ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሩዋንዳ ጦርነት የሚቀሰቅስ ድርጊት ፈጽማለች ስትል ከሰሰች

ሱክሆይ-25

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሱክሆይ-25 ተዋጊ አውሮፕላን

በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ መካከል ያለው ፍጥጫ በተባባሰበት ጊዜ ሩዋንዳ በአንድ ተዋጊ አውሮፕላኗ ላይ ተኩስ መክፈቷ “የጦርነት ድርጊት ነው” ስትል ኮንጎ አወገዘች።

የሩዋንዳ መንግሥት ግን የግዛቱን የአየር ክልል በጣሰው የጦር አውሮፕላን ላይ “የመከላከል እርምጃ ነው የወሰድኩት” ሲል የዲሞክራቲክ ኮንጎን ክስ ውድቅ አድርጓል።

በምሥራቃዊ ኮንጎ ለ400 ሺህ ሕዝብ መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ይህ ውዝግብ በሁለቱ አገራት መካከል የተከሰተ ዋነኛ ፍጥጫ ነው።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ አሜሪካ እና የተባበሩት መንሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ኤም23 የተባለውን የኮንጎ አማጺ ቡድን ሩዋንዳ ትደግፋለች ሲሉ ከሰዋል።

ሩዋንዳ ግን የቀረበባትን ክስ በማስተባበር በማዕድናት የበለጸገ በሆነው አካባቢ ላለው ግጭት የኮንጎን ምንግሥት ተጠያቂ ታደርጋለች።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎች ሩዋንዳ ወደ ግዙፏ ጎረቤቷ ኮንጎ ሁለት ጊዜ ወታደሮቿን አሰማርታ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ቢያንስ ዘጠኝ አገራት ተሳትፈው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሞተበት ከባድ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ነገር ግን ቢቢሲ ያላረጋገጣቸው ምስሎች በኮንጎዋ ጎማ እና በሩዋንዳዋ ጊሲኒዬ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ዝቅ ብሎ ሲበር በነበረ ሱክሆይ-25 የተባለ የጦር አውሮፕላን ላይ ሲተኮስበት አሳይተዋል።

በሌሎች ምስሎች ላይ ደግሞ አውሮፕላኑ በጎማ አየር ማረፊያ ውስጥ ካረፈ በኋላ በቀኝ ክንፉ ላይ የተነሳ እሳትን ለማጥፋ ውሃ ሲረጭበት ታይቷል።

ነገር ግን ዲሞክራቲክ ኮንጎ እንዳለችው ተዋጊ አውሮፕላኑ “ከባድ የሚባል ጉዳት አልደረሰበትም።”

የኮንጎ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በቅርብ በተካሄዱ ንግግሮች በአገሪቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የትግበራ ሂደት “እያደናቀፈች ነው” ሲል ሩዋንዳን ከሷል።

የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ ጨምሮም ዲሞክራቲክ ኮንጎ “ግዛቷን የመከላከል መብት ያላት ሲሆን፣ ይህንንም ከማድረግ ወደ ኋላ እንድትል የሚያሰጋት ነገር አይኖርም” ብሏል።

“መንግሥት ይህንን የሩዋንዳ ተደጋጋሚ ጥቃት ሆን ተብሎ የሚደረግ ድርጊት አድርጎ ይመለከተዋል” ብሏል የሚኒስቴሩ መግለጫ።

ነገር ግን ሩዋንዳ በበኩሏ ወደ አየር ክልሏ የኮንጎ ተዋጊ ጀት ሲገባ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጎረቤቷ “ይህንን ግጭት የመጫር ድርጊት” እንድታቆም ጠይቃለች።

ባለፈው ኅዳር ወር ሌላ የኮንጎ ሱክሆይ-25 ተዋጊ ጀት ሩዋንዳ ውስጥ በሚገኘው ጊሴኒዬ አየር ማረፊያ ለአጭር ጊዜ አርፎ ነበር። በወቅቱም ኮንጎ በሰጠችው ምላሽ ተዋጊ አውሮፕላኑ ያረፈው “በስህተት” ነው ብላለች።

ይህ አሁን የተከሰተው ውዝግብ እና መካሰስ ወትሮውንም በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን ፍጥጫ አባብሶት ወደ ጦርነት እንዳያስገባቸው ስጋት ተፈጥሯል።