ጊዜ በግላጭ የታየችው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ነበር።

ያን ጊዜ ከወንድሟ ጋር የጠላት አገር ደቡብ ኮሪያን ልትጎበኝ ሄደች። ያን ጊዜ የክረምት ኦሊምፒክን ለማዘጋጀት ሁለቱ ባላንጣ አገራት በጋራ ደፋ ቀና እያሉ ነበር።

ከዚያ በኋላ ከወንድሟ ጋር ሆና የደቡብ ኮሪያን ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢንን፣ የቻይናውን ሺ ጂን ፒንግን እንዲሁም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አገኘች።

በዚህ ጊዜ ነው ይቺ ሴት ቀላል ሰው እንዳልሆነች ዓለም መጠርጠር የጀመረው።

በሚያዝያ 2020 ክንደ ብርቱው ወንድሟ ኪም ጆንግ ኡን ከቴሌቪዥን መስኮት ጠፋ።

አገሬው ይህ ሰው አለቅጥ ወፍሮ ስኳሩና ደም ግፊቱ በርትቶበት ይሆን እያለ ተጨነቀ። በዚህ ጊዜ የሰሜን ኮሪያዊያን ተስፋ እሷ ነበረች፤ እህት ኪም።

ፕሬዝዳንት ኪም በጠፋበት ወቅት ዓለም በሙሉ እሱን ማን ሊተካው ይሆን ሲል ስሟን ደጋግሞ አነሳ።

የኪም እህት የፖለቲካ ሚና ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ የሆነው በጥቅምት 2017 ነበር። የፖሊት ቢሮ ተለዋጭ አባል ተደረገች።

ከዚያ በፊት የፕሮፓጋንዳና የንቅናቄ ሚኒስትር ምክትል ዳይሬክተር ነበረች። አሁንም ይህን ሥልጣን አልተወችውም።

እህት ኪም በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባቸው የሰሜን ኮሪያ ሹማምንት ዝርዝር ላይ ስሟ ከፊት ተቀምጧል።

በዚህ ጥቁር መዝገብ ስሟ ሊሰፍር የቻለው በሰሜን ኮሪያ ከሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ እጇ እንዳለበት በመረጋገጡ ነው።

በዚህ ማዕቀብ ስሟ በመኖሩ ማንኛውም የአሜሪካ ኩባንያም ሆነ ግለሰብ ከእሷ ጋር የገንዘብ ንክኪ እንዳይኖረው በሕግ ይከለክላል።

በእሷ ስም የተመዘገበ ንብረት በአሜሪካ ምድር ካለ እንዳይንቀሳቀስ ይታገዳል።

ኪም ዮ ጆንግ በወንድሟ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ተሳታፊ ናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪም ዮ ጆንግ በወንድሟ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ተሳታፊ ናት

እህት ኪም ምን ያህል ኃያል ናት?

በምስጢራዊቷ አገር ሰሜን አሜሪካ ማን የማን አለቃ ነው የሚለውን ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ እሙን ነው። ይህም በመሆኑ እህት ኪም ምን ያህል ሥልጣን ተሰፍሮ እንደተሰጣት የሚያውቀው ሰፋሪው ወንድሟ ኪም ብቻ ነው።

በሐሜት ደረጃ እንደሚወራው ግን ከወንድሟ ውጪ እሷን በሥልጣን የሚበልጥ ወንድም ሆነ ሴት በመላው ሰሜን ኮሪያ እንደሌለ ነው። ምናልባትም ከኪም ቀጥሎ 2ኛዋ ተፈሪ ሰው እሷ ናት።

እንደሚታመነው ከሆነ እህት ኪም ያገባችው የቾ ርዮንግ ሄ ወንድ ልጅን ነው።

ቾ ርዮንግ የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ናቸው።

ይህ ሐሜት እውነት ከሆነ እህት ኪም የበለጠ ተፈሪ የሚያደርጋት የጋብቻ ትስስር አድርጋለች ማለት ነው። ምክንያቱም በሰሜን ኮሪያ የኮሚኒስት ፓርቲን ዋና ጸሐፊነት የያዘ ሰው ሥልጣኑ የዋዛ እንዳልሆነ ማንም የሚረዳው ነው።

እህት ኪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ የማስፈራሪያ ቃላትን የያዙ መግለጫዎችን ስትሰጥ ነበር። ያነጣጠሩትም በጠላት አገር አሜሪካና በጠላት ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ላይ ነበር። ከቀናት በፊት ሰጥታ የነበረው መግለጫም አንዱ ተጠቃሽ ነው። በዚህም 'አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን እንዳታስቆጪ' ስትል አስፈራርታታለች።

ባለፈው ሰኔ እህት ኪም የአገራቸውን ሠራዊት ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ወደሆነው የሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ድንበር እንደምትልክ ስትዝት ነበር።

ይህን መግለጫ የሰጠችው ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ የከዱ ዜጎች የሚልኩትን የተቃውሞ ፊኛና በራሪ ወረቀቶች ማስቆም አለመፈለጓን ተከትሎ ነው።

ከዚህ ዛቻ በኋላ እህት ኪም የኮሪያዎች የግንኙነት ቢሮ እንዲዘጋ ማዘዟ ይታወሳል።

ከቀናት በኋላም ይኸው ዛቻዋ እውን ሆነና በሰኔ 16 ከባድ ፍንዳታ ተሰማ።

የደቡብ ኮሪያ የመረጃ ምንጮች እንዳረጋገጡት በ8 ሚሊዮን ዶላር እንዲታደስ ከደቡብ ኮሪያ ልገሳ የተደረገለት ይህ የሁለቱ ኮሪያዎች አገናኝ ቢሮ (ላይዘን ኦፊስ) ድምጥማጡ እንዲጠፋ ተደርጓል።

የዚህ ጥፋት አስፈጻሚም እህት ኪም እንደሆነች ተደርሶበታል።

የቀድሞው መሪ ኪም ጆንግ ኢል ልጆች የሆኑት ወንድምና እህት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው መሪ ኪም ጆንግ ኢል ልጆች የሆኑት ወንድምና እህት

የኪም የዘር ሐረግ?

ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ተተኪ ቢፈለግ በዝርዝሩ መጀመርያ ረድፍ የሚቀመጡት ሰዎች የኪም ቤተሰቦች እንደሚሆኑ እሙን ነው።

የአገሪቱ ፕሮፓጋንዳ ለዘመናት እንደሚናገረው ሰሜን ኮሪያ የምትመራው 'ፓክቱ' በሚባለው የዘር ሐረግ ነው። ይህም ሄዶ ሄዶ አገሪቷን የመሰረቷት ኪም ኢል ሱንግ ጋር ያደርሳል።

ወጣቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በርከት ያሉ ልጆች በይፋም በምስጢርም እንዳሉት ይገመታል። ሆኖም ልጆቹ ገና ለአቅመ ሥልጣን የበቁ አይደሉም።

እህት ኪም የዚህ ፓክቱ የሚባለው የዘር ሐረግ ስላላት ወንድሟ አንድ ነገር ቢሆን ከእሷ የተሻለ ለአገር መሪነት የቀረብ ሰው ላይኖር ይችላል።

ኪም ዮ ጆንግ የቀድሞ የሰሜን ኮሪያ መሪ የኪም ጆንግ ኢል ትንሽዋ ሴት ልጅ ናት።

ኪምና እሷ ከአንድ አብራክ ነው የተገኙት። ሌላ ኪም ጆንግ ቾል የሚባል ወንድምም አላቸው። ሆኖም ቾል ፖለቲካው ላይ እስከዚህም ነው።

እህት ኪም የተወለደችው እንደ አውሮፓውያኑ በ1987 ሲሆን ከወንድሟ ኪም ጆንግ ኡን በ4 ዓመት ታንሳለች።

ሁለቱም የተማሩት በውዷና በባለጸጋዋ አውሮፓዊት አገር ስዊትዘርላንድ፣ በርን ከተማ ነበር። በበርን ከተማ የተወሰኑ ዓመታትንም ኖረዋል።

የስዊትዘርላንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በእህት ኪም የስዊትዘርላንድ የትምህርት ቤት ቆይታ ወቅት በበርካታ ልዩ ጠባቂዎች እና ምስጢራዊ ክትትል አድራጊዎች እየተጠበቀች ነበር የተማረችውም፣ የኖረችውም።

በአንድ ወቅት መጠነኛ ጉንፋን ይዟት በከፍተኛ ጥድፊያ ሆስፒታል ተወስዳ እንደነበረም ያስታውሳሉ። አንዳንድ ሪፖርቶች እንዳረጋገጡት እሷ የተለየ ጥበቃ ሲደረግላትና ገለል ብላ ስትኖር ልጅነቷን ከብዙ ወዳጅ ዘመድ ጋር ሳትገናኝ አሳልፋለች።

አሁን በሰሜን ኮሪያ ያላት ኃላፊነትና የሥልጣን ድንበር ባይታወቅም በዋናነት ስትሰራ የቆየችው ግን የወንድሟን ምስልና ገጽታ ከፍ ከፍ ማድረግ ላይ ነው።

የወንድሟ ኪም የፖለቲካ አማካሪው እና ልዩ ረዳቱ እንደሆነችም ከምትሰራው ሥራ ተነስቶ መገመት ይቻላል።

በ2019 ኪም ከትራምፕ ጋር ቬትናም ሀኖይ ውስጥ ተገናኝተው ውይይታቸው ፍሬ ሳያፈራ ከቀረ በኋላ፤ እህት ኪም ከእይታ ተሰውራ ነበር። ይህም ምናልባት ከሥልጣኗ ተባራ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል።

ሆኖም በ2020 ወደ ፖሊት ቢሮ ተለዋጭ አባልነቷ ተመልሳ ሥራዋን ተግታ እየከወነች ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 አባቷ ሲሞቱ ቀብር ላይ ታየች። ከዚያ በኋላም አልፎ አልፎ ካልሆነ ታይታ አታውቅም ነበር። በ2014 ደግሞ ወንድሟ ሲመረጥ በዓለ ሲመቱ ላይ ተገኘች።

ቀጣይ የሰሜን ኮሪያ መሪ?

አሁን በሰሜን ኮሪያ አንዳች ኮሽታ ሲሰማ፣ የወንድሟ ከእይታ ሲሰወር ወይም ሲታመም እህት ኪም ትልቅ መነጋገርያ ትሆናለች። ሰሜን ኮሪያም ሆነ ዓለም የሚረዳው እሷ ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ መሪ እንደምትሆን ነው።

ነገር ግን በሰሜን ኮሪያ እንኳን ስለ መጪው ሥልጣን ስለ ዛሬም ቢሆን በእርግጡ የሚታወቅም የሚነገርም ነገር የለም።

በሰሜን ኮሪያ የፖለቲካ ምስጢር ጥብቅ ሐይማኖት ነው። ለሹመት ስትጠበቅ እንደ ታላቁ የኪም አጎት በአደባባይ ልትገደልም ትችላለች። በሰሜን ኮሪያ የሥልጣን ግምት መስጠት እጅግ አስቸጋሪ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሰሜን ኮሪያ ለምን ኑክሊዬርን መረጠች?