የድሬዳዋ ከተማ አወቃቀር አከራካሪ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? መፍትሔውስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ራሱን አሊያም ወደ ሌሎች ክልሎች ለመቀላቀል ለሁለቱም ምክር ቤቶች ጥያቄ አቅርቧል የሚል ዘገባ ተሰምቶ ነበር።
ከረዥም ዓመታት በፊት በቻርተር የተቋቋመው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ ክልል መሆን አልያም ከኦሮሚያ ወይም ከሶማሊ ክልል ጋር ለመቀላቀል ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርቧል መባሉ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ካሉ ሁለት የድሬዳዋ እንደራሴዎች መካከል አንዱ አብዱልጀዋድ ሞሐመድ ሕዝበ-ውሳኔው ከተማዋ ለሚያጋጥማት የበጀት እና የአስተዳደር ችግር መፍትሔ ይሆናል ይላሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ “በበጀት ጉዳይ ተወካዩ ያነሱት ሐሳብ ትክክል ነው” ቢሉም፣ ክልል የመሆን አሊያም ከሌሎች ክልሎች ጋር የመቀላቀልን ሐሳብ አስተዳደሩ እንደማይጋራው ይናገራሉ።
የድሬዳዋ ከተማ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ብሩክ ፈለቀ “ሕዝበ-ውሳኔ ተደርጎ ወደ አንድ ክልል እንጠቃለል የሚለው ሐሳብ የበላይ ኃላፊዎች አልተነጋገርንበትም፤ አቋሟችንም አይደለም፤ የሕዝቡ ጥያቄም አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማዋ አስተዳደር መዋቅርን በተመለከተ የተለያዩ ፍላጎቶች የሚንፀባረቁ ሲሆን የድሬዳዋ ጉዳይ የውጥረት መነሻም ሲሆን ይስተዋላል።
ለመሆኑ ከተማዋ አሁን የምትዳደርበትን አወቃቀር እንዴት አገኘች? መሠረታዊው ችግርስ ምንድነው? መፍትሔዎቹስ?
“ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት የሌለው”
የሕግ ባለሙያው ዳንዔል አሰፋ ትኩረታቸውን በሕገ-መንግሥት ዙሪያ ጥናት በመሥራት ይታወቃሉ።
የሕግ ባለሙያው፤ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እና ሕገ-መንግሥት መሠረት የአገሪቱ አካል ናቸው ተብለው ገቢ መሰብሰብ እና ሕዝብ ማስተዳደር የሚችሉት ዘጠኙ ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ናቸው ይላሉ።
ባለሙያው አክለውም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አመሠራረት የሕገ-መንግሥቱን ሂደት ያልተከተለ መሆኑ አሁን የሚነሱት ጥያቄዎችን ሊያመጣ ችሏል ብለው ያምናሉ።
ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) አዲስ አበባ እና ድሬደዋን በተመለከተ ሰፊ እና ጥልቅ ጥናቶች ካደረጉ ምሑራን መካከል ናቸው።
ኢትዮጵያ ሳሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት የነበሩት ሚልኬሳ አሁን መቀመጫቸውን ሰሜን አሜሪካ ያደረጉ ሲሆን ሥልጣን ያለውን መንግሥት በፅኑ በመተቸት ይታወቃሉ።
“ድሬዳዋን ሕገ-መንግሥቱ አያውቃትም። ሩዋንዳ ወይም ናይጄሪያ ውስጥ ልትሆን ትችላለች” በማለት ይህን ያመጣው በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ነው ይላሉ።
የሕግ ባለሙያው በበኩላቸው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካላት ፍላጎት እና ጥያቄዎችን ሳይመልስ እንደተመሠረተ ያወሳሉ። ዳንዔል ከተማዋ ስትመሠረት “ሁለት አማራጮችን መጠቀም ይቻል ነበር” የሚል ሐሳብ አላቸው።
“የመጀመሪያው ሕገ-መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የገቢ መሰበስብም ሆነ ሕዝቡን የማስተዳደርን ሥልጣን ዕውቅና እንዲኖረው ማድረግ ይቻል ነበር። ሁለተኛው አማራጭ ልክ እንደሌሎች አካባቢዎች በሕዝበ-ውሳኔ ወደ አንዱ ክልል እንድትጠቃለል ማድረግ ነበር።”
በወቅቱ “ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት የሌለው” የከተማ አስተዳደሩ በማዋቀር ከተማዋ በዕድገት ወደ ኋላ እንድትቀር እንዲሁም ከተጠቃሚነት እንድትጎድል አድርጓል ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
በተጨማሪም ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች እያደጉ ሲመጡ ድሬዳዋ በተቃራኒው ወደኋላ ቀርታለች ሲሉ ሐሳባቸውን ያጋራሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ተጠሪነቷ ለፌዴራሉ መንግሥት ቢሆንም ነገር ግን “የከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመበት ቻርተር የሕገ-መንግሥት መሠረት የለውም” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
40-40-20 የሥልጣን ክፍፍል
የድሬዳዋ ከተማ እና የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን በተለመከተ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሄዱት ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) እንደሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ሌላ የገጠመው ችግር የጀመረው በ97ቱ ምርጫ ወቅት እንደሆነ ያወሳሉ።
ሚልኬሳ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የሆነውን እንዲህ ያስታውሳሉ።
ድሬዳዋ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በወቅቱ የኦሮሚያ ክልልን ለሚወክለው ፓርቲ (ኦህዴድ) ድምፅ አትስጡ እያሉ ቅስቀሳ ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ።
በዚህም ምክንያት ድሬዳዋ በፓርላማ ካላት ሁለት ወንበሮች ውስጥ አንዱን ቅንጅት ሲያሸንፍ አንዱን ደግሞ የሶማሊ ክልል ፓርቲ (ሶኢዴፓ) ወሰደ።
“ይህንን ክስተት ተከትሎ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሕዝቡን ‘የኦሮሞ ሕዝብ እውነትም ተጎድተሃል። ከአሁን በኋላ ከንቲባ ከኦሮሞ እና ከሶማሊ እናደርጋለን። ነገር ግን ድጋፋችሁን እንፈልጋለን’ በማለት በወቅቱ የቅንጅት አባላትን ለእሥር ዳረገ።”
ሚልኬሳ እንደሚሉት ከዚህ ምርጫ በኋላ ከተማዋን በጊዜያዊ አስተዳደር እንድትመራ በማድረግ ከኦህዴድ እና ከሶኢዴፓ የተመረጡ ከንቲባዎች እየተፈራረቁ እንዲያስተዳድሩት ሆነ።
የካቢኔው አወቃቃር “40-40-20” በሚባል ሥርዓት እንዲመራ እንደሆነ ምሑሩ ያስረዳሉ።
“40 በመቶ ኦህዴድ፤ 40 በመቶ ሶኢዴፓ፤ የተቀረው 20 በመቶ ከአማራ እና ከትግራይ ክልል የሆኑ ሰዎች እንዲሆኑ ተደረገ። የከተማዋን አስተዳደር ምክር ቤት በተመሳሳይ መልክ እንዲሆን በማድረግ የሥልጣን ክፍፍል አመጡ።”
መፍሔው ምን ይሆን?
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አወቃቀር በሕዝበ-ውሳኔ መፈታት የነበረበት “በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ነበር” የሚሉት ሚልኬሳ፣ አሁን መቅደም ያለበት ይህ አይደለም ብለው ያምናሉ።
“የከተማዋ ነዋሪዎች የአስተዳደር አወቃቀር ጥያቄ የጠየቁ አይመስለኝም። ‘ክልል እንሁን’ ብለውም እየጠየቁ አይደለም” በማለት ጥያቄ ቢነሳ እንኳ ከሕዝቡ ነው መምጣት ያለበት ይላሉ።
ምሑሩ ከዚህ ጥያቄ በፊት ቀድመው መምጣት አለባቸው ከሚሏቸው ነገሮች አንዱ “የከተማዋ የሥራ ቋንቋ” ነው።
አማርኛ የድሬዳዋ ከተማ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ሲሆን ነገር ግን በቁጥር የሚበልጠው ሕዝብ ኦሮምኛ እና ሶማሊኛ የሚናገር እንደሆነ ጠቁመው “የአገልግሎት እና የቋንቋ ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም። ሰብዓዊ መብት ነው” በማለት ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ እና ሶማሊኛ መጨመር እንደሚቻል ይናገራሉ።
ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት ጉዳይ በከተማዋ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች “ሕዝቡን በሚመስል መልኩ” መልሶ ማደራጀት ያስፈልጋል።
እነዚህ ጉዳዮች እና ሌሎችም ጥያቄዎች ከተፈቱ በኋላ የአስተዳደር አወቃቀር ጥያቄ መምጣት ይችላል ይላሉ።
የሕግ ባለሙያው ዳንዔል አሰፋ ግን የከተማዋን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ለመፍታት መቅደም ያለበት መፍትሔ የአስተዳደር ጥያቄውን መፍታት ነው ይላሉ።
“የትኛውም ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው። በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ ቁጥር 39 መሠረት የድሬዳዋ ሕዝብ የራሱ ዕጣ ፈንታ በራሱ መወሰን ይችላል።”
ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ለማስፈፀም የሚኬድበት አማራጭ ድሬዳዋ ራሷን ችላ ክልል እንድትሆን ማድረግ አሊያም ከሌሎች ክልሎች ጋር እንድትቀላቀል ማድረግ ነው።
የሕግ ባለሙያው ድሬዳዋ ራሷን ችላ ክልል መሆኗ “የሚቻል እና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚያመጣ አይመስለኝም” ይላሉ።
ከተማዋ በሁለት ክልሎች መካከል መገኘቷ እና የወሰን ጥያቄ፤ ሁለት ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ብሔሮች ግንኙነትን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ሌሎች ብሔሮች ጉዳይ ድሬዳዋ ራሷን ችላ ክልል እንዳትሆን ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይናግራሉ።
ዳንዔል አክለው ወደ አንዱ ክልል መጠቃለል የሚለው ጉዳይም ቀላል የሚሆን እንዳልሆነ ይገልጣሉ።
“ነገር ግን የሕዝቡ ጥያቄ አጥጋቢ የሆነ ምላሽ እንዲያገኝ ከተፈለገ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማበጀት መልካም ነው።”
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሕገ-መንግሥት መሠረት አግኝቶ ራሱን የቻለ አስተዳደር የመሆን ጉዳይ “የዘገየ ፍርድ” እንደሆነ የሚጠቅሱት የሕግ ባለሙያው ለድሬዳዋ ነዋሪ የሚበጀው “ሕዝቡ ራሱ የሚወስነው ውሳኔ ነው” ይላሉ።
የሕገ-መንግሥት ባለሙያው ድሬዳዋ ከአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ውጪ እየተዳደረች በምትገኝበት ወቅት ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ርቋት እንደቆየ ያነሳሉ።
የከተማዋ አስተዳደር አወቃቀር መፍትሔ ከተገኘለት በኋላ “መንግሥት ድሬዳዋ ልክ እንደሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደታድግ የማድረግ ግዴት አለበት” ይላሉ።












