ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን የሚያጥላሉ በራሪ ወረቀቶችን ልትበትን መሆኑ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን የሚያጥላላ ፕሮፖጋንዳ የያዙ በራሪ ወረቀቶን እያዘጋጀች መሆኑን አስታወቀች።
የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው፤ ደቡብ ኮሪያን እና ከሰሜን ኮሪያ የከዱ ሰዎችን የሚያጥላሉ ጽሑፎች የያዙ በራሪ ወረቀቶች ሊበተኑ ዝግጅት ተጠናቋል።
ሰሜን ኮሪያ በራሪ ወረቀቶቹን ከደቡቧ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ እንደምትበትን አስታውቃለች።
“በደቡብ ኮሪያ እጅጉን የተበሳጨው የሰሜን ኮሪያ ሕዝብ፤ በስፋት የሚሰራጩ በራሪ ወረቀቶች ዝግጅት ላይ ይገኛል” ሲል ኮሪያን ሴንተራል ኒው ኤጀንሲ (ኬሲኤንኤ) ዘግቧል።
“የወረቀቱ ክምር ተራራ እክሏል” ሲል የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ጨምሮ ዘግቧል።
ከሰሜን ኮሪያ ሸሽተው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚሻገሩ ሰዎች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ፊኛዎችን ወደ አገራቸው ሰሜን ኮሪያ ይልካሉ። ይህንን የሚያደርጉትም ከደቡብ ኮሪያ የድንበር ከተማ ሆነው ነው።
ሰሜን ኮሪያን የሸሹት ብቻም ሳይሆን የደቡብ ኮርያ መብት ተሟጋቾች ጭምር በርካታ መልዕክት የያዙ ረዣዥም ፊኛዎችን ወደ ጎረቤታቸው ይልካሉ።
በፊኛዎቹ ውስጥ የሚጠቀለሉት መልዕክቶች በአመዛኙ ሰሜን ኮሪያ ዜጎቿን በጭቆና አረንቋ ማኖሯን እንድትተው የሚወተውቱ ናቸው። አንዳንዶቹ መልዕክቶች ደግሞ የብሽሽቅ ይዘት ያላቸው ናቸው።
በሌላ ወቅት ደግሞ ቸኮሌት እና የመልካም ምኞት መልዕክት የሰፈረባቸው ፖስት ካርዶች በፊኛዎቹ ይላካሉ። ይህ ተግባር ሰሜን ኮሪያን እንጅግ ሲያበሳጭ ቆይቷል።
ለዚህም ሰሜን ኮሪያ ከድተዋት በደቡብ ኮሪያ የሚገኙትን ዜጎቿን ተጠያቂ ታደርጋለች።
ባሳለፍነው ሳምንት ሰሜን ኮሪያን ከደቡብ ኮሪያ የሚያቀራርብ እና ድንበር ላይ የሚገኘውን ጊዜያዊ ቢሮ በቦንብ ማጋየቷ ይታወሳል። ይህ ቢሮ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ አቁሞ ለአገልግሎት ዝግ ሆኖ ቆይቶ ነበር።
በሰሜን ኮሪያ ግዛት ድንበር ላይ ይገኝ የነበረው ቢሮ የተከፈተው ከ2 ዓመት በፊት ነበር።
የጊዜያዊ ቢሮው አገልግሎትም ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ማቀራረብ ነበር። የአገናኝ ቢሮው መውደም በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ እየተሸሻለ የነበረው ግንኙነት ማክተሙን የሚያረዳ ነው ተብሏል።
የደቡብ ኮሪያ የሁለቱ ኮሪያ ሕዝቦች አገናኝ ሚንሰትር፤ ሰሜን ኮሪያ በራሪ ወረቀቶቹን ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመበተን ማሰቧ ‘በጣም አሳዛኝ ነው’ ብለውታል። ሰሜን ኮሪያም ይህን እቅዷን እንድትሰርዝ ጠይቀዋል።
መቀመጫቸውን ደቡብ ኮሪያ ያደረጉ እና ከኮሪያ የከዱ የአንድ ቡድን አባላት፤ በሩዝ፣ መድሃኒት እና የፊት እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የተሞሉ ፕላስቲክ ጠርሙሶች ወደ ሰሜን ኮሪያ ለመላክ ይዘውት የነበረውን እቅድ መተዋቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የዚህ ቡድን አባላት ፕላስቲክ ጠርሙሶቹን በሁለቱ አገራት መካከል በሚፈስ ወንዝ ውስጥ ለመጣል ነበር እቅዳቸው። ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደም ወደ ደቡብ ኮሪያ መሰል የፕሮፖጋንዳ ጽሁፎችን የምትልከው ትልልቅ ፊኛዎችን በመጠቀም ነበር።












